ዘንዶውም በባሕሩ ዳር ቆሞ ነበር። ከዚያም አንድ አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ እርሱም ዐሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፤ በቀንዶቹም ላይ ዐሥር ዘውዶች፣ በራሶቹም ላይ የስድብ ስሞች ነበሩት። ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፤ ነገር ግን እግሮቹ የድብ፣ አፉ ደግሞ የአንበሳ አፍ ይመስል ነበር፤ ዘንዶው የራሱን ኀይልና የራሱን ዙፋን እንዲሁም ታላቅ ሥልጣን ለአውሬው ሰጠው። ከአውሬው ራሶች አንዱ ለሞት የሚያደርስ ቍስል ያለበት ይመስል ነበር። ነገር ግን ለሞት የሚያደርሰው ቍስሉ ዳነ፤ ዓለም በሙሉ በመደነቅ አውሬውን ተከተለው። ሰዎችም ለዘንዶው ሰገዱለት፤ ምክንያቱም ሥልጣኑን ለአውሬው ሰጥቶታል። ደግሞም፣ “አውሬውን የሚመስል ማን ነው? ከእርሱስ ጋር ማን ሊዋጋ ይችላል?” በማለት ለአውሬው ሰገዱለት። አውሬው የትዕቢት ቃል የሚናገርበትና የሚሳደብበት አፍ ተሰጠው፤ አርባ ሁለት ወር በሥልጣን እንዲሠራም ተፈቀደለት። እርሱም እግዚአብሔርን ለመሳደብ እንዲሁም ስሙንና ማደሪያውን፣ በሰማይም የሚኖሩትን ለመሳደብ አፉን ከፈተ። ቅዱሳንን እንዲዋጋና ድልም እንዲነሣቸው ኀይል ተሰጠው። በነገድ፣ በወገን፣ በቋንቋና በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በታረደው በግ የሕይወት መጽሐፍ ላይ ስሞቻቸው ያልተጻፈ የምድር ሰዎች ሁሉ ለአውሬው ይሰግዳሉ። ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ። ማንም የሚማረክ ቢኖር፣ እርሱ ይማረካል፤ ማንም በሰይፍ የሚገደል ቢኖር፣ እርሱ በሰይፍ ይገደላል። ይህም የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት የሚታየው በዚህ እንደ ሆነ ያስገነዝባል።
ራእይ 13 ያንብቡ
ያዳምጡ ራእይ 13
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ራእይ 13:1-10
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos