Лого на YouVersion
Иконка за търсене

ሉቃስ 16

16
የብልኁ መጋቢ ምሳሌነት
1ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፤ “አንድ ሀብታም ሰው አንድ መጋቢ ነበረው፤ ይኸው መጋቢ የሀብታሙን ሰው ንብረት እንደሚያባክን ለዚሁ ሰው ወሬ ደረሰው። 2ስለዚህ አስጠራውና፣ ‘ይህ የምሰማብህ ምንድን ነው? ከእንግዲህ አንተ መጋቢ ልትሆነኝ ስለማትችል፣ የምታስተዳድረውን ንብረት መቈጣጠሪያ ሒሳብ አስረክበኝ’ አለው።
3 “መጋቢውም በልቡ እንዲህ አለ፤ ‘ጌታዬ ከመጋቢነት ሊሽረኝ ነው፤ ለማረስ ጕልበት የለኝም፤ መለመን ደግሞ ዐፍራለሁ፤ ስለዚህ ምን ላድርግ? 4ከመጋቢነት የተሻርሁ እንደ ሆነ፣ ሰዎች በቤታቸው እንዲቀበሉኝ የማደርገውን ዐውቃለሁ።’
5 “ስለዚህ የጌታው ዕዳ ያለባቸውን ሰዎች እያንዳንዳቸውን ጠራ፤ የመጀመሪያውንም ሰው ‘የጌታዬ ዕዳ ምን ያህል አለብህ?’ አለው።
6 “እርሱም፣ ‘አንድ መቶ ማድጋ # 16፥6 ምናልባት 3 ሺሕ ሊትር ይሆናል ዘይት አለብኝ’ አለ።
“መጋቢውም፣ ‘የውል ወረቀትህን ዕንካ፤ ቶሎ ተቀምጠህ “አምሳ ማድጋ” ብለህ ጻፍ’ አለው።
7 “ከዚያም ሌላውን፣ ‘አንተስ ስንት አለብህ?’ አለው።
“እርሱም፣ ‘አምሳ ዳውላ # 16፥7 ምናልባት አንድ መቶ የቆሮስ መስፈሪያ ወይም 35 ሺሕ ሊትር ይሆናል። ስንዴ’ አለው።
“መጋቢውም፣ ‘የብድር ደብዳቤህን ዕንካ፤ “አርባ ዳውላ” ብለህ ጻፍ’ አለው።
8 “ጌታውም አጭበርባሪውን መጋቢ በብልኅነቱ አደነቀው፤ የዚህ ዓለም ልጆች ከመሰሎቻቸው ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ከብርሃን ልጆች ይልቅ ብልኆች ናቸውና። 9ስለዚህ እላችኋለሁ፤ የዚህ ዓለም ገንዘብ ባለቀ ጊዜ በዘላለም ቤት ተቀባይነት እንዲኖራችሁ፣ በዚሁ ገንዘብ ወዳጆችን ለራሳችሁ አፍሩበት።
10 “በትንሽ ነገር ታማኝ የሆነ በትልቁም ይታመናል፤ በትንሽ ነገር ያልታመነ በትልቁም አይታመንም። 11እንግዲህ፣ በዚህ ዓለም ሀብት ካልታመናችሁ፣ እውነተኛውንማ ሀብት ማን ዐደራ ብሎ ይሰጣችኋል? 12በሌላው ሰው ሀብት ካልታመናችሁ፣ የራሳችሁ የሆነውን ሀብት ማን ይሰጣችኋል?
13 “በአንድ ጊዜ ሁለት ጌቶችን ማገልገል የሚችል ማንም ባሪያ የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወድዳል፤ ወይም አንዱን ይጠጋል፤ ሌላውን ይንቃል። የእግዚአብሔርም የገንዘብም ባሪያ መሆን አትችሉም።”
14ገንዘብ የሚወድዱ ፈሪሳውያን ይህን ሁሉ ሰምተው በኢየሱስ ላይ አፌዙበት። 15እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ በሰዎች ፊት ራሳችሁን የምታጸድቁ ናችሁ፤ እግዚአብሔር ግን ልባችሁን ያውቃል፤ በሰዎች ዘንድ የከበረ፣ በእግዚአብሔር ፊት የረከሰ ነውና።
16 “ሕግና ነቢያት እስከ ዮሐንስ ድረስ ሲነገሩ ኖረዋል፤ ከዚያ በኋላ ግን የእግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች ተሰብኳል፤ ሰውም ሁሉ ወደዚያ ለመግባት ይሻማል። 17ነገር ግን ከሕግ አንዲት ነጥብ ከምትወድቅ ሰማይና ምድር ቢያልፍ ይቀልላል።
18 “ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፤ ከባሏ የተፋታችውንም ሴት የሚያገባ ያመነዝራል።”
ሀብታሙ ሰውና አልዓዛር
19ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ሐምራዊና ቀጭን በፍታ የለበሰ፣ በየቀኑም በተድላ ደስታ የሚኖር አንድ ሀብታም ሰው ነበረ። 20በአንጻሩም፣ መላ ሰውነቱ በቍስል የተወረረ አንድ አልዓዛር የሚባል ድኻ በዚህ ሀብታም ሰው ደጃፍ ይተኛ ነበር፤ 21ከሀብታሙ ሰው ማእድ የወደቀውን ፍርፋሪ እንኳ ሊመገብ ይመኝ ነበር፤ ውሾችም ሳይቀሩ መጥተው ቍስሉን ይልሱ ነበር።
22 “ይህም ድኻ ሞተ፤ መላእክትም ወደ አብርሃም ዕቅፍ ወሰዱት። ሀብታሙም ሰው ደግሞ ሞቶ ተቀበረ። 23በሲኦልም እየተሠቃየ ሳለ ቀና ብሎ ከሩቅ አብርሃምን አየ፤ አልዓዛርንም በዕቅፉ ይዞት አየ። 24እርሱም፣ ‘አብርሃም አባት ሆይ፤ ራራልኝ፤ በዚህ ነበልባል እየተሠቃየሁ ስለሆነ፣ አልዓዛር የጣቱን ጫፍ ውሃ ነክሮ ምላሴን እንዲያቀዘቅዝልኝ እባክህ ላክልኝ’ እያለ ጮኸ።
25 “አብርሃም ግን እንዲህ አለው፤ ‘ልጄ ሆይ፤ አንተ በምድራዊ ሕይወትህ ዘመን መልካም ነገሮችን እንደ ተቀበልህ፣ አልዓዛርም ደግሞ ክፉ ነገሮችን እንደ ተቀበለ አስታውስ፤ አሁን ግን እርሱ እዚህ ሲጽናና፣ አንተ በሥቃይ ላይ ትገኛለህ። 26ከሁሉም በላይ ከዚህ ወደ እናንተ ለማለፍ የሚፈልጉ እንደማይችሉ፣ እዚያ ያሉትም ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ፣ በእኛና በእናንተ መካከል ትልቅ ገደል ተደርጓል።’
27 “እርሱም እንዲህ አለ፤ ‘አባት ሆይ፤ እንግዲያውስ አልዓዛርን ወደ አባቴ ቤት እንድትሰድደው እለምንሃለሁ፤ 28አምስት ወንድሞች ስላሉኝ፣ እነርሱም ወደዚህ የሥቃይ ስፍራ እንዳይመጡ ያስጠንቅቃቸው።’
29 “አብርሃም ግን፣ ‘ሙሴና ነቢያት አሏቸው፤ እነርሱን ይስሙ’ አለው።
30 “እርሱም፣ ‘አብርሃም አባት ሆይ፤ እንደዚህ አይደለም፤ አንድ ሰው ከሙታን ተነሥቶ ቢሄድላቸው ንስሓ ይገባሉ’ አለ።
31 “አብርሃምም፣ ‘ሙሴንና ነቢያትን የማይሰሙ ከሆነ፣ አንድ ሰው ከሙታን ቢነሣ እንኳ አያምኑም’ አለው።”

Избрани в момента:

ሉቃስ 16: NASV

Маркирай стих

Споделяне

Копиране

None

Искате ли вашите акценти да бъдат запазени на всички ваши устройства? Регистрирайте се или влезте