ሮሜ 15:9-13
ሮሜ 15:9-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አሕዛብም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ ይቅር ብሎአቸዋልና፤ መጽሐፍ እንዲህ ብሎአልና፥ “አቤቱ፥ ስለዚህ በአሕዛብ መካከል እገዛልሃለሁ፤ ስምህንም አመሰግናለሁ።” ዳግመናም መጽሐፍ እንዲህ ብሎአል፥ “አሕዛብ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ።” ዳግመናም እንዲህ አለ፥ “አሕዛብ ሁላችሁ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ሕዝቡም ሁሉ ያመሰግኑታል።” ኢሳይያስም ደግሞ እንዲህ ብሎአል፥ “የእሴይ ዘር ይነሣል፤ ከእርሱ የሚነሣውም ለአሕዛብ ንጉሥ ይሆናል፤ ሕዝቡም ተስፋ ያደርጉታል።” የተስፋ አምላክ እግዚአብሔርም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል በተስፋ ያበዛችሁ ዘንድ በእምነት ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይፈጽምላችሁ።
ሮሜ 15:9-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንዲሁም አሕዛብ እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ ያመሰግኑት ዘንድ ነው፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ “ስለዚህ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ለስምህም እዘምራለሁ።” ደግሞም፣ “አሕዛብ ሆይ፤ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ” ይላል። እንደ ገናም፣ “አሕዛብም ሁላችሁ ጌታን አመስግኑ፤ ሕዝቦች ሁሉ ወድሱት” ይላል። ኢሳይያስም እንዲሁ፣ “በሕዝቦች ሁሉ ላይ የሚነግሠው፣ የእሴይ ሥር ይመጣል፤ በእርሱም አሕዛብ ተስፋ ያደርጋሉ” ይላል። በእርሱ በመታመናችሁ የተስፋ አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ፤ ይኸውም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተስፋ ተትረፍርፎ እንዲፈስስላችሁ ነው።
ሮሜ 15:8-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ለአባቶች የተሰጠውን የተስፋ ቃል ያጸና ዘንድ ደግሞም፦ ስለዚህ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ ለስምህም እዘምራለሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ አሕዛብ ስለ ምሕረቱ እግዚአብሔርን ያከብሩ ዘንድ፥ ክርስቶስ ስለ እግዚአብሔር እውነት የመገረዝ አገልጋይ ሆነ እላለሁ። ደግሞም፦ አሕዛብ ሆይ፥ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላል። ደግሞም፦ እናንተ አሕዛብ ሁላችሁ፥ ጌታን አመስግኑ ሕዝቦቹም ሁሉ ይወድሱት ይላል። ደግሞም ኢሳይያስ፦ የእሴይ ሥር አሕዛብንም ሊገዛ የሚነሣው ይሆናል፤ በእርሱ አሕዛብ ተስፋ ያደርጋሉ ይላል። የተስፋ አምላክም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በተስፋ እንድትበዙ በማመናችሁ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ።
ሮሜ 15:9-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ክርስቶስ የአይሁድ አገልጋይ የሆነበትም ሌላው ምክንያት አሕዛብ እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ እንዲያመሰግኑት ነው፤ ይህም፦ “ስለዚህ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ለስምህም በዝማሬ ምስጋና አቀርባለሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። ደግሞም፥ “እናንተ አሕዛብ፥ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ደስ ይበላችሁ!” ተብሎ ተጽፎአል። እንደገናም፦ “አሕዛብ ሁሉ! ጌታን አመስግኑት፤ ሕዝቦች ሁሉ አመስግኑት!” ተብሎ ተጽፎአል። እንዲሁም ኢሳይያስ፦ “ከእሴይ ዘር የሚወለድ ይመጣል፤ የአሕዛብም መሪ ለመሆን ይነሣል፤ እነርሱም ተስፋቸውን በእርሱ ላይ ያደርጋሉ” ይላል። ተስፋችሁ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል እያደገ እንዲሄድ የተስፋ አምላክ በእርሱ በመታመናችሁ ደስታንና ሰላምን በሙላት ይስጣችሁ።
ሮሜ 15:9-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አሕዛብ ስለ ምሕረቱ እግዚአብሔርን እንዲያከብሩት፥ “ስለዚህ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ለስምህም እዘምራለሁ፤” ተብሎ እንደተጻፈው ነው። እንደገናም “አሕዛብ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ፤” ይላል። እንደገናም “አሕዛብ ሁላችሁ! ጌታን አመስግኑ፤ ሕዝቦቹም ሁሉ ያመስግኑት፤” ደግሞም ኢሳይያስ “የእሴይ ሥር አሕዛብንም ሊገዛ የሚነሣው ይሆናል፤ በእርሱ አሕዛብ ተስፋ ያደርጋሉ፤” ይላል። በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በተስፋ እንደምትበዙ በማመናችሁ የተስፋ አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ።