መኃልየ መኃልይ 2
2
1እኔ የሳሮን ጽጌ ረዳ የቈላም አበባ ነኝ።
2በእሾህ መካከል እንዳለ የሱፍ አበባ፥
እንዲሁ ወዳጄ በቈነጃጅት መካከል ናት።
3በዱር እንዳለ እንኮይ፥
እንዲሁ ውዴ በልጆች መካከል ነው።
ከጥላው በታች እጅግ ወድጄ ተቀመጥሁ፥
ፍሬውም በጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው።
4ወደ ወይን ጠጁም ቤት አገባኝ፥
በእኔ ላይ ያለው ዓላማውም ፍቅር ነው።
5በዘቢብም አጽናኑኝ፥
በእንኮይ አበረታቱኝ፥
በፍቅሩ ተነድፌ ታምሜያለሁና።
6ግራው ከራሴ በታች ናት፥
ቀኙም ታቅፈኛለች።
7እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥
እርሱ እስኪፈልግ ድረስ፥
ፍቅርን እንዳታስነሱትና እንዳታነሣሡት
በሚዳቋ በምድረ በዳም ዋላ አምላችኋለሁ።
8እነሆ፥ የውዴ ቃል!
በተራሮች ላይ ሲዘልል
በኮረብቶችም ላይ ሲወረወር ይመጣል።
9ውዴ ሚዳቋን ወይም የዋላን እምቦሳ ይመስላል፥
እነሆ፥ በመስኮቶች ሲጐበኝ፥
በዓይነ ርግብም ሲመለከት፥
እርሱ ከቅጥራችን በኋላ ቆሞአል።
10ውዴ እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፦
ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ፥
ውበቴ ሆይ፥ ነዪ።
11እነሆ፥ ክረምት አለፈ፥
ዝናቡም አልፎ ሄደ።
12አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፥
የዜማም ጊዜ ደረሰ፥
የቍርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ።
13በለሱ ጐመራ፥ ወይኖችም አበቡ
መዓዛቸውንም ሰጡ፥
ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ፥
ውበቴ ሆይ፥ ነዪ።
14በዓለት ንቃቃትና በገደል መሸሸጊያ ያለሽ ርግብ ሆይ፥
ቃልሽ መልካም ፊትሽም ያማረ ነውና መልክሽን አሳዪኝ፥
ድምፅሽንም አሰሚኝ።
15ወይናችን አብቦአልና
የወይናችንን ቦታ የሚያጠፉትን ቀበሮች፥
ጥቃቅኑን ቀበሮች አጥምዳችሁ ያዙልን።
16ውዴ የእኔ ነው፥ እኔም የእርሱ ነኝ፥
በሱፍ አበባዎች መካከልም መንጋውን ያሰማራል።
17ውዴ ሆይ፥ ቀኑ እስኪነፍስ፥
ጥላውም እስኪሸሽ ድረስ ተመለስ፥
በቅመም ተራራ ላይ ሚዳቋውን
ወይም የዋላውን እምቦሳ ምሰል።
Currently Selected:
መኃልየ መኃልይ 2: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ