2 ሳሙኤል 16
16
ዳዊትና ሲባ
1ዳዊት ከተራራው ጫፍ ባሻገር ጥቂት ዕልፍ ብሎ እንደ ሄደ፣ ሲባ የተባለው የሜምፊቦስቴ አገልጋይ፣ ሁለት መቶ እንጀራ፣ አንድ መቶ ጥፍጥፍ ዘቢብ፣ አንድ መቶ ጥፍጥፍ በለስና አንድ አቍማዳ የወይን ጠጅ የተጫኑ ሁለት አህዮች እየነዳ ሊገናኘው መጣ።
2ንጉሡም ሲባን፣ “ይህን ሁሉ ያመጣኸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።
ሲባም “አህዮቹን የንጉሡ ቤተ ሰዎች እንዲቀመጡባቸው፣ እንጀራውንና በለሱን ወጣቶቹ እንዲበሉት፣ የወይን ጠጁን ደግሞ በምድረ በዳ የደከሙት እንዲጠጡት ነው” አለው።
3ከዚያም ንጉሡ፣ “የጌታህ ልጅ የት ነው?” ሲል ጠየቀው።
ሲባም፣ “ ‘የእስራኤል ቤት ዛሬ የአባቴን መንግሥት ይመልስልኛል’ ብሎ ስለሚያስብ፣ በኢየሩሳሌም ተቀምጧል” አለው።
4ከዚያም ንጉሡ ሲባን፣ “የሜምፊቦስቴ የነበረው ሁሉ ከእንግዲህ ያንተ ነው” አለው።
ሲባም፣ “በታላቅ ትሕትና በግንባሬ ተደፍቼ እጅ እነሣለሁ፤ ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ በፊትህ ሞገስ ላግኝ” አለው።
ሳሚ ንጉሥ ዳዊትን ረገመ
5ንጉሥ ዳዊት ወደ ብራቂም ሲደርስ፣ ከሳኦል ቤተ ሰብ ነገድ የሆነ አንድ ሰው ብቅ አለ፤ እርሱም የጌራ ልጅ ሳሚ ነው፤ እየተራገመም ወጣ። 6የንጉሡ ወታደሮችና የክብር ዘቦቹ ሁሉ በዳዊት ግራና ቀኝ ቢኖሩም እንኳ፣ በዳዊትና በሹማምቱ ላይ ሁሉ ድንጋይ ይወረውርባቸው ነበር። 7ሳሚም እንዲህ ብሎ ይራገም ነበር፤ “ውጣ! ከዚህ ውጣ! አንተ የደም ሰው፤ አንተ ክፉ ሰው፤ 8መንግሥቱን የወሰድህበትን የሳኦልን ቤተ ሰው ደም ሁሉ እግዚአብሔር ወደ አንተው እየመለሰው ነው። እግዚአብሔር መንግሥትህን ለልጅህ ለአቤሴሎም አሳልፎ ሰጥቶታል፤ አንተ የደም ሰው ስለ ሆንህ እነሆ፣ መከራ መጥቶብሃል።”
9ከዚያም የጽሩያ ልጅ አቢሳ ንጉሡን፣ “ይህ የሞተ ውሻ፣ ንጉሥ ጌታዬን እንዴት ይራገማል? ልሻገርና ራሱን ልቍረጠው” አለ።
10ንጉሡ ግን፣ “እናንት የጽሩያ ልጆች እናንተንና እኔን የሚያገናኘን ምን ነገር አለ? እግዚአብሔር፣ ‘ዳዊትን ርገመው’ ብሎት የሚረግመኝ ከሆነ፣ ‘ይህን ለምን አደረግህ’ ብሎ ማን ሊጠይቀው ይችላል?” አለው።
11ከዚያም ዳዊት አቢሳንና ሹማምቱን ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “ከአብራኬ የወጣው ልጄ ሕይወቴን ሊያጠፋት ከፈለገ፣ ይህ ብንያማዊ ቢያደርገው ምን ያስደንቃል? ስለዚህ ተዉት፤ እግዚአብሔር በል ብሎት ነውና ይራገም፤ 12ምናልባትም እግዚአብሔር ሐዘኔን አይቶ በዛሬውም ርግማን ፈንታ በጎ ነገር ያደርግልኝ ይሆናል።”
13ስለዚህም ዳዊትና ሰዎቹ መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ ሳሚም በአንጻሩ ባለው ኰረብታ ጥግ ጥግ እየሄደ ይራገም፣ ድንጋይ ይወረውርበትና ዐፈር ይበትንበት ነበር። 14ንጉሡና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሁሉ ለመሄድ ወዳሰቡበት ስፍራ ደረሱ፤ በጣም ደክሟቸው ስለ ነበር በዚያ ዐረፉ።
የኩሲና የአኪጦፌል ምክር
15በዚህን ጊዜ አቤሴሎምና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ አኪጦፌልም አብሮት ነበር። 16የዳዊት ወዳጅ አርካዊው ኩሲም ወደ አቤሴሎም መጥቶ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ፤ ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ” አለው።
17አቤሴሎምም፣ ኩሲን፣ “ለወዳጅህ ያለህ ታማኝነት እስከዚህ ድረስ ነው? ለምን ከወዳጅህ ጋር አልሄድህም?” ሲል ጠየቀው።
18ኩሲም፣ አቤሴሎምን እንዲህ አለው፤ “ይህንስ አላዳርገውም! እኔ በእግዚአብሔር፣ በዚህ ሕዝብና በእስራኤል ሰዎች ሁሉ ለተመረጠው ለእርሱ እሆናለሁ፤ አብሬውም እኖራለሁ፤ 19እንግዲህ ልጁን ካላገለገልሁ ማንን ላገለግል ነው? አባትህን እንዳገለገልሁ ሁሉ፤ አንተንም አገለግላለሁ።”
20አቤሴሎምም አኪጦፌልን፤ “እስቲ ምክር አምጣ፤ ምን እናድርግ?” አለው።
21አኪጦፌልም መልሶ፣ “ቤተ መንግሥቱን እንዲጠብቁ አባትህ ከተዋቸው ቁባቶቹ ጋር ግባና ተኛ፤ ከዚያም አንተ፣ አባትህን እጅግ የጠላህ መሆንህን መላው እስራኤል ይሰማና አብሮህ ያለው ሁሉ ክንዱ ይበረታል” አለው። 22ስለዚህ ለአቤሴሎም በሰገነቱ ላይ ድንኳን ተከሉለት፤ እዚያም መላው እስራኤል እያየው ከአባቱ ቁባቶች ጋር ተኛ።
23በዚያም ጊዜ አኪጦፌል የሚሰጠው ምክር ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ መጠየቅ ይቈጠር ነበር፤ ዳዊትም ሆነ አቤሴሎም የአኪጦፌልን ምክር የሚቀበሉት በዚህ ሁኔታ ነበር።
Currently Selected:
2 ሳሙኤል 16: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.