ዘፍጥረት 1

1
የፍጥረት አጀማመር
1በመጀመሪያ እግዚአብሔር#1፥1 ከዚህ ምዕራፍ በቀር፣ በመቅድሙ ላይ እንደ ተጠቀሰው፣ እግዚአብሔር የሚለው ስም ጥቅም ላይ የዋለው ለያህዌ ብቻ ነው። ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ። 2ምድርም ቅርጽ የለሽና ባዶ ነበረች።#1፥2 ወይም ሆነች የምድርን ጥልቅ ስፍራ ሁሉ ጨለማ ውጦት ነበር። የእግዚአብሔርም መንፈስ በውሆች ላይ ይረብብ ነበር።
3እግዚአብሔርም “ብርሃን ይሁን” አለ፤ ብርሃንም ሆነ። 4እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደ ሆነ አየ፤ ብርሃኑን ከጨለማ ለየ። 5እግዚአብሔርም ብርሃኑን “ቀን”፣ ጨለማውን “ሌሊት” ብሎ ጠራው። መሸ፤ ነጋም፤ የመጀመሪያ ቀን።
6እግዚአብሔር፣ “ውሃን ከውሃ የሚለይ ጠፈር በውሆች መካከል ይሁን” አለ። 7ስለዚህ እግዚአብሔር ጠፈርን አድርጎ ከጠፈሩ በላይና ከጠፈሩ በታች ያለውን ውሃ ለየ፤ እንዳለውም ሆነ። 8እግዚአብሔር ጠፈርን “ሰማይ” ብሎ ጠራው። መሸ፤ ነጋም፤ ሁለተኛ ቀን።
9ከዚያም እግዚአብሔር፣ “ከሰማይ በታች ያለው ውሃ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ፤ ደረቁ ምድር ይገለጥ” አለ፤ እንዳለውም ሆነ። 10እግዚአብሔር ደረቁን ምድር፣ “የብስ”፣ በአንድነት የተሰበሰበውን ውሃ፣ “ባሕር” ብሎ ጠራው። እግዚአብሔር ይህ መልካም እንደ ሆነ አየ።
11እግዚአብሔር፣ “ምድር ዕፀዋትንም፣ እንደየወገናቸው ዘር የሚሰጡ ተክሎችንና በምድር ላይ ዘር ያዘሉ ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎችን እንደየወገናቸው ታብቅል” አለ፤ እንዳለውም ሆነ። 12ምድር ዕፀዋትን፣ እንደየወገናቸው ዘር የሚሰጡ ተክሎችንና በውስጣቸው ዘር ያለባቸው ፍሬ የሚያፈሩትን ዛፎች በየወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም ይህ መልካም እንደ ሆነ አየ። 13መሸ፤ ነጋም፤ ሦስተኛ ቀን።
14ከዚያም እግዚአብሔር፣ “ቀኑን ከሌሊት እንዲለዩ፣ የዓመት ወቅቶች፣ ቀናትና ዓመታት የሚጀምሩበትንም እንዲያመለክቱ፣ 15ለምድር ብርሃን የሚሰጡ ልዩ ልዩ ብርሃናት በሰማይ ይሁኑ” አለ፤ እንዳለውም ሆነ። 16እግዚአብሔር፣ ለምድር ብርሃን ይሰጡ ዘንድ ሁለት ታላላቅ ብርሃናት አደረገ፤ ታላቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፣ ታናሹ ብርሃን በሌሊት እንዲሠለጥን አደረገ። እንዲሁም ከዋክብትን አደረገ። 17ለምድር ብርሃን እንዲሰጡ እግዚአብሔር እነዚህን በሰማይ ጠፈር አኖራቸው። 18ይኸውም በቀንና በሌሊት እንዲሠለጥኑ፣ ብርሃንን ከጨለማ እንዲለዩ ነው። እግዚአብሔርም ይህ መልካም እንደ ሆነ አየ። 19መሸ፤ ነጋም፣ አራተኛ ቀን።
20እግዚአብሔር፣ “ውሆች ሕይወት ባላቸው በሕያዋን ፍጥረታት ይሞሉ፤ ወፎች ከምድር በላይ በሰማይ ጠፈር ይብረሩ” አለ። 21በዚህ መሠረት፣ እግዚአብሔር በባሕር ውስጥ የሚኖሩ ታላላቅ ፍጥረታትን፣ በውሃ ውስጥ የሚርመሰመሱ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ እንደየወገናቸው እንዲሁም ክንፍ ያላቸውን ወፎች ሁሉ እንደየወገናቸው ፈጠረ፤ እግዚአብሔርም ይህ መልካም እንደ ሆነ አየ። 22እግዚአብሔርም፣ “ብዙ ተባዙ፤ የባሕርንም ውሃ ሙሏት፤ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ” ብሎ ባረካቸው። 23መሸ፤ ነጋም፤ ዐምስተኛ ቀን።
24እግዚአብሔር፣ “ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን እንደየወገናቸው፣ ከብቶችን፣ በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጥረታትንና የዱር እንስሳትን እያንዳንዱን እንደ ወገኑ ታስገኝ” አለ፤ እንዳለውም ሆነ። 25እግዚአብሔር የዱር እንስሳትን እንደየወገናቸው፣ ከብቶችን እንደየወገናቸው፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጥረታትን እንደየወገናቸው አደረገ። እግዚአብሔርም ይህ መልካም እንደ ሆነ አየ።
26እግዚአብሔር፣ “ሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንሥራ፤ በባሕር ዓሦች፣ በሰማይ ወፎች፣ በከብቶች፣#1፥26 የማሶሬቲክ ጽሑፍም እንደዚሁ ሲሆን ሱርስቱ ግን የዱር እንስሳት ሁሉ ይለዋል። በምድር ሁሉ ላይ፣ እንዲሁም በምድር ላይ በሚሳቡ ፍጥረታት ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራቸው” አለ።
27ስለዚህ እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤
በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤
ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።
28እግዚአብሔርም፣ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ግዟቸው” ብሎ ባረካቸው።
29እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “በምድር ላይ ያሉትን ዘር የሚሰጡ ተክሎችን ሁሉ፣ በፍሬአቸው ውስጥ ዘር ያለባቸውን ዛፎች ሁሉ ምግብ ይሆኑላችሁ ዘንድ ሰጥቻችኋለሁ። 30እንዲሁም ለምድር አራዊት ሁሉ፣ ለሰማይ ወፎች ሁሉ፣ በምድር ላይ ለሚንቀሳቀሱ ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ማንኛውም ለምለም ተክል ምግብ እንዲሆናቸው ሰጥቻለሁ” እንዳለውም ሆነ።
31እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ። መሸ፤ ነጋም፤ ስድስተኛ ቀን።

Цяпер абрана:

ዘፍጥረት 1: NASV

Пазнака

Падзяліцца

Капіяваць

None

Хочаце, каб вашыя адзнакі былі захаваны на ўсіх вашых прыладах? Зарэгіструйцеся або ўвайдзіце