ሮሜ 12:16-21
ሮሜ 12:16-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እርስ በርሳችሁም በአንድ ዐሳብ ተስማሙ፤ ትዕቢትን ግን አታስቡ፤ ራሱን የሚያዋርደውንም ሰው ምሰሉ፤ እና ዐዋቆች ነን አትበሉ። ክፉ ላደረገባችሁም ክፉ አትመልሱለት፤ በሰው ሁሉ ፊት በጎውን ተነጋገሩ። ቢቻላችሁስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ወንድሞቻችን፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ቍጣን አሳልፏት፥ “እኔ እበቀላለሁ፤ እኔ ብድራትን እከፍላለሁ ይላል እግዚአብሔር” ተብሎ ተጽፎአልና። ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማም አጠጣው፤ ይህን ብታደርግ የእሳት ፍሕም በራሱ ላይ ትከምራለህ። ክፉውን በመልካም ሥራ ድል ንሣው እንጂ ክፉውን በክፉ ድል አትንሣው።
ሮሜ 12:16-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እርስ በርሳችሁ በአንድ ሐሳብ በመስማማት ኑሩ። ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ካሉ ጋራ ዐብራችሁ ለመሆን ፍቀዱ እንጂ አትኵራሩ፤ በራሳችሁም አትመኩ። ለማንም ክፉን በክፉ አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት በጎ የሆነውን ነገር ለማድረግ ትጉ። ቢቻላችሁስ በበኩላችሁ ከሰው ሁሉ ጋራ በሰላም ኑሩ። ወዳጆቼ ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ቍጣ ፈንታ ስጡ እንጂ አትበቀሉ፤ ጌታ “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” እንዳለ ተጽፏልና። ይልቁንስ፣ “ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማም አጠጣው። ይህን በማድረግህም የእሳት ፍም በራሱ ላይ ትከምራለህ።” ክፉን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።
ሮሜ 12:16-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ። ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ጠላትህ ግን ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግህ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና። ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።
ሮሜ 12:16-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማምታችሁ ኑሩ፤ ራሳችሁን ከፍ ከማድረግ ይልቅ ትዕቢትን አስወግዳችሁ ከድኾች ጋር በአንድነት ኑሩ፤ በራሳችሁ ዐዋቂዎች ነን አትበሉ። በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን ነገር አድርጉ እንጂ፥ ሰዎች ክፉ ነገር ሲያደርጉባችሁ፥ እናንተም መልሳችሁ ክፉ ነገር አታድርጉባቸው። የሚቻላችሁ ቢሆን ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የሚያስፈልገውን ሁሉ አድርጉ። ወዳጆቼ ሆይ! ቊጣን ለእግዚአብሔር ተዉ እንጂ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ “የምበቀልና የበቀልንም ብድራት የምከፍል እኔ ነኝ ይላል ጌታ እግዚአብሔር” ተብሎ ተጽፎአል። ስለዚህ ከመበቀል ይልቅ ጠላትህን ቢርበው አብላው፤ ቢጠማውም አጠጣው፤ ይህን ብታደርግ በዕፍረት እሳት ታቃጥለዋለህ። ስለዚህ ክፉውን ነገር በመልካም ነገር አሸንፍ እንጂ በክፉ ነገር አትሸነፍ።
ሮሜ 12:16-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እርስ በርሳችሁ በአንድ ነገር ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፤ ነገር ግን የተናቁትን ቅረቡ። በራሳችሁ ዐዋቂዎች ነን አትበሉ። ለማንም በክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን ነገር አስቡ። ቢቻላችሁ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ፤ ይላል ጌታ” ተብሎ ተጽፎአልና፥ ተወዳጆች ሆይ! ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ለቁጣው ቦታ ስጡ እንጂ። ነገር ግን ጠላትህ ቢርበው አብላው፤ ቢጠማው አጠጣው፤ ይህን በማድረግህ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና። ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።