ኦሪት ዘፍጥረት 8

8
የጥፋት ውሃ ፍጻሜ
1እግዚአብሔር ኖኅንና ከእርሱ ጋር በመርከቡ ውስጥ የነበሩትን አራዊትና እንስሶች ሁሉ አሰበ፤ ነፋስ በምድር ላይ እንዲነፍስ አደረገ፤ ውሃውም መጒደል ጀመረ። 2ከምድር በታች ያሉት ጥልቅ ምንጮች፥ በሰማይ ያሉት የውሃ መውረጃ በሮች ሁሉ ተዘጉ፤ ዝናቡም ከሰማይ መውረዱን አቆመ። 3ውሃው ቀስ በቀስ ከምድር ላይ መጒደል ጀመረ፤ ከመቶ ኀምሳ ቀኖችም በኋላ ውሃው ከምድር ላይ በጣም ጐደለ። 4በሰባተኛው ወር፥ በዐሥራ ሰባተኛው ቀን መርከቡ “አራራት” ከተባሉት ተራራዎች በአንደኛው ጫፍ ላይ ዐረፈ። 5ውሃው እስከ ዐሥረኛው ወር ድረስ ቀስ በቀስ እየጐደለ ሄደ፤ በዐሥረኛው ወር መጀመሪያው ቀን የተራሮቹ ጫፎች ታዩ።
6ከአርባ ቀን በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቡን መስኮት ከፈተ፤ 7ቊራን ወደ ውጪ ላከው፤ ቊራውም ውሃው ከምድር እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር። 8ከዚህ በኋላ ኖኅ ውሃው ከምድር ላይ መጒደሉን ለማወቅ አንዲት ርግብ ላከ። 9ነገር ግን ውሃው ገና ምድርን ሁሉ ሸፍኖ ስለ ነበር ርግቢቱ የምታርፍበት ቦታ አላገኘችም፤ ስለዚህ ኖኅ ወዳለበት መርከብ ተመልሳ መጣች፤ ኖኅም እጁን ዘርግቶ ወደ ውስጥ አስገባት። 10ሰባት ቀን ከቈየም በኋላ ርግቢቱን እንደገና አውጥቶ ላካት። 11እርስዋም ወደ ማታ ጊዜ የለመለመ የወይራ ዘይት ዛፍ ቅጠል በአፍዋ ይዛ ወደ ኖኅ ተመለሰች፤ በዚህ ሁኔታ ኖኅ ውሃው ከምድር መጒደሉን ዐወቀ። 12ደግሞም ሰባት ቀን ከቈየ በኋላ ኖኅ ርግቢቱን እንደገና አውጥቶ ላካት፤ በዚህን ጊዜ ግን ርግቢቱ ሳትመለስለት ቀረች።
13የኖኅ ዕድሜ 601 ዓመት በሆነ ጊዜ በመጀመሪያው ወር፥ በመጀመሪያው ቀን ውሃው ከምድር ላይ ደረቀ፤ ኖኅ የመርከቡን ክዳን አንሥቶ ዙሪያውን ተመለከተ፤ ምድሪቱ እንደ ደረቀች አየ። 14በሁለተኛው ወር ከወሩም በሃያ ሰባተኛው ቀን ምድር ፈጽማ ደረቀች።
15እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው፤ 16“አንተ ከሚስትህ፥ ከልጆችህና ከልጆችህ ሚስቶች ጋር ሆነህ ከመርከቡ ውጣ፤ 17ተራብተውና ተባዝተው ምድርን ሁሉ እንዲሞሉ ከአንተ ጋር ያሉትን ሕያዋን ፍጥረቶች ሁሉ ወፎችን፥ እንስሶችንና ሌሎችን በምድር ላይ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱትን ፍጥረቶች ሁሉ ይዘህ ውጣ።” 18ከዚህ በኋላ ኖኅ ከሚስቱ፥ ከልጆቹና ከልጆቹ ሚስቶች ጋር ሆኖ ከመርከቡ ወጣ፤ 19አራዊትና እንስሶች፥ ወፎችም በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችም በየወገናቸው ሆነው ከመርከቡ ወጡ።
ኖኅ መሥዋዕት አቀረበ
20ኖኅ ለእግዚአብሔር መሠዊያን ሠራ፤ ንጹሕ ከሆኑት እንስሶችና ወፎች ሁሉ ከየዐይነቱ አንዳንድ ወሰደ፤ መሥዋዕት እንዲሆኑም ሁሉንም በመሠዊያው ላይ አቃጠላቸው። 21የመሥዋዕቱም መዓዛ እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው፤ በሐሳቡም እንዲህ አለ፥ ገና ከሕፃንነቱ ጊዜ ጀምሮ የሰው ሐሳብ ክፉ መሆኑን ስለማውቅ፤ “ሰው በሚፈጽመው በደል ሁሉ ከእንግዲህ ወዲህ ምድርን አልረግምም፤ በአሁኑ ጊዜ እንዳደረግሁት ሕይወት ያለውን ፍጥረት ሁሉ ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አላጠፋም።
22ምድር እስካለች ድረስ፥
ለመዝራትና ለማጨድ፥ ለብርድና ለሙቀት፥
ለበጋና ለክረምት፥ ለቀንና ለሌሊት የማያቋርጥ ጊዜ ይኖራል።”

Пазнака

Падзяліцца

Капіяваць

None

Хочаце, каб вашыя адзнакі былі захаваны на ўсіх вашых прыладах? Зарэгіструйцеся або ўвайдзіце