ማሕልየ መሓልይ 2:1-13

ማሕልየ መሓልይ 2:1-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እኔ የዱር ጽጌ​ረዳ፥ የቈ​ላም የሱፍ አበባ ነኝ። በእ​ሾህ መካ​ከል እን​ዳለ የሱፍ አበባ፥ እን​ዲሁ ወዳጄ በቈ​ነ​ጃ​ጅት መካ​ከል ነሽ። በዱር እን​ዳለ እን​ኮይ፥ እን​ዲሁ ውዴ በወ​ን​ድ​ሞች መካ​ከል ነው። ከጥ​ላው በታች እጅግ ወድጄ ተቀ​መ​ጥሁ፥ ፍሬ​ውም ለጕ​ሮ​ሮዬ ጣፋጭ ነው። ወደ ወይን ቤት አገ​ቡኝ፥ በእ​ኔም ላይ ፍቅ​ርን አደ​ረጉ። በሽቱ አጸ​ኑኝ፥ በእ​ን​ኮ​ይም አበ​ረ​ታ​ቱኝ፥ በፍ​ቅሩ ተነ​ድ​ፌ​አ​ለ​ሁና። ቀኙ ታቅ​ፈ​ኛ​ለች። ግራ​ውም ከራሴ በታች ናት፥ እና​ንተ የኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ቈነ​ጃ​ጅት ሆይ፥ ወድዶ እስ​ኪ​ነሣ ድረስ፥ ፍቅ​ሬን እን​ዳ​ት​ቀ​ሰ​ቅ​ሱ​ትና እን​ዳ​ታ​ስ​ነ​ሡት፥ በም​ድረ በዳው ኀይ​ልና ጽናት አም​ላ​ች​ኋ​ለሁ። እነሆ፥ የልጅ ወን​ድሜ ቃል በተ​ራ​ሮች ላይ ሲዘ​ልል፥ በኮ​ረ​ብ​ቶ​ችም ላይ ሲወ​ረ​ወር ይመ​ጣል። ልጅ ወን​ድሜ በቤ​ቴል ተራ​ሮች ላይ ሚዳ​ቋን ወይም የዋ​ሊ​ያን እን​ም​ቦሳ ይመ​ስ​ላል፤ እነሆ፥ በመ​ስ​ኮ​ቶች ሲጐ​በኝ፥ በዐ​ይነ ርግ​ብም ሲመ​ለ​ከት፥ እርሱ ከቅ​ጥ​ራ​ችን በኋላ ቆሞ​አል። ልጅ ወን​ድሜ እን​ዲህ ብሎ መለ​ሰ​ልኝ፦ ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ፥ መል​ካ​ምዋ ርግቤ ሆይ፥ ነዪ። እነሆ፥ ክረ​ምቱ ዐለፈ፥ ዝና​ሙም አልፎ ሄደ፤ አበባ በም​ድር ላይ ታየ፥ የመ​ከ​ርም ጊዜ ደረሰ፥ የቍ​ር​ዬ​ውም ቃል በም​ድ​ራ​ችን ተሰማ። በለሱ ጐመራ፥ ወይ​ኖ​ችም አበቡ፥ መዓ​ዛ​ቸ​ው​ንም ሰጡ፤ ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ፤ መል​ካ​ምዋ ርግቤ ሆይ፥ ነዪ። በዐ​ለት ንቃ​ቃ​ትና በገ​ደል መሸ​ሸ​ጊያ ወዳ​ለው ጥላ ነዪ።

ማሕልየ መሓልይ 2:1-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እኔ የሳሮን ጽጌረዳ፣ የሸለቆም አበባ ነኝ። በእሾኽ መካከል እንዳለ ውብ አበባ፣ ውዴም በቈነጃጅት መካከል እንዲሁ ናት። በዱር ዛፎች መካከል እንዳለ እንኮይ፣ ውዴም በጕልማሶች መካከል እንዲሁ ነው፤ በጥላው ሥር መቀመጥ ደስ ያሰኛል፤ የፍሬውም ጣፋጭነት ያረካኛል። ወደ ግብዣው አዳራሽ ወሰደኝ፤ በእኔ ላይ ያለው ዐላማው ፍቅር ነው። በዘቢብ አበረታቱኝ፤ በእንኮይም አስደስቱኝ፤ በፍቅሩ ተይዤ ታምሜአለሁና። ግራ እጁን ተንተርሻለሁ፤ ቀኝ እጁም ዐቅፎኛል። እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት፣ ራሱ እስኪፈልግ ድረስ፣ ፍቅርን እንዳታስነሡት ወይም እንዳትቀሰቅሱት፣ በሚዳቋና በሜዳ ዋሊያ አማፅናችኋለሁ። እነሆ፤ የውዴ ድምፅ በተራሮች ላይ እየዘለለ፣ በኰረብቶችም ላይ እየተወረወረ፣ ሲመጣ ይሰማኛል። ውዴ ሚዳቋ ወይም የዋሊያ ግልገል ይመስላል፤ እነሆ፤ ከቤታችን ግድግዳ ኋላ ቆሟል፤ በመስኮት ትክ ብሎ ወደ ውስጥ ያያል፤ በፍርግርጉም እያሾለከ ይመለከታል። ውዴም እንዲህ አለኝ፤ “ፍቅሬ ሆይ፤ ተነሺ፤ አንቺ የእኔ ቈንጆ፤ ከእኔ ጋራ ነዪ። እነሆ! ክረምቱ ዐለፈ፤ ዝናቡም አባርቶ አበቃ፤ አበቦች በምድር ላይ ታዩ፤ የዝማሬ ወቅት መጥቷል፤ የርግቦችም ድምፅ፣ በምድራችን ተሰማ። በለስ ፍሬዋን አፈራች፤ ያበቡ ወይኖችም መዐዛቸውን ሰጡ፤ ፍቅሬ ሆይ፤ ተነሺና ነዪ፤ አንቺ የእኔ ቈንጆ፤ ከእኔ ጋራ ነዪ።”

ማሕልየ መሓልይ 2:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እኔ የሳሮን ጽጌ ረዳ የቈላም አበባ ነኝ። በእሾህ መካከል እንዳለ የሱፍ አበባ፥ እንዲሁ ወዳጄ በቈነጃጅት መካከል ናት። በዱር እንዳለ እንኮይ፥ እንዲሁ ውዴ በልጆች መካከል ነው። ከጥላው በታች እጅግ ወድጄ ተቀመጥሁ፥ ፍሬውም በጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው። ወደ ወይን ጠጁም ቤት አገባኝ፥ በእኔ ላይ ያለው ዓላማውም ፍቅር ነው። በዘቢብም አጽናኑኝ፥ በእንኮይ አበረታቱኝ፥ በፍቅሩ ተነድፌ ታምሜያለሁና። ግራው ከራሴ በታች ናት፥ ቀኙም ታቅፈኛለች። እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እርሱ እስኪፈልግ ድረስ፥ ፍቅርን እንዳታስነሱትና እንዳታነሣሡት በሚዳቋ በምድረ በዳም ዋላ አምላችኋለሁ። እነሆ፥ የውዴ ቃል! በተራሮች ላይ ሲዘልል በኮረብቶችም ላይ ሲወረወር ይመጣል። ውዴ ሚዳቋን ወይም የዋላን እምቦሳ ይመስላል፥ እነሆ፥ በመስኮቶች ሲጐበኝ፥ በዓይነ ርግብም ሲመለከት፥ እርሱ ከቅጥራችን በኋላ ቆሞአል። ውዴ እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፦ ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ፥ ውበቴ ሆይ፥ ነዪ። እነሆ፥ ክረምት አለፈ፥ ዝናቡም አልፎ ሄደ። አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፥ የዜማም ጊዜ ደረሰ፥ የቍርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ። በለሱ ጐመራ፥ ወይኖችም አበቡ መዓዛቸውንም ሰጡ፥ ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ፥ ውበቴ ሆይ፥ ነዪ።

ማሕልየ መሓልይ 2:1-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እኔ እንደ ሳሮን ጽጌረዳና በሸለቆ ውስጥ እንደሚበቅል የሱፍ አበባ ነኝ። ውዴ በሴቶች መካከል ስትታይ በእሾኽ መካከል እንደሚታይ የሱፍ አበባ ናት። ውዴ ከሌሎች ጐልማሶች ጋር ሲነጻጸር በዱር ዛፎች መካከል አምሮ እንደሚታይ የፖም ዛፍ ነው፤ እኔም እጅግ ደስ ብሎኝ በጥላው ሥር ዐረፍኩ፤ ጣፋጭ ፍሬውንም በመመገብ ተደሰትኩ። ወደ ምግብ አዳራሹ አስገባኝ፤ ፍቅሩንም እንደ ሰንደቅ ዓላማ በእኔ ላይ ከፍ ከፍ አደረገ። እኔ በፍቅሩ ተይዤ ስለ ታመምኩ ዘቢብ እየመገባችሁ አበረታቱኝ፤ በፖም ፍሬም አስደስቱኝ። ግራ እጁን ያንተርሰኛል፤ በቀኝ እጁም ያቅፈኛል። እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ! ፍቅር ራሱ ፈቅዶ እስኪነሣ ድረስ ቀስቅሳችሁ እንዳታስነሡት፤ በፈጣን አጋዘንና በምድረ በዳ ዋልያ ስም ዐደራ እላችኋለሁ። ውዴ በተራሮችና በኮረብቶች ላይ እየዘለለና እየተወረወረ ሲመጣ ድምፁ ይሰማል። ውዴ፥ ዋልያ ወይም የአጋዘን ግልገል ይመስላል፤ እነሆም ከቤታችን ቅጽር አጠገብ ቆሞአል፤ በመስኮትም ወደ ውስጥ ይመለከታል፤ በዐይነ ርግቡ ቀዳዳ በኩል አሾልኮ ይቃኛል። ውዴ እንዲህ ይለኛል፥ ውዴ ሆይ! ተነሺ፤ የእኔ ውብ ሆይ! ነይ አብረን እንሂድ፤ እነሆ፥ ክረምቱ አልፎአል፤ ዝናቡም ቆሞአል፤ በየመስኩ አበባዎች መታየት ጀምረዋል፤ የዜማ ወራት ደርሶአል፤ የርግቦችም ዜማ በምድራችን ይሰማል። በለስ ማፍራት ጀምሮአል፤ የወይን ተክልም አብቦአል፤ የአበባውም ሽታ ምድርን ሞልቶታል፤ ስለዚህ ውዴ ሆይ! ተነሺ፤ የእኔ ውብ ሆይ! ነይ አብረን እንሂድ።

ማሕልየ መሓልይ 2:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እኔ የሳሮን ጽጌረዳ የቈላም አበባ ነኝ። በእሾህ መካከል እንዳለ የሱፍ አበባ፥ እንዲሁ ወዳጄ በልጃገረዶች መካከል ናት። በዱር እንዳለ እንኮይ፥ እንዲሁ ውዴ በጐልማሶች መካከል ነው። ከጥላው በታች እጅግ ወድጄ ተቀመጥሁ፥ ፍሬውም ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው። ወደ ወይን ጠጁም ቤት አገባኝ፥ በእኔ ላይ ያለው ዓላማውም ፍቅር ነው። በዘቢብም አጽናኑኝ፥ በእንኮይ አበረታቱኝ፥ በፍቅሩ ተነድፌ ታምሜያለሁና። ግራው ከራሴ በታች ናት፥ ቀኙም ታቅፈኛለች። እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እርሱ እስኪፈልግ ድረስ፥ ፍቅርን እንዳታስነሱትና እንዳታነሣሡት በሚዳቋ በምድረ በዳም ዋላ አስምላችኋለሁ። እነሆ፥ የውዴ ድምፅ! በተራሮች ላይ ሲዘልል በኮረብቶችም ላይ ሲወረወር ይመጣል። ውዴ ሚዳቋን ወይም የዋላን እምቦሳ ይመስላል፥ እነሆ፥ በመስኮቶች ሲጐበኝ፥ በዓይነ ርግብም ሲመለከት፥ እርሱ ከቅጥራችን በኋላ ቆሞአል። ውዴ እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፦ ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ፥ ውቤ ሆይ፥ ነዪ። እነሆ፥ ክረምት አለፈ፥ ዝናቡም አልፎ ሄደ። አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፥ የዜማም ጊዜ ደረሰ፥ የዋኔዋም ቃል በምድራችን ተሰማ። በለሱ ጐመራ፥ ወይኖችም አበቡ መዓዛቸውንም ሰጡ፥ ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ፥ ውቤ ሆይ፥ ነዪ።