የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ራእይ 13:1-10

ራእይ 13:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ዘንዶውም በባሕሩ ዳር ቆሞ ነበር። ከዚያም አንድ አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ እርሱም ዐሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፤ በቀንዶቹም ላይ ዐሥር ዘውዶች፣ በራሶቹም ላይ የስድብ ስሞች ነበሩት። ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፤ ነገር ግን እግሮቹ የድብ፣ አፉ ደግሞ የአንበሳ አፍ ይመስል ነበር፤ ዘንዶው የራሱን ኀይልና የራሱን ዙፋን እንዲሁም ታላቅ ሥልጣን ለአውሬው ሰጠው። ከአውሬው ራሶች አንዱ ለሞት የሚያደርስ ቍስል ያለበት ይመስል ነበር። ነገር ግን ለሞት የሚያደርሰው ቍስሉ ዳነ፤ ዓለም በሙሉ በመደነቅ አውሬውን ተከተለው። ሰዎችም ለዘንዶው ሰገዱለት፤ ምክንያቱም ሥልጣኑን ለአውሬው ሰጥቶታል። ደግሞም፣ “አውሬውን የሚመስል ማን ነው? ከእርሱስ ጋር ማን ሊዋጋ ይችላል?” በማለት ለአውሬው ሰገዱለት። አውሬው የትዕቢት ቃል የሚናገርበትና የሚሳደብበት አፍ ተሰጠው፤ አርባ ሁለት ወር በሥልጣን እንዲሠራም ተፈቀደለት። እርሱም እግዚአብሔርን ለመሳደብ እንዲሁም ስሙንና ማደሪያውን፣ በሰማይም የሚኖሩትን ለመሳደብ አፉን ከፈተ። ቅዱሳንን እንዲዋጋና ድልም እንዲነሣቸው ኀይል ተሰጠው። በነገድ፣ በወገን፣ በቋንቋና በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በታረደው በግ የሕይወት መጽሐፍ ላይ ስሞቻቸው ያልተጻፈ የምድር ሰዎች ሁሉ ለአውሬው ይሰግዳሉ። ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ። ማንም የሚማረክ ቢኖር፣ እርሱ ይማረካል፤ ማንም በሰይፍ የሚገደል ቢኖር፣ እርሱ በሰይፍ ይገደላል። ይህም የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት የሚታየው በዚህ እንደ ሆነ ያስገነዝባል።

ራእይ 13:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

አንድም አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፥ በቀንዶቹም ላይ አሥር ዘውዶች በራሶቹም ላይ የስድብ ስም ነበረ። ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፥ እግሮቹም እንደ ድብ እግሮች፥ አፉም እንደ አንበሳ አፍ ነበሩ። ዘንዶውም ኃይሉንና ዙፋኑን ትልቅም ሥልጣን ሰጠው። ከራሶቹም ለሞት እንደ ታረደ ሆኖ አንዱን አየሁ፥ ለሞቱ የሆነውም ቍስል ተፈወሰ። ምድርም ሁሉ አውሬውን እየተከተለ ተደነቀ፥ ለዘንዶውም ሰገዱለት፥ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፤ ለአውሬውም፦ አውሬውን ማን ይመስለዋል፥ እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል? እያሉ ሰገዱለት። ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፥ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው። እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ። ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፥ በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው። ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል። ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ። ይማረክ ዘንድ ያለው ማንም ቢኖር ወደ ምርኮነት ይሄዳል፤ በሰይፍ የሚገድል ማንም ቢኖር ራሱ በሰይፍ እንዲገደል ይገባዋል። የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት በዚህ ነው።

ራእይ 13:1-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

አንድም አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ ዐሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፤ በቀንዶቹም ላይ ዐሥር ዘውዶች በራሶቹም ላይ የስድብ ስም ነበረ። ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፤ እግሮቹም እንደ ድብ እግሮች፥ አፉም እንደ አንበሳ አፍ ነበሩ። ዘንዶውም ኀይሉንና ዙፋኑን ትልቅም ሥልጣን ሰጠው። ከራሶቹም ለሞት እንደ ታረደ ሆኖ አንዱን አየሁ፤ ለሞቱ የሆነውም ቍስል ተፈወሰ። ምድርም ሁሉ አውሬውን እየተከተለ ተደነቀ፤ ለዘንዶውም ሰገዱለት፤ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፤ ለአውሬውም “አውሬውን ማን ይመስለዋል? እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል?” እያሉ ሰገዱለት። ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፤ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው። እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ። ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፤ በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው። ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል። ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ። ይማረክ ዘንድ ያለው ማንም ቢኖር ወደ ምርኮነት ይሄዳል፤ በሰይፍ የሚገድል ማንም ቢኖር ራሱ በሰይፍ እንዲገደል ይገባዋል። የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት በዚህ ነው።

ራእይ 13:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ አንድ አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ ዐሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፤ በቀንዶቹም ላይ ዐሥር ዘውዶች ነበሩ፤ በራሶቹም ላይ የስድብ ስሞች ነበሩ። ያየሁት አውሬ ነብር ይመስል ነበር፤ እግሮቹ የድብ እግሮች፥ አፉ የአንበሳ አፍ ይመስል ነበር። ዘንዶው የራሱን ኀይልና የራሱን ዙፋን ትልቅም ሥልጣን ለአውሬው ሰጠው። ከአውሬው ራሶች አንዱ ለሞት የሚያደርስ ቊስል እንደ ነበረው ሆኖ አየሁት፤ ነገር ግን ለሞት የሚያደርሰው ቊስሉ ድኖአል፤ ዓለም በሙሉ በመደነቅ አውሬውን ተከተለ። ለአውሬው ሥልጣን በመስጠቱ ሰዎች ሁሉ ለዘንዶው ሰገዱለት፤ “አውሬውን የሚመስል ማን ነው? ከእርሱስ ጋር ማን ሊዋጋ ይችላል?” እያሉ ለእርሱም ሰገዱለት። የትዕቢትና የስድብ ቃል የሚናገርበት አፍ ለአውሬው ተሰጠው፤ አርባ ሁለት ወር በሥልጣን እንዲሠራም ተፈቀደለት። እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔርን ስም፥ መኖሪያውንና በሰማይ የሚኖሩትን መሳደብ ጀመረ። ቅዱሳንን እንዲዋጋና ድል እንዲነሣቸው ሥልጣን ተሰጠው፤ በነገድና በወገን፥ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች በሚናገሩና በሕዝብ ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው። ዓለም ሲፈጠር ጀምሮ ስሞቻቸው በታረደው በግ የሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፈ በዓለም ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ለአውሬው ይሰግዳሉ። ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ! “ለመማረክ የተመደበ ይማረካል፤ በሰይፍ ለመገደል የተመደበ በሰይፍ ይገደላል፤” እንግዲህ የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት የሚያስፈልገው በዚህ ጊዜ ነው።

ራእይ 13:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከዚያም አንድ አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ ዐሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፤ በቀንዶቹም ላይ ዐሥር ዘውዶች በራሶቹም ላይ የስድብ ስም ነበረ። ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፤ እግሮቹም እንደ ድብ እግሮች፥ አፉም እንደ አንበሳ አፍ ነበሩ። ዘንዶውም ኀይሉን፥ ዙፋኑንና ትልቅ ሥልጣንን ሰጠው። ከራሶቹም አንዱ ለሞት የሚያደርስ ቁስል ነበረው፤ ለሞት የሚያደርሰውም ቁስል ተፈወሰ። ምድርም ሁሉ በመገረም አውሬውን ተከተለ፤ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና ለዘንዶውም ሰገዱለት፤ ለአውሬውም “አውሬውን ማን ይመስለዋል? እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል?” እያሉ ሰገዱለት። ታላቅ ነውርንና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፤ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው። እግዚአብሔርንም ለመሳደብ፥ ስሙንና ማደሪያውን፥ በሰማይ የሚያድሩትን ለመሳደብ አፉን ከፈተ። ቅዱሳንንም የመዋጋት፥ ድልም የማድረግ ፈቃድ ተሰጠው፤ በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው። ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ የሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ የምድር ነዋሪዎች በሙሉ ይሰግዱለታል። ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ። ለመማረክ የተመደበ ወደ ምርኮ ይሄዳል፤ በሰይፍ የሚገድል ማንም ቢኖር ራሱ በሰይፍ መገደል ይገባዋል። የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት የሚያስፈልገው እዚህ ላይ ነው።