1 ነገሥት 8
8
ታቦቱ ወደ ቤተ መቅደሱ ገባ
8፥1-21 ተጓ ምብ – 2ዜና 5፥2–6፥11
1ከዚያም ንጉሥ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን ለማምጣት፣ የእስራኤልን ሽማግሌዎች፣ የእስራኤልን ነገድ አለቆችና የእስራኤልን ጐሣዎች ሹማምት ሁሉ እርሱ ወዳለበት ወደ ኢየሩሳሌም ጠራቸው። 2በዓሉ በሚከበርበት ኤታኒም በተባለው በሰባተኛው ወር፣ የእስራኤል ወንዶች ሁሉ ንጉሥ ሰሎሞን ወዳለበት ተሰበሰቡ።
3የእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ በመጡ ጊዜም ካህናቱ ታቦቱን አነሡ፤ 4የእግዚአብሔርን ታቦት፣ የመገናኛውን ድንኳንና በውስጡ ያሉትን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ አመጡ፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም ይህን ሁሉ ተሸከሙ። 5ንጉሥ ሰሎሞንና አብሮት በዚያ የተሰበሰበው መላው የእስራኤል ጉባኤም በታቦቱ ፊት በመሆን ስፍር ቍጥር የሌለው በግና በሬ ሠዋ።
6ከዚያም ካህናቱ የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት አምጥተው በቤተ መቅደሱ ውስጥ ወዳለው ማደሪያው፣ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ በማስገባት ከኪሩቤል ክንፍ በታች አኖሩት። 7ኪሩቤልም ታቦቱ ባለበት ቦታ ላይ ክንፋቸውን ዘርግተው፣ ታቦቱንና መሎጊያዎቹን ጋረዱ። 8መሎጊያዎቹ ከመርዘማቸው የተነሣ ጫፎቻቸው ከቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት ካለው ከመቅደሱ ሆኖ ይታዩ ነበር፤ ከመቅደሱ ወዲያ ላለ ሰው ግን አይታዩም ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ እዚያው ይገኛሉ። 9የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር በወጡ ጊዜ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ኪዳን በገባበት በኮሬብ፣ ሙሴ በታቦቱ ውስጥ ካስቀመጣቸው ሁለት የድንጋይ ጽላቶች በቀር በታቦቱ ውስጥ ምንም አልነበረም።
10ካህናቱ ከቤተ መቅደሱ በወጡ ጊዜ፣ ደመና የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሞላው። 11የእግዚአብሔር ክብር ቤተ መቅደሱን ሞልቶት ስለ ነበር፣ ካህናቱ በደመናው ምክንያት አገልግሎታቸውን ማከናወን አልቻሉም ነበር።
12ከዚያም ሰሎሞን እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ጥቅጥቅ ባለ ደመና ውስጥ እንደሚኖር ተናግሯል፤ 13እነሆ፣ እኔም ለዘላለም የምትኖርበትን ታላቅ ቤተ መቅደስ ሠርቼልሃለሁ።”
14መላው የእስራኤል ጉባኤ በዚያ ቆሞ ሳለ፣ ንጉሡ ፊቱን ወደ እነርሱ መልሶ ጉባኤውን ባረከ። 15ከዚያም እንዲህ አለ፤
“ለአባቴ ለዳዊት በገዛ አፉ ተናግሮ የሰጠውን ተስፋ፣ እርሱ ራሱ በእጁ የፈጸመ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ እርሱም እንዲህ ብሎ ነበርና፤ 16‘ሕዝቤን እስራኤልን ከግብፅ ምድር ካወጣሁበት ዕለት አንሥቶ፣ ስሜ በዚያ እንዲጠራና ቤተ መቅደስ እንዲሠራበት ከመላው የእስራኤል ነገድ አንድም ከተማ አልመረጥሁም፤ ሕዝቤን እስራኤልን እንዲመራ ግን ዳዊትን መረጥሁት።’
17“አባቴ ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልቡ ዐስቦ ነበር፤ 18እግዚአብሔር ግን አባቴን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ ‘ለስሜ ቤተ መቅደስ ለመሥራት አስበሃልና፣ ይህን በልብህ ማሰብህ መልካም ነው፤ 19ይሁን እንጂ ቤተ መቅደሱን የምትሠራው አንተ ሳትሆን፣ ከአንተ የሚወለደው ልጅህ ነው፤ አዎን ለስሜ ቤተ መቅደስ የሚሠራው እርሱ ነው።’
20“እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ ፈጽሟል፤ እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ መሠረት፣ በአባቴ በዳዊት እግር ተተክቻለሁ፤ በእስራኤል ዙፋን ተቀምጫለሁ፤ እንዲሁም ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ ሠርቻለሁ። 21ከግብፅ ባወጣቸው ጊዜ ከአባቶቻችን ጋር የገባው የእግዚአብሔር ኪዳን በውስጡ ላለበት ታቦት መኖሪያ ስፍራ በዚያ አዘጋጅቻለሁ።”
ሰሎሞን በምረቃው ላይ ያቀረበው ጸሎት
8፥22-53 ተጓ ምብ – 2ዜና 6፥12-40
22ከዚያም ሰሎሞን መላው የእስራኤል ጉባኤ ባለበት በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ቆመ፤ እጆቹንም ወደ ሰማይ ዘርግቶ፣ 23እንዲህ አለ፤
“የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በፊትህ በፍጹም ልባቸው ጸንተው ለሚኖሩ አገልጋዮችህ ኪዳንህን የምትጠብቅ፣ ጽኑ ፍቅርህን የምትገልጥ አንተ ነህ፤ በላይ በሰማይ፣ በታችም በምድር እንደ አንተ ያለ አምላክ ከቶ የለም፤ 24ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ ጠብቀሃል፤ በአፍህ ተናገርህ፤ ይህንኑም በዛሬው ዕለት በእጅህ ፈጸምኸው።
25“አሁንም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ ለአባቴ ለባሪያህ ለዳዊት፣ ‘አንተ እንደ አደረግኸው ሁሉ፣ ልጆችህ በፊቴ ለመመላለስ በሚያደርጉት ሁሉ ይጠንቀቁ ብቻ እንጂ በእስራኤል ዙፋን ላይ በፊቴ የሚቀመጥ ሰው አታጣም’ ስትል የሰጠኸውን ተስፋ ፈጽምለት። 26አሁንም የእስራኤል አምላክ ሆይ፤ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ይፈጸም።
27“ነገር ግን አምላክ በርግጥ በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፤ ሰማይ፣ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ እንኳ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምኑ ሊበቃ! 28አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህም ሆኖ የባሪያህን ጸሎትና ልመና ስማ፤ በዛሬው ዕለት ባሪያህ በፊትህ የሚያቀርበውን ጩኸትና ልመና አድምጥ። 29ባሪያህ ወደዚህ ቦታ የሚያቀርበውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ፣ ‘ስሜ በዚያ ይሆናል’ ወደ አልኸው በዚህ ስፍራ ወዳለው ቤተ መቅደስ ዐይኖችህ ሌትና ቀን የተከፈቱ ይሁኑ። 30ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ ጸሎት በሚያቀርቡበት ጊዜ፣ ልመናቸውን ተቀበል፤ መኖሪያህ በሆነው በሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል።
31“አንድ ሰው ባልንጀራውን በድሎ መማል ኖሮበት ቢመጣና በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ በመሠዊያህ ፊት ቢምል፣ 32ይህን በሰማይ ሆነህ ስማ፤ አድርግም፤ በባሪያዎችህ መካከል ፍረድ፤ ለበደለኛው ስለ አድራጎቱ የእጁን ክፈል፤ ከበደል ነጻ ለሆነውም ንጽሕናውን ይፋ በማድረግ ይህንኑ አረጋግጥለት።
33“ሕዝብህ እስራኤል አንተን ከመበደላቸው የተነሣ፣ በጠላቶቻቸው ድል በሚሆኑበት ጊዜ፣ ወደ አንተም ተመልሰው ስምህን ቢጠሩ፣ በዚህም ቤተ መቅደስ ወደ አንተ ቢጸልዩና ልመናቸውን ቢያቀርቡ፣ 34በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የሕዝብህ የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸውም ምድር መልሰህ አግባቸው።
35“ሕዝቡም አንተን ከመበደላቸው የተነሣ፣ ሰማዩ ተዘግቶ ዝናብ ሳይዘንብ ቢቀር፣ ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩና ስምህን ቢጠሩ፣ ስላስጨነቅሃቸውም ከበደላቸው ቢመለሱ፣ 36በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የባሪያዎችህን የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ የሚሄዱበትን ቀናውን መንገድ አስተምራቸው፤ ርስት አድርገህ ለሕዝብህ ለሰጠሃትም ምድር ዝናብ አውርድ።
37“በምድሪቱ ላይ ራብ ወይም ቸነፈር በሚመጣበት፣ ዋግ ወይም አረማሞ በሚከሠትበት፣ አንበጣ ወይም ኵብኵባ በሚወርድበት ወይም በምድራቸው ውስጥ ባሉት ከተሞቻቸው ጠላት ቢከብባቸው፣ እንዲሁም ማንኛውም ዐይነት ጥፋት ወይም በሽታ በሚመጣባቸው ጊዜ፣ 38ከሕዝብህ ከእስራኤል ማንኛውም ሰው የልቡን ጭንቀት ዐውቆ እጆቹን ወደዚህ ቤት በመዘርጋት ጸሎትና ልመና በሚያቀርብበት ጊዜ ሁሉ፣ 39በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ይቅር በል፤ አድርግም። አንተ ብቻ የሰውን ሁሉ ልብ የምታውቅ ስለ ሆንህ ልቡን ለምታውቀው ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው ሁሉ ክፈለው፤ 40ይህም እነርሱ ለአባቶቻችን በሰጠሃቸው ምድር በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ፣ አንተን እንዲፈሩ ነው።
41“ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ፣ ግን ከስምህ ታላቅነት የተነሣ ከሩቅ የመጣ የባዕድ አገር ሰው ቢኖር፣ 42ሰዎች ከሩቅ የሚመጡት ስለ ታላቁ ስምህ፣ ስለ ጠንካራዪቱ እጅህ፣ ስለ ተዘረጋችው ክንድህ ሰምተው ነውና፤ እንግዳው መጥቶ ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቢጸልይ፣ 43አንተ በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የጠየቀህንም ሁሉ ፈጽምለት፤ ይኸውም የምድር ሕዝቦች ሁሉ ስምህን ዐውቀው፣ ሕዝብህ እስራኤል አንተን እንደሚፈሩት ሁሉ እንዲፈሩህ፣ እኔ የሠራሁትም ይህ ቤት በስምህ መጠራቱን እንዲያውቁ ነው።
44“ሕዝብህ ጠላታቸውን ለመውጋት አንተ ወደምትልካቸው ወደ የትኛውም ቦታ ለጦርነት በሚወጡበት ጊዜ፣ አንተ ወደ መረጥሃት ከተማና እኔ ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው ለእግዚአብሔር ቢጸልዩ፣ 45ጸሎትና ልመናቸውን በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ርዳቸውም።
46“መቼም ኀጢአት የማይሠራ የለምና ሕዝብህ በአንተ ላይ ኀጢአት ቢሠሩ፣ አንተም ተቈጥተህ ሩቅ ወይም ቅርብ ወደ ሆነው ምድሩ ማርኮ ለሚወስደው ጠላት አሳልፈህ ብትሰጣቸው፣ 47ተማርከው በሚኖሩበት አገር ሳሉ ልባቸው ቢመለስ፣ በተማረኩበትም ምድር ሆነው ንስሓ ቢገቡና ‘ኀጢአት ሠርተናል፤ በድለናል፤ ክፉ ድርጊትም ፈጽመናል’ ብለው ቢለምኑህ፣ 48እንዲሁም ማርከው በወሰዷቸው ጠላቶቻቸው ምድር ሳሉ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ወደ አንተ ቢመለሱ፣ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃት ወደዚህች ምድር፣ ወደ መረጥሃትም ወደዚህች ከተማና እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው ቢጸልዩ፣ 49ከማደሪያህ ከሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ ልመናቸውንም ተቀበል፤ ርዳቸውም። 50በአንተ ላይ ስለ ሠሩት ኀጢአት፣ አንተንም ስለ በደሉህ በደል ሁሉ ሕዝብህን ይቅር በል፤ የማረኳቸውም እንዲራሩላቸው አድርግ። 51ከዚያች እንደ ብረት ማቅለጫ እቶን እሳት ከሆነችው፣ ከግብፅ ምድር ያወጣሃቸው ሕዝብህም ርስትህም ናቸውና።
52“አሁንም ዐይኖችህ ለባሪያህና ለሕዝብህ ለእስራኤል ልመና የተከፈቱ ይሁኑ፤ ወደ አንተ በሚጮኹበትም ጊዜ ሁሉ ስማቸው፤ 53አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ፤ አባቶቻችንን ከግብፅ ባወጣህ ጊዜ፣ በባሪያህ በሙሴ አማካይነት እንደ ተናገርኸው ሁሉ፣ ርስትህ ይሆኑ ዘንድ ከምድር ሕዝቦች ሁሉ ለይተሃቸዋልና።”
54ሰሎሞንም ይህን ሁሉ ጸሎትና ልመና ለእግዚአብሔር አቅርቦ ከፈጸመ በኋላ፣ እጆቹን ወደ ሰማይ በመዘርጋት፣ በጕልበቱ ተንበርክኮ ከነበረበት ከእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ተነሣ። 55ከዚያም ቆሞ መላውን የእስራኤልን ጉባኤ ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ ሲል መረቀ፤
56“በሰጠው ተስፋ መሠረት ለሕዝቡ ለእስራኤል ዕረፍትን ለሰጠ እግዚአብሔር ምስጋና ይግባው፤ በባሪያው በሙሴ አማካይነት ከተሰጠው መልካም ተስፋ ሁሉ አንድም ቃል አልቀረምና። 57አምላካችን እግዚአብሔር ከአባቶቻችን ጋር እንደ ነበረ ሁሉ ከእኛም ጋር ይሁን፤ አይተወን፤ አይጣለንም። 58በመንገዱም ሁሉ እንድንሄድ፣ ለአባቶቻችን የሰጣቸውን ትእዛዞች፣ ሥርዐቶችና ደንቦች እንድንጠብቅ ልባችንን ወደ እርሱ ይመልስ። 59በየዕለቱም ባሪያውንና ሕዝቡን እስራኤልን በሚያስፈልጋቸው ሁሉ እንዲረዳቸው፣ ይህች በእግዚአብሔር ፊት ያቀረብኋት የራሴ ልመና በቀንና በሌሊት ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ፊት ትቅረብ። 60ይኸውም የምድር ሕዝቦች ሁሉ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ እንደ ሆነና ከእርሱ በቀር ሌላ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ ነው። 61ስለዚህ እንደ ዛሬው ዕለት ሁሉ፣ በሥርዐቱ እንድትኖሩና ትእዛዙን እንድትጠብቁ ልባችሁ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር የተገዛ ይሁን።”
የቤተ መቅደሱ መመረቅ
8፥62-66 ተጓ ምብ – 2ዜና 7፥1-10
62ከዚያም ንጉሡና ከእርሱ ጋር ያሉት እስራኤል ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት አቀረቡ። 63ሰሎሞንም ሃያ ሁለት ሺሕ በሬ፣ መቶ ሃያ ሺሕ በግና ፍየል የኅብረት መሥዋዕት#8፥63 በዚህና በ64 ላይ በትውፊት፣ የሰላም መሥዋዕት ይባላል። አድርጎ ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ ንጉሡና እስራኤላውያንም ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በዚህ ሁኔታ ቀደሱ።
64በዚያኑ ዕለትም ንጉሡ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት ያለውን የአደባባዩን መካከለኛ ክፍል ቀደሰ፤ በዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት፣ የእህል ቍርባንና የኅብረት መሥዋዕቱን ሥብ አቀረበ፤ ይህን ያደረገውም በእግዚአብሔር ፊት የነበረው የናስ መሠዊያ ከትንሽነቱ የተነሣ የሚቃጠለውን መሥዋዕት የእህሉን ቍርባንና የኅብረት መሥዋዕቱን ስብ መያዝ ባለመቻሉ ነበር።
65በዚያን ጊዜም ሰሎሞን አብረውት ካሉት የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ጋር፣ ማለትም ከሐማት መተላለፊያ እስከ ግብፅ ደረቅ ወንዝ#8፥65 ወይም ከመግቢያው ጀምሮ ተብሎ መተርጐም ይችላል። ካለው ምድር ከተሰበሰበው ታላቅ ጉባኤ ጋር በዓሉን አከበረ። እነርሱም ሰባት ቀን፣ በተጨማሪም ሌላ ሰባት ቀን በድምሩ ዐሥራ አራት ቀን በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት በዓሉን አከበሩ። 66በሚቀጥለው ቀን ሕዝቡን አሰናበተ፤ ሕዝቡም ንጉሡን መረቁ፤ እግዚአብሔር ለባሪያው ለዳዊትና ለሕዝቡ ለእስራኤል ባደረገው በጎ ነገር ሁሉ ከልብ ተደስተው ሐሤት በማድረግ ወደየቤታቸው ተመለሱ።
Currently Selected:
1 ነገሥት 8: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.