ወደ ሮሜ ሰዎች 15
15
ራስን ሳይሆን ሰውን ማስደሰት
1እኛ ብርቱዎች የሆንን የደካሞችን ድካም መሸከም እንጂ ራሳችንን ማስደሰት የለብንም። 2እያንዳንዳችን እንድናንጸው እርሱን ለመጥቀም ባልንጀራችንን ደስ እናሰኝ። 3#መዝ. 69፥9።ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘምና፤ ነገር ግን “አንተን የነቀፉበት ነቀፋ ወደቀብኝ፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ ሆነበት። 4#1መቃ. 12፥9፤ 2መቃ. 15፥9።በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ነገሮች ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአል። 5የትዕግሥትና የመጽናናት አምላክ እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ እርስ በርሳችሁ በአንድ ሐሳብ መሆንን ይስጣችሁ። 6ይኸውም በአንድ ልብ ሆናችሁ በአንድ አፍ እግዚአብሔርን፥ እርሱም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት፥ እንድታከብሩ ነው።
7ስለዚህ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር እንደ ተቀበላችሁ እንዲሁ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ። 8ለአባቶች የተሰጠውን የተስፋ ቃል ሊያጸና፤ ስለ እግዚአብሔር እውነት ክርስቶስ ለተገረዙት አገልጋይ ሆነ እላለሁ፤ 9#2ሳሙ. 22፥50፤ መዝ. 18፥49።አሕዛብ ስለ ምሕረቱ እግዚአብሔርን እንዲያከብሩት፥ “ስለዚህ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ለስምህም እዘምራለሁ፤” ተብሎ እንደተጻፈው ነው። 10#ዘዳ. 32፥43።እንደገናም “አሕዛብ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ፤” ይላል። 11#መዝ. 117፥1።እንደገናም
“አሕዛብ ሁላችሁ! ጌታን አመስግኑ፤
ሕዝቦቹም ሁሉ ያመስግኑት፤”
12 #
ኢሳ. 11፥10። ደግሞም ኢሳይያስ
“የእሴይ ሥር አሕዛብንም ሊገዛ የሚነሣው ይሆናል፤
በእርሱ አሕዛብ ተስፋ ያደርጋሉ፤”
ይላል። 13በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በተስፋ እንደምትበዙ በማመናችሁ የተስፋ አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ።
የጳውሎስ የተልእኮ ተግባር
14ወንድሞቼ ሆይ! እኔም ራሴ ስለ እናንተ በበጎነት ራሳችሁ እንደ ተሞላችሁ፥ እውቀትም ሁሉ እንደ ሞላባችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ደግሞ ልትወቃቀሱ እንደምትችሉ ተረድቼአለሁ። 15ነገር ግን አንዳንድ ነገሮችን ላስታውሳችሁ ፈልጌ ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ጸጋ መሰረት በድፍረት ጻፍሁላችሁ። 16በእግዚአብሔር ወንጌል እንደ ካህን እያገለገልሁ፥ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ እንድሆን ነው፥ ይህም አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው የተወደደ መሥዋዕት እንዲሆኑ ነው። 17እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሆነ ነገር የምመካበት አለኝ። 18አሕዛብ እንዲታዘዙ ክርስቶስ በቃልና በሥራ፥ በእኔ አድርጎ ከሠራው በቀር ምንም ልናገር አልደፍርም፤ 19በምልክትና በድንቅ ሥራ ኃይል፥ በመንፈስ ቅዱስም ኃይል፥ ከኢየሩሳሌም ጀምሬ እስከ እልዋሪቆን ድረስ እየዞርሁ የክርስቶስን ወንጌል ፈጽሜ ሰብኬአለሁ። 20እንዲሁም በሌላው ሰው መሠረት ላይ አልሠራሁም፤ የክርስቶስ ስም ባልተጠራበት ስፍራ ወንጌልን ለመስበክ ተጋሁ፤ 21#ኢሳ. 52፥15።ነገር ግን
“ስለ እርሱ ያልተወራላቸው ያያሉ፤
ያልሰሙም ያስተውላሉ፤”
ተብሎ እንደተጻፈው ነው።
ጳውሎስ ሮምን ለመጎብኘት እንዳቀደ
22 #
ሮሜ 1፥13። ስለዚህ ደግሞ ወደ እናንተ እንዳልመጣ ብዙ ጊዜ ተከለከልሁ። 23አሁን ግን በዚህ አገር ስፍራ ከእንግዲህ ወዲያ የለኝም፥ ከብዙ ዓመታት ጀምሮም ወደ እናንተ ልመጣ ናፍቆት ስላለኝ፥ 24ወደ ስፔን በምሄድበት ጊዜ፥ ከእናንተ ጋር ተደስቼ ጥቂት ካሳላፍሁ በኋላ በጉዞዬ እንድትረዱኝ ሳልፍ ላያችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። 25#1ቆሮ. 16፥1-4።አሁን ግን ቅዱሳንን ለማገልገል ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ። 26መቄዶንያና አካይያ በኢየሩሳሌም ካሉት ቅዱሳን መካከል ያሉትን ድሆች ለመርዳት ወደዋል። 27#1ቆሮ. 9፥11።ተደስተዋልና የእነርሱ ባለ ዕዳዎች ናቸው፤ በእነርሱ መንፈሳዊ ነገር አሕዛብ ተካፋዮች ከሆኑ በሥጋዊ ነገር ደግሞ ሊያገለግሉአቸው ይገባቸዋል። 28ስለዚህ ይህን ፈጽሜ፥ ይህን ፍሬ ካተምሁላቸው በኋላ በእናንተ በኩል አድርጌ ወደ ስፔን እሄዳለሁ፤ 29ወደ እናንተም ስመጣ በክርስቶስ በረከት ሙላት እንደምመጣ አውቃለሁ።
30ወንድሞች ሆይ! ስለ እኔ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ ከእኔ ጋር እንድትጋደሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ፍቅር እለምናችኋለሁ፤ 31ይህም በይሁዳ ካሉት፥ ከማይታዘዙት እንድድን፥ ለኢየሩሳሌምም ያለኝ አገልግሎቴ በቅዱሳን ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው፥ 32በእግዚአብሔር ፈቃድ በደስታ ወደ እናንተ መጥቼ ከእናንተ ጋር እንዳርፍ ነው። 33የሰላም አምላክ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።
Currently Selected:
ወደ ሮሜ ሰዎች 15: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ