2 ነገሥት 20
20
የሕዝቅያስ መታመም
20፥1-11 ተጓ ምብ – 2ዜና 32፥24-26፤ ኢሳ 38፥1-8
1ሕዝቅያስ በጠና ታምሞ፤ ሊሞት ተቃርቦ ነበር። የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስም ወደ እርሱ መጥቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ከሕመምህ አትድንም፤ ትሞታለህና ቤትህን አስተካክል’ ” አለው።
2ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳ አዙሮ፣ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ 3“እግዚአብሔር ሆይ፤ በፊትህ በታማኝነትና በፍጹም ልብ እንደ ሄድሁ፣ ደስ የሚያሰኝህንም እንዳደረግሁ ዐስብ፤” ሕዝቅያስም አምርሮ አለቀሰ።
4ኢሳይያስ የመካከለኛውን አደባባይ ዐልፎ ከመሄዱ በፊት የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እርሱ መጣ፤ 5“ተመለስና የሕዝቤን አለቃ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው፤ ‘የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፤ እፈውስሃለሁ። ከዛሬ ሦስት ቀን በኋላ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ትወጣለህ፤ 6በዕድሜህም ላይ ዐሥራ ዐምስት ዓመት እጨምርልሃለሁ፤ አንተንና ይህችን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፤ ስለ እኔ ስለ ራሴና ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ስል ይህችን ከተማ እከላከልላታለሁ።’ ”
7ከዚያም ኢሳይያስ፣ “ትኵስ የበለስ ጥፍጥፍ አዘጋጁ” አላቸው፤ እነርሱም አዘጋጅተው ዕባጩ ላይ አደረጉለት፤ ተፈወሰም።
8ሕዝቅያስም፣ “እግዚአብሔር እኔን ስለ መፈወሱ፣ ከሦስት ቀን በኋላም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ስለ መውጣቴ ምልክቱ ምንድን ነው?” ሲል ኢሳይያስን ጠየቀው።
9ኢሳይያስም፣ “እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም ምልክቱ ይህ ነው፤ ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ፊት ይቅደምን? ወይስ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ ይመለስ?” ሲል ጠየቀው።
10ሕዝቅያስም መልሶ፣ “ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ፊት መሄዱ ቀላል ነገር ነው፤ ይልቁን ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ ይመለስ” አለ።
11ከዚያም ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ እግዚአብሔርም አካዝ በሠራው ደረጃ ላይ የወረደውን ጥላ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላው እንዲመለስ አደረገ።
ከባቢሎን የመጡ መልእክተኞች
20፥12-19 ተጓ ምብ – ኢሳ 39፥1-8
20፥20-21 ተጓ ምብ – 2ዜና 32፥32-33
12በዚያ ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ የባልዳን ልጅ መሮዳክ ባልዳን የሕዝቅያስን መታመም ሰምቶ ስለ ነበር፣ ደብዳቤና ገጸ በረከት ለሕዝቅያስ ላከለት። 13ሕዝቅያስም መልክተኞቹን ተቀብሎ በዕቃ ቤቱ ያለውን ሁሉ ብሩን፣ ወርቁን ቅመማ ቅመሙንና ከፍ ያለ ዋጋ ያለውን ዘይት የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤቱንና በቀረውም ግምጃ ቤት ያለውን በሙሉ አሳያቸው። በቤተ መንግሥቱም ሆነ በመላው ግዛቱ ሕዝቅያስ ሳያሳያቸው የቀረ ምንም ነገር አልነበረም።
14ከዚያም ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ንጉሡ ሕዝቅያስ መጥቶ፣ “እነዚያ ሰዎች ምን አሉህ? ወደ አንተ ዘንድ የመጡትስ ከየት ነው?” አለው።
ሕዝቅያስም መልሶ፣ “የመጡት ከሩቅ አገር ከባቢሎን ነው” አለው።
15ነቢዩም፣ “በቤተ መንግሥትህ ምን ምን አዩ?” ሲል ጠየቀው።
ሕዝቅያስም፣ “በቤተ መንግሥቴ ያለውን ሁሉ አይተዋል፤ በግምጃ ቤቶቼ ሳላሳያቸው የቀረ ምንም ነገር የለም” አለ።
16ከዚያም ኢሳይያስ ሕዝቅያስን እንዲህ አለው፤ “የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ 17በቤተ መንግሥትህ ያለው ሁሉ አባቶችህም እስከ ዛሬ ድረስ ያከማቹት በሙሉ ወደ ባቢሎን የሚወሰድበት ጊዜ በርግጥ ይመጣል፤ አንዳች የሚቀር ነገር የለም ይላል እግዚአብሔር። 18የሥጋህ ቍራጭ የዐጥንትህ ፍላጭ ከሚሆኑት፣ ከምትወልዳቸው ልጆችህ አንዳንዶቹ በምርኮ ይወሰዳሉ፤ በባቢሎንም ቤተ መንግሥት ጃንደረቦች ይሆናሉ።”
19ሕዝቅያስም ኢሳይያስን፣ “የተናገርኸው የእግዚአብሔር ቃል መልካም ነው” ሲል መለሰ፤ “እኔ እስካለሁ ድረስ ሰላምና ጸጥታ ከተገኘ ምን ይገድደኛል?” ብሎ ዐስቦ ነበርና።
20በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወኑ ሌሎች ተግባራትና፣ ጀግንነቱ ሁሉ ኵሬውንና ውሃውን ወደ ከተማዪቱ ያመጣበትን የመሬት ለመሬት ቦይ እንዴት አድርጎ እንደ ሠራው በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 21ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ ልጁ ምናሴም በእግሩ ተተካ።
Currently Selected:
2 ነገሥት 20: NASV
Highlight
Share
Copy
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fen.png&w=128&q=75)
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.