ሮሜ 11:7-12
ሮሜ 11:7-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንግዲህ ምንድን ነው? እስራኤል የፈለገውን አላገኘም። የተመረጠው ግን አግኝቶአል፤ የቀሩትም ታወሩ። መጽሐፍ እንዳለ፥ “እስከ ዛሬ ድረስ በዐይናቸው እንዳያዩ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ እግዚአብሔር ደንዛዛ አእምሮን ሰጣቸው።” ዳዊትም እንዲህ ብሎአል፥ “ማዕዳቸው በፊታቸው ወጥመድና አሽክላ፥ መሰናከያና ፍዳም ትሁንባቸው። እንዳያዩ ዐይኖቻቸው ይጨልሙ፤ ዘወትርም ጀርባቸው ይጕበጥ።” እንግዲህ እላለሁ፤ ሊወድቁ ተሰናከሉን? አይደለም፤ ነገር ግን እስራኤል ይቀኑ ዘንድ እነርሱ በመሰናከላቸው ለአሕዛብ ድኅነት ሆነ። የእነርሱ መሰናከል ለዓለም ባለጸግነት፥ በደላቸውም ለአሕዛብ ባለጸግነት ከሆነ ፍጹምነታቸውማ እንዴት በሆነ ነበር?
ሮሜ 11:7-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንግዲህ ምንድን ነው? እስራኤል አጥብቀው የፈለጉትን አላገኙትም፤ የተመረጡት ግን አገኙት፤ የቀሩትም ልባቸው ደነደነ፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ “ዐይናቸው እንዳያይ፣ ጆሯቸውም እንዳይሰማ፣ እግዚአብሔር እስከዚህ ቀን ድረስ፣ የድንዛዜ መንፈስ ሰጣቸው።” ዳዊትም አለ፤ “ማእዳቸው ወጥመድና ማሰናከያ፣ ዕንቅፋትና ቅጣት ይሁንባቸው። ዐይኖቻቸው እንዳያዩ ይጨልሙ፤ ወገባቸውም ለዘላለም ይጕበጥ።” ተመልሰው እስከማይድኑ ድረስ ተሰናከሉን? ብዬ እንደ ገና እጠይቃለሁ፤ ከቶ አይሆንም! ይልቁንም እስራኤልን ለማስቀናት ሲባል በእነርሱ መተላለፍ ምክንያት ድነት ለአሕዛብ መጥቷል። ነገር ግን የእነርሱ መተላለፍ ለዓለም በረከት ከሆነ፣ ውድቀታቸውም ለአሕዛብ በረከት ከሆነ፣ ሙላታቸው ምን ያህል ታላቅ በረከት ያመጣ ይሆን?
ሮሜ 11:7-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንግዲህ ምንድር ነው? እስራኤል የሚፈልጉትን አላገኙትም፤ የተመረጡት ግን አገኙት፤ ሌሎቹም ደነዘዙ፤ እንዲሁም፦ ዓይኖቻቸው እንዳያዩ ጆሮቻቸውም እንዳይሰሙ እግዚአብሔር የእንቅልፍ መንፈስን እስከ ዛሬ ድረስ ሰጣቸው ተብሎ ተጽፎአል። ዳዊትም፦ ማዕዳቸው ወጥመድና አሽክላ ማሰናከያም ፍዳም ይሁንባቸው፤ ዓይኖቻቸው እንዳያዩ ይጨልሙ፥ ጀርባቸውንም ዘወትር አጉብጥ ብሎአል። እንግዲህ፦ የተሰናከሉ እስኪወድቁ ድረስ ነውን? እላለሁ። አይደለም፤ ነገር ግን እነርሱን ያስቀናቸው ዘንድ በእነርሱ በደል መዳን ለአሕዛብ ሆነ። ዳሩ ግን በደላቸው ለዓለም ባለ ጠግነት መሸነፋቸውም ለአሕዛብ ባለ ጠግነት ከሆነ፥ ይልቁንስ መሙላታቸው እንዴት ይሆን?
ሮሜ 11:7-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ታዲያ፥ ውጤቱ ምን ሆነ? እስራኤላውያን የፈለጉትን አላገኙም፤ የተመረጡት ግን የፈለጉትን አገኙ፤ የቀሩት ልባቸውን አደነደኑ። ይህም “እግዚአብሔር ልቡናቸውን አደነዘዘ፤ ስለዚህ እስከ ዛሬ ድረስ በዐይናቸው አያዩም፤ በጆሮአቸውም አይሰሙም” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። ዳዊትም፦ “ማእዳቸው የሚይዝ ወጥመድ፥ የሚጥል ጒድጓድ ሆኖ ያሠቃያቸው! ያደረጉት ክፋት በራሳቸው ላይ ይድረስ! ዐይናቸው እንዳያይ ይጨልም፤ ወገባቸውም በችግር ሁልጊዜ ይጒበጥ” ብሎአል። እስቲ፥ እንደገና ልጠይቅ፤ አይሁድ የወደቁት ዳግመኛ እንደማይነሡ ሆነው ነውን? አይደለም! በአይሁድ በደል ምክንያት አሕዛብ መዳንን አገኙ፤ ይህም የሆነው አይሁድ በአሕዛብ እንዲቀኑ ለማድረግ ነው። የአይሁድ በደል ለዓለም ብዙ በረከት አስገኝቶአል፤ የእነርሱም ውድቀት ለአሕዛብ በረከት ሆኖአል፤ አይሁድ ቢድኑማ ኖሮ በረከቱ ምን ያኽል ብዙ በሆነ ነበር!
ሮሜ 11:7-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንግዲህ ምንድነው? እስራኤል የሚፈልጉትን አላገኙትም፤ የተመረጡት ግን አገኙት፤ የቀሩትም ደነዘዙ፤ ይህም “ዐይኖቻቸው እንዳያዩ፥ ጆሮቻቸውም እንዳይሰሙ፥ እግዚአብሔር ከባድ የእንቅልፍን መንፈስ እስከ ዛሬ ድረስ ሰጣቸው፤” ተብሎ ተጽፎአል። ዳዊትም፥ ማዕዳቸው ወጥመድና አሽክላ ማሰናከያም ፍዳም ይሁንባቸው፤ እንዳያዩ ዐይኖቻቸው ይጨልሙ፤ ጀርባቸውም ሁልጊዜ ይጉበጥ ብሏል። ተመልሰው መዳን እስከማይችሉ ድረስ ተሰናከሉን? ብዬ እጠይቃለሁ፤ በጭራሽ! ነገር ግን እነርሱን ለማስቀናት፥ በእነርሱ በደል፥ መዳን ለአሕዛብ ሆነ። ነገር ግን በደላቸው ለዓለም ባለጠግነት ውድቀታቸውም ለአሕዛብ ባለጠግነት ከሆነ፥ ይልቁንስ መሙላታቸው እንዴት ይሆን?