ሩት 1
1
ኑኃሚንና ሩት
1መሳፍንት#1፥1 በትውፊት ፈራጆች ተብሏል። በሚገዙበት ዘመን፣ በምድሪቱ ላይ ራብ ሆነ፤ አንድ ሰው በይሁዳ ከምትገኘው ከቤተ ልሔም ሚስቱንና ሁለቱን ወንዶች ልጆቹን ይዞ፣ ለተወሰነ ጊዜ ለመኖር ወደ ሞዓብ አገር ሄደ። 2የሰውየው ስም አቤሜሌክ፣ የሚስቱ ኑኃሚን፣ የሁለቱም ወንዶች ልጆቹ ስም መሐሎንና ኬሌዎን ነበር። እነርሱም የይሁዳ ቤተ ልሔም ኤፍራታውያን ሲሆኑ፣ ወደ ሞዓብ አገር ሄደው በዚያ ኖሩ።
3የኑኃሚን ባል አቤሜሌክ ሞተ፤ ኑኃሚን ከሁለት ልጆቿ ጋር ብቻዋን ቀረች። 4ልጆቿም ዖርፋና ሩት የተባሉ የሞዓብ ሴቶችን አገቡ። በዚያም ዐሥር ዓመት ያህል ከኖሩ በኋላ፣ 5መሐሎንና ኬሌዎን ሁለቱም ሞቱ፤ ኑኃሚንም ሁለት ልጆቿንና ባሏን ዐጥታ ብቻዋን ቀረች።
6እርሷም በሞዓብ ሳለች እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደ ጐበኘና እህል እንደ ሰጣቸው በሰማች ጊዜ፣ ሁለቱን ምራቶቿን ይዛ ወደ አገሯ ለመመለስ ከዚያ ተነሣች። 7የኖረችበትን ስፍራ ትታ ከሁለቱ ምራቶቿ ጋር ወደ ይሁዳ ምድር የሚመልሳቸውን መንገድ ይዘው ጕዟቸውን ቀጠሉ።
8ከዚያም ኑኃሚን ሁለቱን ምራቶቿን እንዲህ አለቻቸው፤ “እያንዳንዳችሁ ወደ እናቶቻችሁ ቤት ተመለሱ፤ ለሞቱ ባሎቻችሁና ለእኔ በጎ ነገር እንዳደረጋችሁ፣ ለእናንተም እግዚአብሔር እንደዚሁ ያድርግላችሁ፤ 9እያንዳንዳችሁ በምታገቡት ባል ቤት እግዚአብሔር ያሳርፋችሁ።” ከዚያም ሳመቻቸው፤ እነርሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ 10ቀጥለውም፣ “አይሆንም! ከአንቺ ጋር ተመልሰን ወደ ወገኖችሽ እንሄዳለን” አሏት።
11ኑኃሚን ግን እንዲህ አለቻቸው፤ “ልጆቼ ሆይ፤ ወደየቤታችሁ ተመለሱ፤ ከእኔ ጋር ለምን ትሄዳላችሁ? ባል የሚሆኗችሁ ሌሎች ልጆች ከእንግዲህ የምወልድ ይመስላችኋልን? 12ወደየቤታችሁ ተመለሱ፣ ልጆቼ፤ ሌላ ባል እንዳላገባ እጅግ አርጅቻለሁ፤ አሁንም ተስፋ አለኝ ብል፣ ዛሬ ማታ አግብቼ ከዚያም ልጆች ብወልድ፣ 13እስኪያድጉ ድረስ ትጠብቃላችሁን? እነርሱን በመጠበቅ እስከዚያ ሳታገቡ ትቈያላችሁን? ልጆቼ ሆይ፤ እንዲህ አይሆንም፤ ሁኔታው ከእናንተ ይልቅ ለእኔ እጅግ መራራ ነው፤ የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ተነሥቷልና።”
14እነርሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንደ ገና አለቀሱ፤ ከዚያም ዖርፋ ዐማቷን ስማ ተሰናበተቻት፤ ሩት ግን ልትለያት ስላልፈለገች ተጠመጠመችባት።
15ኑኃሚን መልሳ፣ “እነሆ የባልሽ ወንድም ሚስት ወደ ወገኖቿና ወደ አማልክቷ ተመልሳለች፤ አብረሻት ተመለሽ” አለቻት።
16ሩት ግን እንዲህ አለች፤ “ተለይቼሽ እንድቀር ወይም እንድመለስ አትለማመጭኝ፤ ወደምትሄጂበት እሄዳለሁ፤ በምትኖሪበትም እኖራለሁ፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽ አምላኬ ይሆናል። 17በምትሞቺበት እሞታለሁ፤ እዚያው እቀበራለሁ። ከእንግዲህ ሞት ከሚለየን በቀር ብለይሽ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ፤ ከዚህም የከፋ ያድርግብኝ።” 18ሩት አብራት ለመሄድ መቍረጧን በተረዳች ጊዜ፣ ኑኃሚን መጐትጐቷን ተወች።
19ከዚያም ሁለቱ ሴቶች እስከ ቤተ ልሔም ድረስ ተጓዙ፤ ቤተ ልሔም እንደ ደረሱም፣ በእነርሱ ምክንያት ከተማው በሙሉ ተተረማመሰ፤ ሴቶቹም፣ “ይህች ኑኃሚን ናትን?” በማለት ተገረሙ።
20እርሷም እንዲህ አለች፤ “ሁሉን የሚችል አምላክ#1፥20 በዚህና በቍጥር 21 ላይ ዕብራይስጡ፣ ሻዳይ ይላል። ሕይወቴን እጅግ መራራ አድርጎታልና ማራ#1፥20 ማራ ማለት መራራ ማለት ነው። በሉኝ እንጂ፣ ኑኃሚን#1፥20 በዚህና በቍጥር 21 ላይ፣ ኑኃሚን ማለት ደስተኛ ማለት ነው። ብላችሁ አትጥሩኝ። 21በሙላት ወጣሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ባዶዬን መለሰኝ፤ እግዚአብሔር አስጨንቆኝ#1፥21 ወይም እግዚአብሔር ፈትኖኝ፣ ሁሉን የሚችል አምላክ መከራ አምጥቶብኝ ሳለ እንዴት ኑኃሚን ብላችሁ ትጠሩኛላችሁ?” አለቻቸው።
22ስለዚህ ኑኃሚን ከምራቷ ከሞዓባዊቷ ሩት ጋር በመሆን ከሞዓብ ተመለሰች፤ ቤተ ልሔም የደረሱትም የገብስ አዝመራ በሚሰበሰብበት ወቅት መጀመሪያ ላይ ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.