ሩት 1:10-22

ሩት 1:10-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እነርሱም፦ ከአንቺ ጋር ወደ ሕዝብሽ እንመለሳለን አሉአት። ኑኃሚንም አለች፦ ልጆቼ ሆይ፥ ተመለሱ፣ ለምን ከእኔ ጋር ትሄዳላችሁ? ባሎቻችሁ የሚሆኑ ልጆች በሆዴ አሉኝን? ልጆቼ ሆይ፥ ተመለሱ፣ ባል ለማግባት አርጅቻለሁና ሂዱ፣ ተስፋ አለኝ ብል፥ ዛሬ ሌሊትስ እንኳ ባል ባገባ፥ ወንዶች ልጆችም ብወልድ፥ እነርሱ እስኪያድጉ ድረስ ትቆያላችሁን? ስለ እነርሱስ ባል ማግባት ትተዋላችሁን? ልጆቼ ሆይ፥ እንዲህ አይደለም፣ የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ወጥቶአልና ከእናንተ የተነሣ እጅግ ተመርሬአለሁ። ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንደ ገና አለቀሱ፣ ዖርፋም አማትዋን ሳመች፣ ሩት ግን ተጠጋቻት። ኑኃሚንም፦ እነሆ፥ ባልንጀራሽ ወደ ሕዝብዋና ወደ አማልክትዋ ተመልሳለች፣ አንቺም ደግሞ ከባልንጀራሽ ጋር ተመለሽ አለቻት። ሩትም፦ ወደምትሄጅበት እሄዳለሁና፥ በምታድሪበትም አድራለሁና እንድተውሽ ከአንቺም ዘንድ እንድመለስ አታስቸግሪኝ፣ ሕዝብሽ ሕዝቤ፥ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል፣ በምትሞችበትም ስፍራ እሞታለሁ፥ በዚያም እቀበራለሁ፣ ከሞት በቀር አንቺንና እኔን አንዳች ቢለየን እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ እንዲሁም ይጨምርብኝ አለች። ኑኃሚንም ከእርስዋ ጋር ለመሄድ እንደ ቈረጠች ባየች ጊዜ እርስዋን ከመናገር ዝም አለች። ሁለቱም እስከ ቤተ ልሔም ድረስ ሄዱ። ወደ ቤተ ልሔምም በደረሱ ጊዜ የከተማይቱ ሰዎች ሁሉ ስለ እነርሱ፦ ይህች ኑኃሚን ናትን? እያሉ ተንጫጩ። እርስዋም፦ ሁሉን የሚችል አምላክ አስመርሮኛልና ማራ በሉኝ እንጂ ኑኃሚን አትበሉኝ። በሙላት ወጣሁ፥ እግዚአብሔርም ወደ ቤቴ ባዶዬን መለሰኝ፣ እግዚአብሔር አዋርዶኛልና፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ አስጨንቆኛልና ኑኃሚን ለምን ትሉኛላችሁ? አለቻቸው። ኑኃሚንም ከእርስዋም ጋር ከሞዓብ ምድር የተመለሰችው ሞዓባዊቱ ምራትዋ ሩት ተመለሱ። የገብስም መከር በተጀመረ ጊዜ ወደ ቤተልሔም መጡ።

ሩት 1:10-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ቀጥለውም፣ “አይሆንም! ከአንቺ ጋራ ተመልሰን ወደ ወገኖችሽ እንሄዳለን” አሏት። ኑኃሚን ግን እንዲህ አለቻቸው፤ “ልጆቼ ሆይ፤ ወደየቤታችሁ ተመለሱ፤ ከእኔ ጋራ ለምን ትሄዳላችሁ? ባል የሚሆኗችሁ ሌሎች ልጆች ከእንግዲህ የምወልድ ይመስላችኋልን? ወደየቤታችሁ ተመለሱ፣ ልጆቼ፤ ሌላ ባል እንዳላገባ እጅግ አርጅቻለሁ፤ አሁንም ተስፋ አለኝ ብል፣ ዛሬ ማታ አግብቼ ከዚያም ልጆች ብወልድ፣ እስኪያድጉ ድረስ ትጠብቃላችሁን? እነርሱን በመጠበቅ እስከዚያ ሳታገቡ ትቈያላችሁን? ልጆቼ ሆይ፤ እንዲህ አይሆንም፤ ሁኔታው ከእናንተ ይልቅ ለእኔ እጅግ መራራ ነው፤ የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ተነሥቷልና።” እነርሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንደ ገና አለቀሱ፤ ከዚያም ዖርፋ ዐማቷን ስማ ተሰናበተቻት፤ ሩት ግን ልትለያት ስላልፈለገች ተጠመጠመችባት። ኑኃሚን መልሳ፣ “እነሆ የባልሽ ወንድም ሚስት ወደ ወገኖቿና ወደ አማልክቷ ተመልሳለች፤ ዐብረሻት ተመለሽ” አለቻት። ሩት ግን እንዲህ አለች፤ “ተለይቼሽ እንድቀር ወይም እንድመለስ አትለማመጭኝ፤ ወደምትሄጂበት እሄዳለሁ፤ በምትኖሪበትም እኖራለሁ፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽ አምላኬ ይሆናል። በምትሞቺበት እሞታለሁ፤ እዚያው እቀበራለሁ። ከእንግዲህ ሞት ከሚለየን በቀር ብለይሽ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ፤ ከዚህም የከፋ ያድርግብኝ።” ሩት ዐብራት ለመሄድ መቍረጧን በተረዳች ጊዜ፣ ኑኃሚን መጐትጐቷን ተወች። ከዚያም ሁለቱ ሴቶች እስከ ቤተ ልሔም ድረስ ተጓዙ፤ ቤተ ልሔም እንደ ደረሱም፣ በእነርሱ ምክንያት ከተማው በሙሉ ተተረማመሰ፤ ሴቶቹም፣ “ይህች ኑኃሚን ናትን?” በማለት ተገረሙ። እርሷም እንዲህ አለች፤ “ሁሉን ቻይ አምላክ ሕይወቴን እጅግ መራራ አድርጎታልና ማራ በሉኝ እንጂ፣ ኑኃሚን ብላችሁ አትጥሩኝ። በሙላት ወጣሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ባዶዬን መለሰኝ፤ እግዚአብሔር አስጨንቆኝ፣ ሁሉን ቻይ አምላክ መከራ አምጥቶብኝ ሳለ እንዴት ኑኃሚን ብላችሁ ትጠሩኛላችሁ?” አለቻቸው። ስለዚህ ኑኃሚን ከምራቷ ከሞዓባዊቷ ሩት ጋራ በመሆን ከሞዓብ ተመለሰች፤ ቤተ ልሔም የደረሱትም የገብስ አዝመራ በሚሰበሰብበት ወቅት መጀመሪያ ላይ ነበር።

ሩት 1:10-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እነርሱም “ከእንቺ ጋር ወደ ሕዝብሽ እንመለሳለን፤” አሉአት። ኑኃሚንም አለች “ልጆቼ ሆይ! ተመለሱ፤ ለምን ከእኔ ጋር ትሄዳላችሁ? ባሎቻችሁ የሚሆኑ ልጆች በሆዴ አሉኝን? ልጆቼ ሆይ! ተመለሱ፤ ባል ለማግባት አርጅቻለሁና ሂዱ፤ ተስፋ አለኝ ብል፥ ዛሬ ሌሊትስ እንኳ ባል ባገባ፥ ወንዶች ልጆችም ብወልድ፥ እነርሱ እስኪያድጉ ድረስ ትቆያላችሁን? ስለ እነርሱስ ባል ማግባት ትተዋላችሁን? ልጆቼ ሆይ! እንዲህ አይደለም፤ የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ወጥቶአልና ከእናንተ የተነሣ እጅግ ተመርሬአለሁ።” ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንደ ገና አለቀሱ፤ ዖርፋም አማትዋን ሳመች፤ ሩት ግን ተጠጋቻት። ኑኃሚንም “እነሆ፥ ባልንጀራሽ ወደ ሕዝብዋና ወደ አማልክትዋ ተመልሳለች፤ አንቺም ደግሞ ከባልንጀራሽ ጋር ተመለሽ፤” አለቻት። ሩትም “ወደምትሄጅበት እሄዳለሁና፥ በምታድሪበትም አድራለሁና እንድተውሽ ከአንቺም ዘንድ እንድመለስ አታስቸግሪኝ፤ ሕዘሽ ሕዝቤ፥ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል፤ በምትሞችበትም ስፍራ እሞታለሁ፤ በዚያም እቀበራለሁ፤ ከሞት በቀር አንቺንና እኔን አንዳች ቢለየን እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፤ እንዲሁም ይጨምርብኝ፤” አለች። ኑኃሚንም ከእርስዋ ጋር ለመሄድ እንደ ቈረጠች ባየች ጊዜ እርስዋን ከመናገር ዝም አለች። ሁለቱም እስከ ቤተ ልሔም ድረስ ሄዱ። ወደ ቤተ ልሔምም በደረሱ ጊዜ የከተማይቱ ሰዎች ሁሉ ስለ እነርሱ “ይህች ኑኃሚን ናትን?” እያሉ ተንጫጩ። እርስዋም “ሁሉን የሚችል አምላክ አስመርሮኛልና ማራ በሉኝ እንጂ ኑኃሚን አትበሉኝ። በሙላት ወጣሁ፤ እግዚአብሔርም ወደ ቤቴ ባዶዬን መለሰኝ፤ እግዚአብሔር አዋርዶኛልና፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ አስጨንቆኛልና ኑኃሚን ለምን ትሉኛላችሁ?” አለቻቸው። ኑኃሚንም ከእርስዋም ጋር ከሞዓብ ምድር የተመለሰችው ሞዓባዊቱ ምራትዋ ሩት ተመለሱ። የገብስም መከር በተጀመረ ጊዜ ወደ ቤተልሔም መጡ።

ሩት 1:10-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

“አይሆንም! እኛ ከአንቺ ጋር ወደ ወገኖችሽ እንሄዳለን” አሉአት። ናዖሚም እንዲህ አለቻቸው፤ “ልጆቼ ሆይ! እባካችሁ ተመለሱ፤ ከእኔ ጋር ለመሄድ የምትፈልጉት ለምንድነው? ለእናንተ ባሎች የሚሆኑ ልጆች እንደገና መውለድ የምችል ይመስላችኋልን? ልጆቼ ሆይ! ወደየቤታችሁ ተመለሱ፤ እኔ ሌላ ባል እንዳላገባ ዕድሜዬ አይፈቅድልኝም፤ ለመሆኑ ለማግባት ተስፋ ቢኖረኝና ዛሬውኑ አግብቼ ልጆች ብወልድስ፥ እነርሱ ለአካለ መጠን እስኪደርሱ መጠበቅ ትችላላችሁን? በዚህስ ምክንያት ሌሎች ባሎች ሳታገቡ ትቀራላችሁን? ልጆቼ ሆይ! ይህ የማይሆን ነው፤ እኔን እግዚአብሔር ተቈጥቶኛል፤ በእናንተም ላይ በደረሰው ነገር በጣም አዝኜአለሁ” አለቻቸው። እነርሱም እንደገና ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ በዚህ ጊዜ ዖርፋ ዐማትዋን ስማ ተሰናበተች፤ ሩት ግን ከዐማትዋ ላለመለየት ወሰነች። ስለዚህ ናዖሚ “ሩት ሆይ! የባልሽ ወንድም ሚስት ወደ ወገኖችዋና ወደ አማልክትዋ ተመልሳለች፤ አንቺም ከእርስዋ ጋር ተመለሺ” አለቻት። ሩት ግን እንዲህ አለቻት፦ “ተለይቼሽ እንድመለስ አታስገድጅኝ! አንቺ ወደምትሄጂበት ሁሉ እሄዳለሁ፤ አንቺ በምትኖሪበት እኖራለሁ፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ፥ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል፤ በምትሞቺበት እሞታለሁ፤ በምትቀበሪበትም እቀበራለሁ፤ ከሞት በቀር ከአንቺ የሚለየኝ ነገር ቢኖር እግዚአብሔር ይፍረድብኝ!” ሩት ከእርስዋ ጋር ለመሄድ ቊርጥ ሐሳብ ማድረጓን በተረዳች ጊዜ፥ ናዖሚ ሌላ ነገር አልተናገረችም። ስለዚህ ሁለቱም አብረው ወደ ቤተልሔም ተጓዙ፤ ቤተልሔም ሲደርሱም የከተማው ሰዎች ሁሉ ተገረሙ፤ እዚያም ያሉ ሴቶች በመደነቅ “በእርግጥ ይህች ናዖሚ ናትን?” አሉ። እርስዋም እንዲህ አለች፦ “ሁሉን የሚችል አምላክ ሕይወቴን መራራ ስላደረገው ‘ማራ’ በሉኝ እንጂ ‘ናዖሚ’ ብላችሁ አትጥሩኝ፤ ከዚህ አገር በሄድሁ ጊዜ ብዙ ነገር ነበረኝ፤ እግዚአብሔር ግን ባዶ እጄን መልሶኛል፤ ታዲያ ሁሉን የሚችል አምላክ ሲፈርድብኝና ይህን ሁሉ ችግር ሲያደርስብኝ ‘ናዖሚ’ ብላችሁ ለምን ትጠሩኛላችሁ?” እንግዲህ ናዖሚ ከሞአባዊት ምራትዋ ከሩት ጋር ከሞአብ አገር የተመለሰችው በዚህ ሁኔታ ነበር፤ እነርሱ ቤተልሔም በደረሱ ጊዜ የገብስ መከር የሚሰበሰብበት ወቅት መጀመሩ ነበር።

ሩት 1:10-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እነርሱም፦ “ከአንቺ ጋር ወደ ሕዝብሽ እንመለሳለን” አሉአት። ናዖሚም አለች፦ “ልጆቼ ሆይ፥ ተመለሱ፥ ለምን ከእኔ ጋር ትሄዳላችሁ? ለእናንተ ባሎች የሚሆኑ ልጆች በማህፀኔ ይዣለሁን? ልጆቼ ሆይ፥ ተመለሱ፥ ባል ለማግባት አርጅቻለሁና ሂዱ፥ ተስፋ አለኝ ብል፥ ዛሬ ሌሊትስ እንኳ ባል ባገባ፥ ወንዶች ልጆችም ብወልድ፥ እነርሱ እስኪያድጉ እስኪደርሱ መጠበቅ ትችላላችሁን? በእነርሱስ ምክንያት ባል ሳታገቡ ትቆያላችሁን? ልጆቼ ሆይ፥ እንዲህስ አይሆንም፥ እኔን ጌታ ተቈጥቶኛል፤ በእናንተም ላይ በደረሰው ነገር በጣም አዝኜአለሁ።” ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንደገና አለቀሱ፥ ዖርፋም አማቷን ሳመች፥ ሩት ግን አማቷ ጋር ተጣበቀች። እሷም፦ “እነሆ ዋርሳሽ ወደ ሕዝብዋና ወደ አማልክትዋ ተመልሳለች፥ አንቺም ደግሞ ከባልንጀራሽ ጋር ተመለሽ” አለቻት። ሩት ግን እንዲህ አለች፦ “እንድተውሽ ተለይቼሽም እንድመለስ አታስገድጅኝ፤ በምትሄጅበት እሄዳለሁ፥ በምታድሪበትም አድራለሁ፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ፥ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል፤ በምትሞቺበት እሞታለሁ፤ በምትቀበሪበትም እቀበራለሁ፤ ከሞት በቀር ከአንቺ የሚለየኝ ነገር ቢኖር ጌታ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ!” ከእርሷ ጋር ለመሄድ እንደ ቈረጠች ባየች ጊዜ ናዖሚ ከመናገር ዝም አለች። ስለዚህ ሁለቱም እስከ ቤተልሔም ድረስ ሄዱ። ወደ ቤተልሔምም በደረሱ ጊዜ፥ ያገሩ ሰዎች ሁሉ ታወኩ ስለ እነርሱ፥ ሴቶቹም፦ “ይህች ናዖሚን ናትን?” አሉ። እሷም፦ “ሁሉን የሚችል አምላክ አስመርሮኛልና ‘ማራ’ በሉኝ እንጂ ‘ናዖሚ’ አትበሉኝ። በሙላት ወጣሁ፥ ጌታም ባዶዬን መለሰኝ፤ ጌታ በእኔ ላይ ሰቆቃን ሲያደርስ፥ ሁሉን የሚችል አምላክ አስጨንቆኛልና፥ ናዖሚ ብላችሁ ለምን ትጠሩኛላችሁ?” አለቻቸው። ስለዚህ ናዖሚ፥ ከሞአባዊት ምራትዋ ከሩት ጋር፥ ከሞዓብ አገር ተመለሰች። የገብስም መከር መሰብሰቢያ ጅማሬ ላይ ቤተልሔም መጡ።