ሮሜ 10:1-17
ሮሜ 10:1-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወንድሞች፥ የእኔስ የልቤ ምኞት፥ ወደ እግዚአብሔር የማቀርበው ጸሎትም እስራኤል እንዲድኑ ነው። ለእግዚአብሔር እንዲቀኑ ምስክራቸው እኔ ነኝና፤ ነገር ግን ዐውቀው አይደለም። የእግዚአብሔርን ጽድቅ አያውቁአትምና በራሳቸውም ጽድቅ ጸንተው ሊኖሩ ወደዱ፤ ለእግዚአብሔር ጽድቅ ግን መገዛት ተሳናቸው። የኦሪት ጽድቅ ፍጻሜስ ለሚያምኑበት ሁሉ በክርስቶስ ማመን ነው። ሙሴም “የኦሪትን ጽድቅ መሥራትን የፈጸመ ሁሉ በእርሱ ይጸድቅበታል” አለ። የእምነት ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል፥ “በልብህ ወደ ሰማይ ማን ይወጣል?” አትበል፤ ከሰማይ የወረደው ክርስቶስ ነው። “ወደ ጥልቁም ማን ይወርዳል?” አትበል፤ ከሙታን ተለይቶ የተነሣው ክርስቶስ ነው። መጽሐፍ እንዲሁ፥ “ቃል ለልብህም ለአፍህም ቀርቦልሃል ይል የለምን?” ይህም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው። ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን ለይቶ እንደ አስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህ። በልቡ የሚያምን ይጸድቃልና፤ በአፉም የሚመሰክር ይድናልና። መጽሐፍ፥ “የሚያምንበት ሁሉ አያፍርም” ብሎአል። አይሁዳዊንና አረማዊን አልለየም፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ እግዚአብሔር ባለጸጋ ስለሆነ ለለመነው ሁሉ ይበቃልና። “የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።” ነገር ግን ያላመኑበትን እንዴት ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ? “መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው?” ተብሎ እንደ ተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ? ነገር ግን ሁሉም የወንጌልን ትምህርት የሰሙ አይደለም፤ ኢሳይያስም፥ “አቤቱ፥ ምስክርነታችንንስ ማን አመነ? የእግዚአብሔርስ ክንዱ ለማን ተገለጠ?” ብሎአልና። ማመን ከመስማት ነው፤ መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።
ሮሜ 10:1-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ወንድሞች ሆይ፤ ስለ እስራኤላውያን የልቤ ምኞት፣ እግዚአብሔርንም የምለምነው እንዲድኑ ነው። ለእግዚአብሔር ቀናተኞች እንደ ሆኑ ስለ እነርሱ መመስከር እችላለሁና፤ ቅናታቸው ግን ከዕውቀት የተነሣ አይደለም። ከእግዚአብሔር የሚመጣውን ጽድቅ ስላላወቁና የራሳቸውን ጽድቅ ለመመሥረት ስለ ፈለጉ፣ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም። ለሚያምን ሁሉ ጽድቅ ይሆን ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና። ሙሴ በሕግ በኩል የሆነውን ጽድቅ ሲገልጽ፣ “እነዚህን የሚፈጽም ሰው በእነርሱ ይኖራል” ይላል። ከእምነት የሆነው ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል፤ “ ‘በልብህ ማን ወደ ሰማይ ይወጣል?’ አትበል”፤ ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ “ወይም ‘ወደ ጥልቁስ ማን ይወርዳል?’ አትበል”፤ ይህም ክርስቶስን ከሙታን ለማውጣት ነው። ነገር ግን ምን ይላል? “ቃሉ በአጠገብህ ነው፤ በአፍህና በልብህም ውስጥ ነው፤” የምንሰብከውም የእምነት ቃል ይህ ነው፤ “ኢየሱስ ጌታ ነው” ብለህ በአፍህ ብትመሰክር፣ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን፣ ትድናለህ። የምትጸድቀው በልብህ አምነህ ነው፤ የምትድነውም በአፍህ መስክረህ ነውና። መጽሐፍ እንደሚለው፣ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም።” በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ልዩነት የለም፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፤ የሚለምኑትንም አብዝቶ ይባርካል፤ “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።” ታዲያ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ስለ እርሱስ ሳይሰሙ እንዴት ያምኑበታል? ሰባኪ ሳይኖር እንዴት መስማት ይችላሉ? ካልተላኩስ እንዴት መስበክ ይችላሉ? ይህም፣ “የምሥራችን የሚያመጡ እግሮች እንዴት ያማሩ ናቸው!” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። ነገር ግን የሰሙት ሁሉ የምሥራቹን ቃል አልተቀበሉም፤ ኢሳይያስም፣ “ጌታ ሆይ፤ መልእክታችንን ማን አምኗል?” ብሏልና። እንግዲያስ እምነት የሚገኘው መልእክቱን ከመስማት ነው፤ መልእክቱም በክርስቶስ ቃል ነው።
ሮሜ 10:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ወንድሞች ሆይ፥ የልቤ በጎ ፈቃድና ስለ እስራኤል ወደ እግዚአብሔር ልመናዬ እንዲድኑ ነው። በእውቀት አይቅኑ እንጂ ለእግዚአብሔር እንዲቀኑ እመሰክርላቸዋለሁና። የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውንም ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ፥ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም። የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና። ሙሴ ከሕግ የሆነውን ጽድቅ የሚያደርገው ሰው በእርሱ በሕይወት እንዲኖር ጽፎአልና። ከእምነት የሆነ ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል፦ በልብህ፦ ማን ወደ ሰማይ ይወጣል? አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ ወይም፦ በልብህ፦ ወደ ጥልቁ ማን ይወርዳል? አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ከሙታን ለማውጣት ነው። ነገር ግን ምን ይላል? በአፍህ በልብህም ሆኖ ቃሉ ቀርቦልሃል፤ ይህም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው። ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና። መጽሐፍ፦ በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም ይላልና። በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና። እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ? መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ? ነገር ግን ሁሉ ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ኢሳይያስ፦ ጌታ ሆይ፥ ምስክርነታችንን ማን አመነ? ብሎአልና። እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።
ሮሜ 10:1-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ወንድሞቼ ሆይ! በልቤ ያለው ታላቅ ምኞትና ወደ እግዚአብሔር የማቀርበው ጸሎት እስራኤላውያን እንዲድኑ ነው። በትክክለኛ ዕውቀት አለመሆኑ ነው እንጂ እነርሱ ለእግዚአብሔር መንፈሳዊ ቅናት እንዳላቸው እኔ ራሴ እመሰክርላቸዋለሁ። እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያጸድቅበትን መንገድ ባለማወቃቸው የራሳቸውን የጽድቅ መንገድ ተከተሉ እንጂ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አልተከተሉም። ሰው ሁሉ በእምነት እንዲጸድቅ ሕግ በክርስቶስ አክትሞአል። ሕግን በመከተል ስለሚገኘው ጽድቅ ሙሴ የጻፈው “ሕግን የሚፈጽም ሁሉ በሕይወት ይኖራል” የሚል ነው። እግዚአብሔር ሰዎችን በእምነት ስለ ማጽደቁ ግን እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤ “በልብህ ወደ ሰማይ ማን ይወጣል?” አትበል፤ ይህም ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ ወይም በልብህ “ወደ ሲኦል ማን ይወርዳል?” አትበል፤ ይህም ክርስቶስን ከሞት ለማስነሣት ነው። ደግሞም እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፦ “የእግዚአብሔር ቃል አጠገብህ ነው፤ እንዲያውም በአፍህና በልብህ ነው፤” ይህም ቃል እኛ የምናበሥረው የእምነት ቃል ነው። ኢየሱስ ጌታ መሆኑን በአፍህ ብትመሰክርና እግዚአብሔር ከሞት እንዳስነሣውም በልብህ ብታምን ትድናለህ። ሰው በልቡ ሲያምን ይጸድቃል፤ በአፉም ሲመሰክር ይድናል፤ በቅዱስ መጽሐፍ እንደ ተጻፈው፦ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም።” እንግዲህ አንዱ ጌታ የሁሉም ጌታ ስለ ሆነ በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ምንም ልዩነት የለም፤ እርሱም ለሚለምኑት ሁሉ በረከቱን አብዝቶ ይሰጣል፤ “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ተብሎአልና። ነገር ግን ሳያምኑበት እንዴት ሊጠሩት ይችላሉ? ስለ እርሱ ሳይሰሙስ እንዴት ያምናሉ? ያለ አስተማሪስ እንዴት ሊሰሙ ይችላሉ? አስተማሪዎች ካልተላኩስ እንዴት ቃሉን ሊያስተምሩ ይችላሉ? ይህም “የመልካም ዜና አብሣሪዎች መምጣት እንዴት ደስ ያሰኛል!” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። ነገር ግን ኢሳይያስ፥ “ጌታ ሆይ! የተናገርነውን ቃል ማን ተቀበለ” ብሎ እንደ ተናገረ፥ ሁሉም የምሥራቹን ቃል አልተቀበሉም። ስለዚህ እምነት የሚገኘው የምሥራቹን ቃል ከመስማት ነው፤ የምሥራቹም ቃል የሚገኘው ስለ ክርስቶስ ከሚነገረው ትምህርት ነው።
ሮሜ 10:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወንድሞች ሆይ! የልቤ መልካም ምኞትና እግዚአብሔርንም የምለምነው እስራኤላውያን እንዲድኑ ነው። ለእግዚአብሔር ቅንዓት እንዳላቸው እመሰክርላቸዋለሁ ነገር ግን ቅንአታቸው በእውቀት ላይ የተመሠረተ አይደለም። የእግዚአብሔርን ጽድቅ ባለማወቅ፥ የራሳቸውንም ጽድቅ ለመመሥረት በመፈለግ፥ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም። የሚያምን ሁሉ እንዲጸድቅ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና። ሙሴ በሕግ ስለ ሆነው ጽድቅ ሲጽፍ “እነዚህን የሚፈጽም ሰው በእነርሱ ይኖራል” ይላል። ከእምነት የሆነው ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል፥ “በልብህ ‘ወደ ሰማይ ማን ይወጣል?’ አትበል፤” ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ ወይም “በልብህ ‘ወደ ጥልቁስ ማን ይወርዳል?’ አትበል፤” ይህም ክርስቶስን ከሙታን ለማስነሣት ነው። ነገር ግን ምን ይላል? ቃሉ በአጠገብህ ነው፤ በአፍህና በልብህም ነው፤ የምንሰብከው የእምነት ቃል ይህ ነው። ምክንያቱም ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ በአፍህ ብትመሰክር፥ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህ፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃል፥ በአፉም መስክሮ ይድናልና። መጽሐፍ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም” ይላልና። በአይሁዳዊና በግሪካዊ መካከል ልዩነት የለምና፤ ያው ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤ “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።” ታዲያ ያላመኑበትን እንዴት ይጠሩታል? ያልሰሙትንስ እንዴት ያምኑታል? ያለ ሰባኪስ እንዴት ሊሰሙ ይችላሉ? ካልተላኩስ እንዴት ይሰብካሉ? “መልካሙን ዜና የሚያበሥሩ እግሮቻቸው እንዴት ውብ ናቸው!” ተብሎ እንደተጻፈው ነው። ነገር ግን ሁሉም ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ኢሳይያስ “ጌታ ሆይ! የተናገርነውን ማን አመነ?” ብሏልና። ስለዚህ እምነት የሚመጣው ከመስማት ነው፤ መስማትም በክርስቶስ ቃል በኩል ነው።