የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሮሜ 15:14-21

ሮሜ 15:14-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ወን​ድ​ሞች ሆይ፥ እኔም በጎ ምግ​ባ​ርን ሁሉ እን​ደ​ም​ት​ፈ​ጽሙ እታ​መ​ን​ባ​ች​ኋ​ለሁ፤ እና​ንተ ፍጹም ዕው​ቀ​ትን የተ​መ​ላ​ችሁ ናችሁ፤ ባል​ን​ጀ​ሮ​ቻ​ች​ሁ​ንም ልታ​ስ​ተ​ም​ሩ​አ​ቸው ትች​ላ​ላ​ችሁ። ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ስለ አገ​ኘ​ሁት ጸጋ ላሳ​ስ​ባ​ችሁ በአ​ን​ዳ​ንድ ቦታ በድ​ፍ​ረት ጻፍ​ሁ​ላ​ችሁ። በአ​ሕ​ዛብ መካ​ከል ኢየ​ሱስ ክር​ስ​ቶ​ስን አገ​ለ​ግል ዘንድ፥ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ወን​ጌ​ልም እገዛ ዘንድ፥ በእኔ ትም​ህ​ርት አሕ​ዛብ በመ​ን​ፈስ ቅዱስ የተ​ወ​ደ​ደና የተ​መ​ረጠ መሥ​ዋ​ዕት ይሆኑ ዘንድ። ለእ​ኔም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ መመ​ኪ​ያዬ ኢየ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ነው። አሕ​ዛ​ብም እን​ዲ​ያ​ምኑ ክር​ስ​ቶስ በቃ​ልም በሥ​ራም ያደ​ረ​ገ​ል​ኝን እና​ገር ዘንድ እደ​ፍ​ራ​ለሁ። በኀ​ይ​ልና በተ​አ​ም​ራት፥ በመ​ን​ፈስ ቅዱስ ኀይ​ልና ድንቅ ሥራን በመ​ሥ​ራ​ትም፥ ከኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም አው​ራ​ጃ​ዎች ጀምሬ እስከ እል​ዋ​ሪ​ቆን ድረስ እንደ አስ​ተ​ማ​ርሁ፥ የክ​ር​ስ​ቶ​ስ​ንም ወን​ጌል ፈጽሞ እንደ ሰበ​ክሁ እና​ገር ዘንድ እደ​ፍ​ራ​ለሁ። ወን​ጌ​ልን ለማ​ስ​ተ​ማር ተጋሁ፤ ነገር ግን በሌላ መሠ​ረት ላይ እን​ዳ​ላ​ንጽ የክ​ር​ስ​ቶስ ስም ወደ ተጠ​ራ​በት አል​ሄ​ድ​ሁም። “ወሬው ያል​ደ​ረ​ሳ​ቸው ያው​ቁ​ታል፤ ያል​ሰ​ሙ​ትም ያስ​ተ​ው​ሉ​ታል” ብሎ መጽ​ሐፍ እንደ ተና​ገረ ነው።

ሮሜ 15:14-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ወንድሞቼ ሆይ፤ እናንተ ራሳችሁ በበጎነት የተሞላችሁ፣ በዕውቀትም ሁሉ የተሞላችሁና አንዱ ሌላውን ለመምከር ችሎታ ያላችሁ መሆናችሁን እኔ ራሴ ርግጠኛ ሆኛለሁ። እግዚአብሔር በሰጠኝ ጸጋ መሠረት፣ እንደ ገና አሳስባችሁ ዘንድ በአንዳንድ ጕዳዮች ላይ በድፍረት የጻፍሁላችሁ፣ በእግዚአብሔር ወንጌል የክህነት ተግባር፣ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ ለመሆን ነው፤ ይኸውም አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት እንዲሆኑ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔርን በማገልገሌ በክርስቶስ ኢየሱስ እመካለሁ። በተናገርሁትና ባደረግሁት ነገር አሕዛብ ለእግዚአብሔር እንዲታዘዙ፣ ክርስቶስ በእኔ ሆኖ ከፈጸመው በቀር ሌላ ነገር ለመናገር አልደፍርም፤ ይህም የሆነው በመንፈስ ቅዱስ ኀይል፣ በምልክቶችና በታምራት ነበር። በዚህም ሁኔታ ከኢየሩሳሌም እስከ እልዋሪቆን ዙሪያ ድረስ የክርስቶስን ወንጌል ፈጽሜ ሰብኬአለሁ። ሌላው በጣለው መሠረት ላይ እንዳልገነባ ብዬ፣ ክርስቶስ ባልተጠራበት ስፍራ ወንጌልን መስበክ የዘወትር ምኞቴ ነበር። ይልቁንም፣ “ስለ እርሱ ያልተነገራቸው ያያሉ፤ ያልሰሙም ያስተውላሉ” ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።

ሮሜ 15:14-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እኔም ራሴ ደግሞ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በበጎነት ራሳችሁ እንደ ተሞላችሁ፥ እውቀትም ሁሉ እንደ ሞላባችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ደግሞ ልትገሠጹ እንዲቻላችሁ ስለ እናንተ ተረድቼአለሁ። ነገር ግን አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው የተወደደ መሥዋዕት ሊሆኑ፥ ለእግዚአብሔር ወንጌል እንደ ካህን እያገለገልሁ፥ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ እሆን ዘንድ ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ጸጋ ምክንያት ተመልሼ ላሳስባችሁ ብዬ በአንዳንድ ቦታ በድፍረት ጻፍሁላችሁ። እንግዲህ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሚሆን ነገር በክርስቶስ ኢየሱስ ትምክህት አለኝ። አሕዛብ እንዲታዘዙ ክርስቶስ በቃልና በሥራ፥ በምልክትና በድንቅ ነገር ኃይል፥ በመንፈስ ቅዱስም ኃይል በእኔ አድርጎ ከሠራው በቀር ምንም ልናገር አልደፍርም፤ ስለዚህ ከኢየሩሳሌም ጀምሬ እስከ እልዋሪቆን ድረስ እየዞርሁ የክርስቶስን ወንጌል ፈጽሜ፤ ሰብኬአለሁ። እንዲሁም በሌላው ሰው መሠረት ላይ እንዳልሠራ የክርስቶስ ስም በተጠራበት ስፍራ ሳይሆን ወንጌልን ለመስበክ ተጣጣርሁ፤ ነገር ግን፦ ስለ እርሱ ያልተወራላቸው ያያሉ፥ ያልሰሙም ያስተውላሉ ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።

ሮሜ 15:14-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ወንድሞቼ ሆይ! በደግነት የተሞላችሁ፥ በዕውቀት የበለጸጋችሁና እያንዳንዳችሁም ሌላውን ለመምከር የምትችሉ መሆናችሁን ተረድቼአለሁ። አንዳንድ ነገሮችን ላስታውሳችሁ ፈልጌ ይህን መልእክት እግዚአብሔር በሰጠኝ ጸጋ መሠረት በድፍረት ጻፍኩላችሁ። ይህም ጸጋ የተሰጠኝ የእግዚአብሔርን የምሥራች ቃል ለአሕዛብ በማብሠር እንደ ካህን ሆኜ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማገልገል ነው፤ ስለዚህ አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ የተቀደሰና እግዚአብሔርንም ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ሆነው እንዲቀርቡ አገለግላለሁ። በዚህ ምክንያት በኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርን ለማገልገል በመቻሌ እመካለሁ። አሕዛብ ታዛዦች እንዲሆኑ ለማድረግ ክርስቶስ በእኔ ቃልና ሥራ አማካይነት የሠራው ነገር ካልሆነ በቀር ምንም ነገር ለመናገር አልደፍርም። እንዲሁም በታላላቅ ተአምራትና በድንቅ ሥራዎች፥ በመንፈስ ቅዱስም ኀይል ከኢየሩሳሌምና ከአካባቢዋ ጀምሮ እስከ እልዋሪቆን ድረስ የክርስቶስን ወንጌል አስተምሬአለሁ። የዘወትር ምኞቴም ሌላው ሰው በጣለው መሠረት ላይ መገንባት ሳይሆን የክርስቶስ ስም ባልተሰማበት ስፍራ ሁሉ መልካሙን ዜና ማብሠር ነው። ይህም፦ “ከዚህ በፊት ስለ እርሱ ምንም ያልተነገራቸው ሰዎች ያያሉ፤ ስለ እርሱ ያልሰሙም ያስተውላሉ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።

ሮሜ 15:14-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ወንድሞቼ ሆይ! እኔም ራሴ ስለ እናንተ በበጎነት ራሳችሁ እንደ ተሞላችሁ፥ እውቀትም ሁሉ እንደ ሞላባችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ደግሞ ልትወቃቀሱ እንደምትችሉ ተረድቼአለሁ። ነገር ግን አንዳንድ ነገሮችን ላስታውሳችሁ ፈልጌ ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ጸጋ መሰረት በድፍረት ጻፍሁላችሁ። በእግዚአብሔር ወንጌል እንደ ካህን እያገለገልሁ፥ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ እንድሆን ነው፥ ይህም አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው የተወደደ መሥዋዕት እንዲሆኑ ነው። እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሆነ ነገር የምመካበት አለኝ። አሕዛብ እንዲታዘዙ ክርስቶስ በቃልና በሥራ፥ በእኔ አድርጎ ከሠራው በቀር ምንም ልናገር አልደፍርም፤ በምልክትና በድንቅ ሥራ ኃይል፥ በመንፈስ ቅዱስም ኃይል፥ ከኢየሩሳሌም ጀምሬ እስከ እልዋሪቆን ድረስ እየዞርሁ የክርስቶስን ወንጌል ፈጽሜ ሰብኬአለሁ። እንዲሁም በሌላው ሰው መሠረት ላይ አልሠራሁም፤ የክርስቶስ ስም ባልተጠራበት ስፍራ ወንጌልን ለመስበክ ተጋሁ፤ ነገር ግን “ስለ እርሱ ያልተወራላቸው ያያሉ፤ ያልሰሙም ያስተውላሉ፤” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።