YouVersion Logo
Search Icon

ዘዳግም 1

1
እስራኤል ከኮሬብ እንዲነሡ የተሰጠ ትእዛዝ
1ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ዓረባ በተባለው ምድረ በዳ ከሱጰ ትይዩ፣ በፋራንና በጦፌል፣ በላባን፣ በሐጼሮትና በዲዛሃብ መካከል ሳሉ፣ ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ የተናገረው ቃል ይህ ነው። 2(በሴይር ተራራ መንገድ ከኮሬብ እስከ ቃዴስ በርኔ ዐሥራ አንድ ቀን ያስሄዳል)።
3በአርባኛው ዓመት፣ በዐሥራ አንደኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን እስራኤላውያንን በሚመለከት እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘውን ሁሉ ሙሴ ለእነርሱ ነገራቸው። 4ይህ የሆነው በሐሴቦን ይገዛ የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንና በአስታሮት ይገዛ የነበረውን የዐግን ንጉሥ ባሳንን በኤድራይ ድል ካደረገ በኋላ ነው።
5ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በሞዓብ ምድር ሳሉ፣ ሙሴ ይህን ሕግ እንዲህ እያለ መግለጥ ጀመረ፤
6 እግዚአብሔር አምላካችን (ያህዌ ኤሎሂም) በኮሬብ እንዲህ አለን፤ “እነሆ፤ በዚህ ተራራ ለረጅም ጊዜ ቈይታችኋል። 7ሰፈር ነቅላችሁ ወደ ኰረብታማው የአሞራውያን አገር ጕዞ ቀጥሉ፤ ከዚያም በዓረባ፣ በተራሮቹ፣ በምዕራብ ኰረብታዎች ግርጌ፣ በኔጌብና በባሕሩ ዳርቻ ወዳሉት አጐራባች ሕዝቦች ሁሉ ሂዱ፤ እንዲሁም ወደ ከነዓናውያን ምድርና ወደ ሊባኖስ፣ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ዝለቁ። 8እነሆ፤ ይህችን ምድር ሰጥቻችኋለሁ፤ እንግዲህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአባቶቻችሁ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ፣ ከእነርሱም በኋላ ለዘሮቻቸው ሊሰጥ የማለላቸውን ምድር ገብታችሁ ውረሱ።”
የመሪዎች መሾም
9እኔም በዚያን ጊዜ እንዲህ አልኋችሁ፤ “ብቻዬን ልሸከማችሁ አልችልም፤ 10አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቍጥራችሁን ጨምሯል፤ ስለዚህ ዛሬ እናንተ እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝታችኋል። 11አሁንም የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሺሕ ጊዜ ያብዛችሁ፣ በሰጠውም ተስፋ መሠረት ይባርካችሁ! 12ይሁን እንጂ ችግራችሁን፣ ሸክማችሁንና ክርክራችሁን ሁሉ ብቻዬን እንዴት አድርጌ መሸከም እችላለሁ? 13ጥበበኞችን፣ አስተዋዮችንና የተከበሩ ሰዎችን ከየነገዳችሁ ምረጡ፤ እኔም በእናንተ ላይ እሾማቸዋለሁ።”
14እናንተም፣ “ይደረግ ዘንድ ያቀረብኸው ሐሳብ መልካም ነው” ብላችሁ መለሳችሁልኝ።
15ስለዚህ እኔም የየነገዶቻችሁን አለቆች ጥበበኞችንና የተከበሩትን ሰዎች ተቀብዬ፣ ሻለቆች፣ መቶ አለቆች፣ አምሳ አለቆችና ዐሥር አለቆች እንዲሁም የየነገዱ ሹማምት በማድረግ በእናንተ ላይ ሥልጣን እንዲኖራቸው ሾምኋቸው። 16በዚያን ጊዜም ዳኞቻችሁን እንዲህ ስል አዘዝኋቸው፤ “በወንድሞቻችሁ መካከል የሚነሣውን ክርክር ያለ አድልዎ እዩት፤ ሙግቱ ወንድማማች በሆኑ እስራኤላውያን መካከል ወይም በአንድ እስራኤላዊና በመጻተኛ መካከል ቢሆን፣ በትክክል ፍረዱ። 17በፍርድ አድልዎ አታድርጉ፤ ትልቁንም ትንሹንም እኩል እዩ፤ ፍርድ የእግዚአብሔር ስለሆነ፣ ማንኛውንም ሰው አትፍሩ። ከዐቅማችሁ በላይ የሆነውን ሁሉ ወደ እኔ አምጡት፤ እኔ አየዋለሁ።” 18በዚያን ጊዜ ማድረግ የነበረባችሁን ሁሉ ነገርኋችሁ።
የሰላዮች መላክ
19ከዚያም አምላካችን እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘን መሠረት ከኮሬብ ተነሥተን እንዳያችሁት በዚያ ጭልጥ ባለና በሚያስፈራ ምድረ በዳ ዐልፈን፣ በኰረብታማው በአሞራውያን አገር በኩል ወደ ቃዴስ በርኔ መጣን። 20እኔም፣ እንዲህ አልኋችሁ፤ “አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጠን ወደ ኰረብታማው የአሞራውያን አገር ደርሳችኋል፤ 21እነሆ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ምድሪቱን ሰጥቷችኋል፤ አሁንም የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በነገራችሁ መሠረት ውጡ፤ ውረሷትም፤ አትፍሩ፤ አትደንግጡም።”
22ከዚያም ሁላችሁ ወደ እኔ መጥታችሁ፣ “ምድሪቱን እንዲሰልሉልን ሰዎች አስቀድመን እንላክ፤ እነርሱም ወደዚያ የሚያደርሰንን መንገድና የምንሄድባቸውን ከተሞች በማጥናት ተመልሰው ይነግሩናል” አላችሁ።
23ይህም ሐሳብ መልካም መስሎ ታየኝ፤ እኔም ከእያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ ሰው በማድረግ ከእናንተ ዐሥራ ሁለት ሰዎች መረጥሁ። 24እነርሱም ተነሥተው ወደ ኰረብታማው አገር ከወጡ በኋላ ወደ ኤሽኮል ሸለቆ መጥተው ምድሪቱን ሰለሉ።
25ከምድሪቱም ፍሬ ወደ እኛ ይዘው በመምጣት፣ “አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚሰጠን ምድር መልካም ናት” ብለው ነገሩን።
በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ
26እናንተ ግን ለመውጣት ፈቃደኞች አልነበራችሁም፤ በአምላካችን በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዝ ላይ ዐመፃችሁ። 27በየድንኳኖቻችሁ ሆናችሁ እንዲህ ስትሉ አጕረመረማችሁ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ጠልቶናል፤ ስለዚህም ከግብፅ ያወጣን አሞራውያን እንዲያጠፉን በእጃቸው አሳልፎ ሊሰጠን ነው። 28ታዲያ ወዴት መሄድ እንችላለን? ወንድሞቻችን፣ ‘ሰዎቹ ከእኛ ይልቅ ብርቱዎችና ቁመተ ረጃጅሞች፣ ከተሞቹም ትልልቆችና እስከ ሰማይ በሚደርስ ቅጥር የታጠሩ ናቸው፤ እንዲያውም በዚያ የዔናቅን ልጆች አይተናቸዋል’ ሲሉ እንድንፈራ አድርገውናል።”
29እኔም አልኋችሁ፤ “አትሸበሩ፤ አትፍሯቸውም። 30በፊታችሁ የሚሄደው አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከዚህ በፊት ዐይናችሁ እያየ በግብፅ እንዳደረገላችሁ ሁሉ፣ አሁንም ለእናንተ ይዋጋል፤ 31በምድረ በዳው እንደ አደረገው ሁሉ። በዚያም አባት ልጁን እንደሚሸከም፣ እናንተን አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እዚህ ስፍራ እስክትደርሱ በመጣችሁበት መንገድ ሁሉ እንዴት እንደ ተሸከማችሁ አይታችኋል።”
32ይህም ሆኖ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አልታመናችሁም፤ 33በጕዞ ላይ ሳላችሁ የምትሰፍሩባቸውን ቦታዎች ለመፈለግና የምትሄዱበትን መንገድ ለማሳየት እርሱ ሌሊት በእሳት፣ ቀን በደመና ይመራችሁ ነበር።
34 እግዚአብሔርም (ያህዌ) እናንተ ያላችሁትን በሰማ ጊዜ ተቈጣ፤ ማለም፤ 35“ለቀደሙት አባቶቻችሁ ለመስጠት የማልሁላቸውን መልካሚቱን ምድር፣ ከዚህ ክፉ ትውልድ አንድም ሰው አያያትም፤ 36ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብ በስተቀር የሚያያት የለም፤ እርሱ ያያታል፤ እግዚአብሔርን (ያህዌ) በፍጹም ልቡ ስለ ተከተለ፣ የረገጣትን ምድር ለእርሱና ለዘሮቹ እሰጣለሁ።”
37በእናንተ ምክንያት እግዚአብሔር (ያህዌ) እኔን ተቈጥቶ እንዲህ አለኝ፤ “አንተም ብትሆን አትገባባትም። 38ረዳትህ የነዌ ልጅ ኢያሱ ግን ይገባባታል፤ ምድሪቱን እንዲወርሱ እስራኤልን የሚመራ እርሱ ስለሆነ፣ አበረታታው። 39ይማረካሉ ያላችኋቸው ታናናሾች፣ ክፉና በጎውን ለይተው የማያውቁት ልጆቻችሁ ምድሪቱን ይገቡባታል፤ ለእነርሱም እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ይወርሷታል። 40እናንተ ግን፣ ተመልሳችሁ ወደ ቀይ ባሕር#1፥40 ዕብራይስጡ፣ ያም ሳውፍ ይለዋል፤ ይኸውም፣ የደንገል ባሕር ማለት ነው። የሚወስደውን መንገድ ይዛችሁ ወደ ምድረ በዳው ተጓዙ።”
41እናንተ፣ “እግዚአብሔርን (ያህዌ) በድለናል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ባዘዘንም መሠረት ወጥተን እንዋጋለን” ብላችሁ መለሳችሁልኝ። ወደ ተራራማው አገር መሄድ ቀላል መስሎ ስለ ታያችሁ፣ እያንዳንዳችሁ የጦር መሣሪያችሁን ታጥቃችሁ ተነሣችሁ።
42 እግዚአብሔር (ያህዌ) ግን፣ “እኔ ከእናንተ ጋር አልሆንምና ወጥታችሁ እንዳትዋጉ፤ በጠላቶቻችሁ ድል ትነሣላችሁ ብለህ ንገራቸው” አለኝ።
43እኔም ነገርኋችሁ፤ እናንተ ግን አላዳመጣችሁም፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ትእዛዝ ላይ ዐምፃችሁ፣ በትዕቢታችሁ ወደ ኰረብታማዪቱ አገር ዘመታችሁ። 44በእነዚያ ኰረብቶች ላይ የሚኖሩት አሞራውያን ሊወጓችሁ ወጡ፤ እንደ ንብ ሰራዊትም ሆነው አባረሯችሁ፤ ከሴይር አንሥቶ እስከ ሔርማ ድረስ አሳድደው መቷችሁ። 45እናንተም ተመልሳችሁ መጥታችሁ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አለቀሳችሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) ልቅሷችሁን አልሰማም፤ አላዳመጣችሁምም። 46ስለዚህ ያን ያህል ጊዜ በማጥፋት በቃዴስ ብዙ ቀን ቈያችሁ።

Currently Selected:

ዘዳግም 1: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in