የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ሮም ሰዎች 10:1-17

ወደ ሮም ሰዎች 10:1-17 አማ05

ወንድሞቼ ሆይ! በልቤ ያለው ታላቅ ምኞትና ወደ እግዚአብሔር የማቀርበው ጸሎት እስራኤላውያን እንዲድኑ ነው። በትክክለኛ ዕውቀት አለመሆኑ ነው እንጂ እነርሱ ለእግዚአብሔር መንፈሳዊ ቅናት እንዳላቸው እኔ ራሴ እመሰክርላቸዋለሁ። እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያጸድቅበትን መንገድ ባለማወቃቸው የራሳቸውን የጽድቅ መንገድ ተከተሉ እንጂ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አልተከተሉም። ሰው ሁሉ በእምነት እንዲጸድቅ ሕግ በክርስቶስ አክትሞአል። ሕግን በመከተል ስለሚገኘው ጽድቅ ሙሴ የጻፈው “ሕግን የሚፈጽም ሁሉ በሕይወት ይኖራል” የሚል ነው። እግዚአብሔር ሰዎችን በእምነት ስለ ማጽደቁ ግን እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤ “በልብህ ወደ ሰማይ ማን ይወጣል?” አትበል፤ ይህም ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ ወይም በልብህ “ወደ ሲኦል ማን ይወርዳል?” አትበል፤ ይህም ክርስቶስን ከሞት ለማስነሣት ነው። ደግሞም እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፦ “የእግዚአብሔር ቃል አጠገብህ ነው፤ እንዲያውም በአፍህና በልብህ ነው፤” ይህም ቃል እኛ የምናበሥረው የእምነት ቃል ነው። ኢየሱስ ጌታ መሆኑን በአፍህ ብትመሰክርና እግዚአብሔር ከሞት እንዳስነሣውም በልብህ ብታምን ትድናለህ። ሰው በልቡ ሲያምን ይጸድቃል፤ በአፉም ሲመሰክር ይድናል፤ በቅዱስ መጽሐፍ እንደ ተጻፈው፦ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም።” እንግዲህ አንዱ ጌታ የሁሉም ጌታ ስለ ሆነ በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ምንም ልዩነት የለም፤ እርሱም ለሚለምኑት ሁሉ በረከቱን አብዝቶ ይሰጣል፤ “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ተብሎአልና። ነገር ግን ሳያምኑበት እንዴት ሊጠሩት ይችላሉ? ስለ እርሱ ሳይሰሙስ እንዴት ያምናሉ? ያለ አስተማሪስ እንዴት ሊሰሙ ይችላሉ? አስተማሪዎች ካልተላኩስ እንዴት ቃሉን ሊያስተምሩ ይችላሉ? ይህም “የመልካም ዜና አብሣሪዎች መምጣት እንዴት ደስ ያሰኛል!” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። ነገር ግን ኢሳይያስ፥ “ጌታ ሆይ! የተናገርነውን ቃል ማን ተቀበለ” ብሎ እንደ ተናገረ፥ ሁሉም የምሥራቹን ቃል አልተቀበሉም። ስለዚህ እምነት የሚገኘው የምሥራቹን ቃል ከመስማት ነው፤ የምሥራቹም ቃል የሚገኘው ስለ ክርስቶስ ከሚነገረው ትምህርት ነው።