1 ሳሙኤል 24
24
ዳዊት ሳኦልን ከመግደል ታቀበ
1ሳኦል ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ከተመለሰ በኋላ፣ “እነሆ፤ ዳዊት በዓይንጋዲ ምድረ በዳ አለ” ብለው ነገሩት። 2ስለዚህ ሳኦል ከመላው እስራኤል የተመረጡ ሦስት ሺሕ ሰዎችን ይዞ ዳዊትንና ሰዎቹን ለመፈለግ “የሜዳ ፍየሎች ዐለት” ወደ ተባለው ቦታ አቅራቢያ ሄደ።
3ሳኦልም በመንገድ ዳር ወዳለው ወደ አንድ የበጎች ማደሪያ በደረሰ ጊዜ፣ ዋሻ አግኝቶ ወገቡን ሊሞክር ወደዚያ ገባ። ዳዊትና ሰዎቹም ከዋሻው በውስጠኛው ቦታ ተቀምጠው ነበር። 4የዳዊት ሰዎችም ዳዊትን፣ “እግዚአብሔር፣ ‘የወደድኸውን ታደርግበት ዘንድ ጠላትህን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ’ ብሎ ለአንተ የተናገረው ቀን ዛሬ ነው” አሉት። ዳዊትም በልቡ እየተሳበ ሄዶ የሳኦልን ልብስ ጫፍ ማንም ሳያውቅ ቈርጦ ወሰደ።
5ዳዊት የሳኦልን ልብስ ጫፍ በመቍረጡ ልቡ በሐዘን ተመታ። 6ለሰዎቹም፣ “እግዚአብሔር በቀባው በጌታዬ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር ከማድረግና እግዚአብሔር የቀባው ስለ ሆነም እጄን በእርሱ ላይ ከማንሣት እግዚአብሔር ይጠብቀኝ” አላቸው። 7ዳዊት ሰዎቹን በዚህ ቃል ገሠጻቸው፤ በሳኦል ላይ አደጋ እንዲያደርሱበትም አልፈቀደላቸውም። ሳኦልም ከዋሻው ወጥቶ ሄደ።
8ከዚያም ዳዊት ከዋሻው ወጥቶ ሳኦልን፣ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ!” ብሎ ጠራው። ሳኦልም ወደ ኋላው ዞር ባለ ጊዜ፣ ዳዊት ወደ መሬት ጐንበስ ብሎ እጅ ሲነሣው ተመለከተ፤ 9ዳዊትም ሳኦልን እንዲህ አለው፤ “ሰዎች፣ ‘እነሆ፤ ዳዊት ክፉ ነገር ሊያደርግብህ ይፈልጋል’ ሲሉ ለምን ትቀበላቸዋለህ? 10በዛሬው ዕለት በዋሻው ውስጥ እግዚአብሔር አንተን እንዴት አድርጎ በእጄ ላይ እንደ ጣለህ እነሆ፤ በገዛ ዐይንህ አይተሃል፤ አንዳንዶች እንድገድልህ ገፋፍተውኝ ነበር፤ እኔ ግን፣ ‘እግዚአብሔር በቀባው በጌታዬ ላይ እጄን አላነሣም’ በማለት ራራሁልህ። 11አባቴ ሆይ፤ የልብስህ ቍራጭ ይኸው በእጄ ላይ ተመልከት! የልብስህን ጫፍ ቈረጥሁ እንጂ አንተን አልገደልሁህም። አሁንም ክፋት ወይም ዐመፅ አለመፈጸሜን ዕወቅልኝ፤ ተረዳልኝም፤ እኔ ክፉ አልሠራሁብህም፤ አንተ ግን ሕይወቴን ለማጥፋት እያሳደድኸኝ ነው። 12እግዚአብሔር በአንተና በእኔ መካከል ይፍረድ። ክፉ ስላደረግህብኝ እግዚአብሔር ይበቀልህ እንጂ፣ እጄስ በአንተ ላይ አትሆንም፤ 13በጥንት አባባል፣ ‘ከክፉ አድራጊዎች ክፉ ድርጊት ይወጣል’ እንደ ተባለ፤ አሁንም እጄ በአንተ ላይ አትሆንም።
14“የእስራኤል ንጉሥ የወጣው በማን ላይ ነው? አንተስ የምታሳድደው ማንን ነው? የሞተ ውሻን? ወይስ ቍንጫ? 15አሁንም እግዚአብሔር ዳኛ ሆኖ በመካከላችን ይፍረድ፤ ጕዳዬን ተመልክቶ እርሱው ይሟገትልኝ፤ እኔንም ከእጅህ ነጻ በማውጣት እውነተኛ መሆኔን ይግለጠው።”
16ዳዊት ይህን ተናግሮ ሲያበቃ ሳኦል፣ “ልጄ ዳዊት ሆይ፤ ይህ የአንተ ድምፅ ነውን?” ሲል ጠየቀው፤ ጮኾም አለቀሰ። 17እንዲህም አለ፤ “ክፉ ሳደርግብህ፣ በጎ መልሰህልኛልና፣ አንተ ከእኔ ይልቅ ጻድቅ ነህ። 18ያደረግህልኝን በጎ ነገር ይኸው ነግረኸኛል፤ እግዚአብሔር እኔን በእጅህ ጥሎኝ ነበር፤ አንተ ግን አልገደልኸኝም። 19ለመሆኑ ጠላቱን አግኝቶ ጕዳት ሳያደርስበት የሚለቀው ማን ነው? ዛሬ ስላደረግህልኝ ቸርነት እግዚአብሔር ይመልስልህ። 20እነሆ፤ አንተ በርግጥ እንደምትነግሥና የእስራኤል መንግሥት በእጅህ እንደምትጸና ዐውቃለሁ። 21ዘሮቼን እንዳታጠፋ ስሜንም ከአባቴ ቤት እንዳት ደመስስ አሁን በእግዚአብሔር ማልልኝ።”
22ዳዊትም ለሳኦል ማለለት፤ ከዚያም ሳኦል ወደ ቤቱ ተመለሰ። ዳዊትና ሰዎቹ ግን ወደ ዐምባው ወጡ።
Currently Selected:
1 ሳሙኤል 24: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.