YouVersion Logo
Search Icon

1 ነገሥት 11

11
የሰሎሞን ሚስቶች
1ንጉሥ ሰሎሞን ከፈርዖን ልጅ ሌላ ብዙ የባዕድ አገር ሴቶችን ማለትም ሞዓባውያትን፣ አሞናውያትን፣ ኤዶማውያትን፣ ሲዶናውያትን፣ ኬጢያውያትን አፈቀረ። 2እነዚህም እግዚአብሔር እስራኤላውያንን፣ “ልባችሁን ወደ አማልክታቸው በርግጥ ይመልሱታልና ከእነርሱ ጋር መጋባት የለባችሁም” ካላቸው አሕዛብ ወገን ነበሩ፤ ሆኖም ሰሎሞን ከእነዚሁ ጋር ፍቅሩ ጠና። 3እርሱም ከነገሥታት የተወለዱ ሰባት መቶ ሚስቶችና ሦስት መቶ ቁባቶች ነበሩት፤ ሚስቶቹም ልቡ ወደ ሌላ እንዲያዘነብል አደረጉት። 4ሰሎሞን በሸመገለ ጊዜ ሚስቶቹ ልቡን ወደ ሌሎች አማልክት መለሱት፤ የአባቱ የዳዊት ልብ እንደ ተገዛ ሁሉ፣ በፍጹም ልቡ ለአምላኩ ለእግዚአብሔር አልተገዛም። 5ሰሎሞንም የሲዶናውያንን ሴት አምላክ አስታሮትን፣ አስጸያፊውን የአሞናውያንን አምላክ ሚልኮምን ተከተለ። 6ስለዚህ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ፤ እንደ አባቱ እንደ ዳዊትም እግዚአብሔርን እስከ መጨረሻው አልተከተለም።
7ሰሎሞን ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ ባለው ተራራ ላይ ለአስጸያፊው የሞዓብ አምላክ ለካሞሽ እንዲሁም አስጸያፊ ለሆነው ለአሞናውያን አምላክ ለሞሎክ ማምለኪያ ኰረብታ ሠራ። 8ለአማልክቶቻቸው ዕጣን ለሚያጥኑና መሥዋዕት ለሚያቀርቡ ለሌሎቹ ሚስቶቹም ሁሉ በዚሁ ዐይነት ሠራላቸው።
9ሰሎሞን ሁለት ጊዜ ከተገለጠለት ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ልቡ ስለ ሸፈተ፣ እግዚአብሔር ተቈጣው። 10ምንም እንኳ ሌሎች አማልክትን እንዳይከተል ሰሎሞንን ቢከለክለውም፣ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልጠበቀም፤ 11ስለዚህ እግዚአብሔር ሰሎሞንን እንዲህ አለው፤ “ይህን በማድረግህ ያዘዝሁህን ኪዳኔንና ሥርዐቴንም ባለመጠበቅህ፣ መንግሥትህን ከአንተ ወስጄ ከአገልጋዮችህ ለአንዱ እሰጠዋለሁ፤ 12ይህን ግን ስለ አባትህ ስለ ዳዊት ስል በዘመንህ አላደርገውም፤ መንግሥትህን የምቀድዳት ከልጅህ እጅ ነው። 13ይህም ሆኖ መንግሥቱን በሙሉ አልነጥቀውም፤ ነገር ግን ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊትና ስለ መረጥኋት ስለ ኢየሩሳሌም ስል ለልጅህ አንድ ነገድ እሰጠዋለሁ።”
የሰሎሞን ጠላቶች
14 እግዚአብሔር ከኤዶም ንጉሣዊ ቤተ ሰብ ኤዶማዊውን ሃዳድን በሰሎሞን ላይ አስነሣው። 15ከዚያ በፊት ዳዊት ከኤዶም ጋር በተዋጋ ጊዜ፣ የሞቱትን ለመቅበር መጥቶ የነበረው የሰራዊቱ አዛዥ ኢዮአብ የኤዶምን ሰዎች ሁሉ ፈጅቶ ነበር። 16ኢዮአብና እስራኤላውያን ሁሉ፣ በኤዶም ያሉትን ወንዶች በሙሉ እስኪያጠፉ ድረስ፣ እዚያው ስድስት ወር ቈይተው ነበርና። 17ሃዳድ ግን ገና በልጅነቱ አባቱን ካገለገሉ ጥቂት ኤዶማውያን ጋር ወደ ግብፅ ሸሸ፤ 18እነርሱም ከምድያም ተነሥተው ወደ ፋራን ሄዱ፤ ከፋራንም ሰዎች ይዘው ወደ ግብፅ በመምጣት፣ ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ፈርዖን ገቡ። ንጉሡም ለሃዳድ ቤትና መሬት ሰጠው፤ ቀለብም አዘዘለት።
19ፈርዖንም ሃዳድን እጅግ ወደደው፤ ስለዚህም ከሚስቱ ከንግሥት ጣፍኔስ እኅት ጋር አጋባው። 20የጣፍኔስም እኅት ጌንባት የተባለውን ልጅ ወለደችለት፤ ጣፍኔስ በፈርዖን ቤት አሳደገችው፤ ጌንባትም ከፈርዖን ልጆች ጋር አደገ።
21ሃዳድ በግብፅ ሳለ ዳዊት ከአባቶቹ ጋር ማንቀላፋቱን፣ የሰራዊቱ አዛዥ ኢዮአብም መሞቱን ሰማ። ሃዳድም ፈርዖንን፣ “ወደ አገሬ እንድመለስ አሰናብተኝ” አለው።
22ፈርዖንም፣ “እዚህ ምን ጐደለብህና ነው ወደ አገርህ ለመግባት የፈለግኸው?” ሲል ጠየቀው።
ሃዳድም፣ “ምንም የጐደለብኝ የለም፣ ብቻ እንድሄድ ፍቀድልኝ” አለ።
23እግዚአብሔርም ከጌታው ከሱባ ንጉሥ ኰብልሎ የነበረውን የኤልያዳን ልጅ ሬዞንን ሌላ ጠላት አድርጎ በሰሎሞን ላይ አስነሣው፤ 24ዳዊት የሱባን ኀይል በደመሰሰ#11፥24 ዕብራይስጡ በደመሰሳቸው ጊዜ ይላል። ጊዜ፣ ሬዞን ሰዎቹን በዙሪያው አሰባስቦ የወንበዴ አለቃ ሆነ፤ ሰዎቹም ወደ ደማስቆ ሄደው ተቀመጡ፤ በዚያም አነገሡት። 25ሃዳድ ካስከተለበት ችግር ሌላ ሬዞን በሰሎሞን ዘመን ሁሉ ሌላው የእስራኤል ተቃዋሚ ሆነ፤ ሬዞን ሶርያን ገዛ፤ እስራኤልንም ይጠላ ነበር።
ኢዮርብዓም በሰሎሞን ላይ ዐመፀ
26እንዲሁም ከሰሎሞን ሹማምት አንዱ የሆነው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በንጉሡ ላይ ዐመፀ፤ እርሱም ከጸሬዳ የመጣ ኤፍሬማዊ ሲሆን፣ እናቱ ጽሩዓ የተባለች መበለት ነበረች።
27በንጉሡ ላይ ያመፀበትም ምክንያት እንዲህ ነው፤ ሰሎሞን ድጋፍ የሚሆኑ እርከኖች በመሥራት የአባቱን የዳዊትን ከተማ ቅጥር ይጠግን ነበር። 28ኢዮርብዓም ከፍተኛ ችሎታ ያለው ሰው ነበር፤ ሰሎሞንም ወጣቱ ሥራውን እንዴት በሚገባ እንደሚያከናውን ባየ ጊዜ፣ በዮሴፍ ነገድ ለሚሠራው የጕልበት ሥራ ሁሉ ኀላፊ አደረገው።
29በዚያ ጊዜም ኢዮርብዓም ከኢየሩሳሌም ሲወጣ፣ የሴሎው ነቢይ አኪያ በመንገድ ላይ ተገናኘው፤ አኪያም አዲስ መጐናጸፊያ ለብሶ ነበር፤ ሁለቱ ብቻቸውን ሳሉ፣ 30አኪያ የለበሰውን አዲስ መጐናጸፊያ ይዞ ዐሥራ ሁለት ቦታ ቀደደው። 31ከዚያም ኢዮርብዓምን እንዲህ አለው፤ “ዐሥሩን ቍራጭ ለራስህ ውሰድ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘እነሆ፤ መንግሥቱን ከሰሎሞን እጅ እቀድዳለሁ፤ ዐሥሩን ነገድ ለአንተ እሰጣለሁ፤ 32ነገር ግን ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊትና ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ስለ መረጥኋት ስለ ኢየሩሳሌም ስል አንድ ነገድ ይቀርለታል፤ 33ይህን የማደርገውም እኔን ትተው#11፥33 የዕብራይስጡ፣ የሰብዓ ሊቃናት፣ የቩልጌትና የሱርስት ትርጕሞች፣ እኔን ስለ ተወ ይላሉ። የሲዶናውያንን አምላክ አስታሮትን፣ የሞዓብን አምላክ ካሞሽን፣ የአሞናውያንን አምላክ ሚልኮምን ስላመለኩ እንዲሁም አባቱ ዳዊት እንዳደረገው በመንገዴ ስላልሄዱ፣ በፊቴ ትክክለኛውን ነገር ስላላደረጉ፣ ሥርዐቴንና ሕጌን ስላልጠበቁ ነው።
34“ ‘ይሁን እንጂ መንግሥቱን በሙሉ ከእጁ አልወስድበትም፤ ስለ መረጥሁት፣ ትእዛዜንና ሥርዐቴን ስለ ጠበቀው ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ስል በሕይወት ዘመኑ ሁሉ እንዲገዛ አድርጌዋለሁ። 35መንግሥትን ከልጁ እጅ እወስዳለሁ፤ ለአንተም ዐሥሩን ነገድ እሰጥሃለሁ። 36ስሜ እንዲኖርባት በመረጥኋት በዚያች በኢየሩሳሌም ከተማ ለባሪያዬ ለዳዊት ምንጊዜም በፊቴ መብራት እንዲኖረው፣ ለልጁ አንድ ነገድ እሰጣለሁ። 37አንተን ግን እኔ እወስድሃለሁ፤ ልብህ በወደደው ሁሉ ላይ ትነግሣለህ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ትሆናለህ። 38ባሪያዬ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ አንተም ያዘዝሁህን ሁሉ ብትፈጽም፣ በመንገዴ ብትሄድ፣ ሥርዐቴንና ትእዛዜን በመጠበቅ ትክክል የሆነውን ነገር በፊቴ ብታደርግ፣ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ የዳዊትን ሥርወ መንግሥት እንዳጸናሁ፣ ለአንተም አጸናልሃለሁ፤ እስራኤልንም ለአንተ እሰጣለሁ። 39ከዚህ የተነሣም የዳዊትን ቤት አዋርዳለሁ፤ ነገር ግን ለዘላለም አይደለም።’ ”
40ሰሎሞን ኢዮርብዓምን ለመግደል ፈለገ፤ ኢዮርብዓም ግን ወደ ግብፅ ሸሸ፤ ወደ ንጉሡ ወደ ሺሻቅ ሄዶ፣ ሰሎሞን እስኪሞት ድረስ በዚያው ተቀመጠ።
የሰሎሞን መሞት
11፥41-43 ተጓ ምብ – 2ዜና 9፥29-31
41የቀረው በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት የተከናወነው፣ የሠራውም ሁሉ፣ ጥበቡም በሰሎሞን የታሪክ መጽሐፍ ተጽፎ የለምን? 42ሰሎሞን በመላው እስራኤል ላይ በኢየሩሳሌም የነገሠው አርባ ዓመት ነው። 43ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም ሮብዓም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

Currently Selected:

1 ነገሥት 11: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in