ሮሜ 15:1-7
ሮሜ 15:1-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የሚገባስ እና ብርቱዎች ደካሞችን በድካማቸው እንድንረዳቸው ነው፤ ለራሳችንም አናድላ። ሁላችንም በእውነትና በመልካም ሥራ ይታነጽ ዘንድ ለባልንጀራችን እናድላ። ክርስቶስም፥ “አንተን የነቀፉበት ነቀፋ በእኔ ላይ ደረሰ” ብሎ መጽሐፍ እንደ ተናገረ ለራሱ ያደላ አይደለም። የተጻፈው ሁሉ በመታገሣችንና መጻሕፍትን በመታመናችን ተስፋችንን እናገኝ ዘንድ እና ልንማርበት ተጻፈ። የትዕግሥትና የመጽናናት አምላክ እግዚአብሔር እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ እርስ በርሳችን አንድ ዐሳብ መሆንን ይስጠን። ሁላችን አንድ ሆነን በአንድ አፍ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርን እናመሰግነው ዘንድ። አሁንም ባልንጀሮቻችሁን ተቀበሉ፤ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር ተቀብሎአችኋልና።
ሮሜ 15:1-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እኛ ብርቱዎች የሆንን፣ የደካሞችን ጕድለት መሸከም እንጂ ራሳችንን ማስደሰት የለብንም። እያንዳንዳችን ባልንጀራችንን ለማነጽ፣ እርሱንም ለመጥቀም ደስ የሚያሰኘውን ነገር ማድረግ ይገባናል። ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘምና፤ ነገር ግን፣ “አንተን የሰደቡበት ስድብ በእኔ ላይ ደረሰብኝ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ሆነበት። በጽናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፏልና። ብርታትንና መጽናናትን የሚሰጥ አምላክ፣ ክርስቶስ ኢየሱስን ስትከተሉ፣ በመካከላችሁ የአንድነትን መንፈስ ይስጣችሁ፤ ይኸውም በአንድ ልብና በአንድ አፍ ሆናችሁ፣ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክና አባት ታከብሩ ዘንድ ነው። እንግዲህ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሆን ዘንድ ክርስቶስ እንደ ተቀበላችሁ፣ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ።
ሮሜ 15:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እኛም ኃይለኞች የሆንን የደካሞችን ድካም እንድንሸከም ራሳችንንም ደስ እንዳናሰኝ ይገባናል። እያንዳንዳችን እንድናንጸው እርሱን ለመጥቀም ባልንጀራችንን ደስ እናሰኝ። ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘምና፤ ነገር ግን፦ አንተን የነቀፉበት ነቀፋ ወደቀብኝ ተብሎ እንደ ተጻፈ ሆነበት። በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና። በአንድ ልብ ሆናችሁ በአንድ አፍ እግዚአብሔርን፥ እርሱም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት፥ ታከብሩ ዘንድ፥ የትዕግሥትና የመጽናናት አምላክ እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ፈቃድ እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ መሆንን ይስጣችሁ። ስለዚህ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር እንደ ተቀበላችሁ እንዲሁ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ።
ሮሜ 15:1-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እኛ በእምነት ብርቱዎች የሆንን፥ የደካሞችን ድካም መሸከም ይገባናል እንጂ ራሳችንን ብቻ የምናስደስት መሆን የለብንም፤ እያንዳንዳችን ሌላው ሰው በእምነቱ እንዲጠነክር እርሱን የሚጠቅመውንና የሚያስደስተውን ነገር እናድርግ። ክርስቶስ ራሱን አላስደሰተም፤ ይልቁንም “ሰዎች አንተን የሰደቡበት ስድብ በእኔ ላይ ወረደ” የሚለው የቅዱሳት መጻሕፍት አባባል ደረሰበት። ከቅዱሳት መጻሕፍት በምናገኛቸው ትዕግሥትና መጽናናት ተስፋ ይኖረን ዘንድ ቀደም ብለው የተጻፉት ሁሉ ትምህርት እንዲሆኑን ተጽፈዋል። የትዕግሥትና የመጽናናት አምላክ እርስ በርሳችሁ የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመከተል አብሮ የመኖርን ኅብረት ይስጣችሁ። እንዲሁም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር በአንድ ልብና በአንድ ቃል እንድታከብሩት ያድርጋችሁ። ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር እናንተን እንደ ተቀበላችሁ እናንተ ሁላችሁም አንዱ ሌላውን በደስታ ይቀበለው።
ሮሜ 15:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እኛ ብርቱዎች የሆንን የደካሞችን ድካም መሸከም እንጂ ራሳችንን ማስደሰት የለብንም። እያንዳንዳችን እንድናንጸው እርሱን ለመጥቀም ባልንጀራችንን ደስ እናሰኝ። ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘምና፤ ነገር ግን “አንተን የነቀፉበት ነቀፋ ወደቀብኝ፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ ሆነበት። በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ነገሮች ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአል። የትዕግሥትና የመጽናናት አምላክ እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ እርስ በርሳችሁ በአንድ ሐሳብ መሆንን ይስጣችሁ። ይኸውም በአንድ ልብ ሆናችሁ በአንድ አፍ እግዚአብሔርን፥ እርሱም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት፥ እንድታከብሩ ነው። ስለዚህ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር እንደ ተቀበላችሁ እንዲሁ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ።