1 ሳሙኤል 26
26
ዳዊት ለሁለተኛ ጊዜ ሳኦልን ከመግደል ታቀበ
1የዚፍ ሰዎች ሳኦል ወዳለበት ወደ ጊብዓ መጥተው፣ “እነሆ፤ ዳዊት በየሴሞን ትይዩ በሚገኘው በኤኬላ ኰረብታ ተደብቋል” ብለው ነገሩት።
2ስለዚህ ሳኦል ተነሣ፤ ከእስራኤል የተመረጡትን ሦስት ሺሕ ሰዎችን ይዞ፣ ዳዊትን ፍለጋ ወደ ዚፍ ምድረ በዳ ወረደ። 3ሳኦልም በየሴሞን ትይዩ በሚገኘው በኤኬላ ኰረብታ ላይ በመንገድ ዳር ሰፈረ፤ ዳዊት ግን በምድረ በዳ ነበር። ዳዊትም ሳኦል እዚያ ድረስ እንደ ተከተለው ባወቀ ጊዜ፣ 4ሰላዮች ልኮ በትክክል ሳኦል መምጣቱን አረጋገጠ።
5ዳዊትም ተነሥቶ ሳኦል ወደ ሰፈረበት ቦታ ሄደ፤ ሳኦልና የሰራዊቱ አለቃ፣ የኔር ልጅ አበኔር የተኙበትን ስፍራ አየ። ሳኦል በሰፈሩ መካከል ተኝቶ ሳለ፣ ሰራዊቱ በዙሪያው ሰፍሮ ነበር።
6ዳዊትም ኬጢያዊውን አቢሜሌክንና የጽሩያን ልጅ የኢዮአብን ወንድም አቢሳን፣ “ወደ ሳኦል ሰፈር አብሮኝ የሚወርድ ማነው?” ሲል ጠየቃቸው።
አቢሳም፣ “እኔ አብሬህ እወርዳለሁ” አለ።
7ስለዚህ ዳዊትና አቢሳ በሌሊት ሰራዊቱ ወዳለበት ሄዱ። እነሆ፤ ሳኦል በሰፈሩ ውስጥ ተኝቶ ጦሩም ራስጌው አጠገብ በመሬት ላይ ተተክሎ ነበር፤ አበኔርና ወታደሮቹም በዙሪያው ተኝተው ነበር።
8አቢሳም ዳዊትን፣ “ዛሬ እግዚአብሔር ጠላትህን በእጅህ ላይ ጥሎታል፤ አሁንም እኔ አንድ ጊዜ በጦር ወግቼ ከመሬት ጋር ላጣብቀው፤ መድገምም አያስፈልገኝም” አለው።
9ዳዊት ግን አቢሳን እንዲህ አለው፤ “አትግደለው! እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጁን አንሥቶ ከበደል ነጻ የሚሆን ማን ነው? 10ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር ራሱ ይቀሥፈዋል፤ ወይም ቀኑ ደርሶ ይሞታል፤ ወይም በጦርነት ይሞታል። 11እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን ከማንሣት እግዚአብሔር ይጠብቀኝ! ነገር ግን በራስጌው አጠገብ ያለውን ጦርና የውሃ መያዣውን ያዝና እንሂድ።”
12ስለዚህ ዳዊት በሳኦል ራስጌ አጠገብ የነበረውን ጦርና የውሃውን መያዣ ወሰደ፤ ከዚያም ሄዱ፤ ይህን ያየም ሆነ ያወቀ ወይም የነቃ ማንም አልነበረም። ከእግዚአብሔር ዘንድ ከባድ እንቅልፍ ስለ ወደቀባቸው ሁሉም ተኝተው ነበርና።
13ከዚህ በኋላ ዳዊት ወደ ማዶ ተሻግሮ በኰረብታው ጫፍ ላይ ራቅ ብሎ ቆመ፤ በመካከላቸውም ሰፊ ርቀት ነበር። 14ዳዊት ሰራዊቱንና የኔርን ልጅ አብኔርን፣ “አበኔር ሆይ፣ አትመልስልኝምን?” ሲል ተጣራ።
አበኔርም፣ “በንጉሡ ላይ የምትጮኽ አንተ ማነህ?” በማለት መለሰ።
15ዳዊትም እንዲህ አለ፤ “አንተ ብርቱ ሰው ነህ? በእስራኤልስ ዘንድ አንተን የሚመስል ማን ነው? እነሆ፤ አንድ ሰው ንጉሡን ጌታህን ለመግደል መጥቶ ነበር፤ ታዲያ አንተ ንጉሥ ጌታህን ያልጠበቅኸው ስለ ምንድን ነው? 16ያደረግኸው መልካም አይደለም፤ ሕያው እግዚአብሔርን! አንተና ሰዎችህ ሞት ይገባችኋል፤ እግዚአብሔር የቀባውን ጌታችሁን አልጠበቃችሁምና። እስቲ ተመልከት፤ በራስጌው የነበሩት የንጉሡ ጦርና የውሃ መያዣ የት አሉ?”
17ሳኦል የዳዊትን ድምፅ ለይቶ ስላወቀ፣ “ልጄ ዳዊት ሆይ፤ ይህ ድምፅህ ነውን?” አለው። ዳዊትም፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ አዎን ድምፄ ነው” ሲል መለሰ፤ 18በመቀጠልም፣ “ጌታዬ አገልጋዩን የሚያሳድደው ስለ ምንድን ነው? ምን አደረግሁ? ምን በደልስ ፈጸምሁ? 19አሁንም ንጉሥ ጌታዬ የባሪያውን ቃል ያድምጥ፤ እግዚአብሔር በእኔ ላይ አነሣሥቶህ እንደ ሆነ፣ ቍርባን ይቀበል፤ ነገር ግን ይህን ያደረጉት ሰዎች ከሆኑ፣ በእግዚአብሔር ፊት የተረገሙ ይሁኑ፤ ‘ሂድ ሌሎችን አማልክት አምልክ’ ብለው በእግዚአብሔር ርስት ድርሻ እንዳይኖረኝ ዛሬ አሳድደውኛልና። 20አንድ ሰው በተራራ ላይ ቆቅ እንደሚያድን የእስራኤልም ንጉሥ ቍንጫ ለመፈለግ ስለ ወጣ፣ ደሜ ከእግዚአብሔር ፊት ርቆ በምድር ላይ እንዲፈስ አታድርግ።”
21ሳኦልም፣ “በድያለሁ፤ ልጄ ዳዊት ሆይ፤ ተመለስ፤ ዛሬ ነፍሴ በፊትህ ስለ ከበረች፣ ከእንግዲህ ወዲያ አልጐዳህም፤ በርግጥ የሞኝ ሥራ ሠርቻለሁ፤ እጅግ ሲበዛም ተሳስቻለሁ” አለ።
22ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “የንጉሥ ጦር እነሆ፤ ከወጣቶችህ አንዱ መጥቶ ይውሰዳት። 23እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ጽድቁና እንደ ታማኝነቱ ይክፈለው። እኔ ግን ዛሬ እግዚአብሔር አንተን በእጄ አሳልፎ ሰጥቶኝ ሳለ እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን አላነሣሁም። 24እነሆ፤ ዛሬ ሕይወትህ በፊቴ እንደ ከበረች ሁሉ፣ የእኔም ሕይወት በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረች ትሁን፤ ከመከራም ሁሉ ያድነኝ።”
25ከዚያም ሳኦል ዳዊትን፣ “ልጄ ዳዊት ሆይ፤ የተባረክህ ሁን፤ ታላቅ ነገር ታደርጋለህ፤ በርግጥም ይከናወንልሃል” አለው።
ስለዚህም ዳዊት ወደሚሄድበት ሄደ፤ ሳኦልም ወደ ቤቱ ተመለሰ።
Currently Selected:
1 ሳሙኤል 26: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.