የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ራእይ 11:1-19

ራእይ 11:1-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በትር የሚመስል መለኪያ ለእኔ ተሰጠኝ፤ እንዲህም ተባልሁ “ተነሥተህ የእግዚአብሔርን መቅደስና መሠዊያውን በዚያም የሚሰግዱትን ለካ። በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው፤ አትለካውም፤ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል። ለሁለቱም ምስክሮቼ ማቅ ለብሰው ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ሊናገሩ እሰጣለሁ።” እነዚህ በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙ ሁለቱ ወይራዎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው። ማንምም ሊጐዳቸው ቢወድ እሳት ከአፋቸው ይወጣል፤ ጠላቶቻቸውንም ይበላል፤ ማንም ሊጐዳቸው ቢወድም እንዲሁ ሊገደል ይገባዋል። እነዚህ ትንቢት በሚናገሩበት ወራት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ሊዘጉ ሥልጣን አላቸው፤ ውሕሃዎችንም ወደ ደም ሊለውጡ በሚፈልጉበትም ጊዜ ሁሉ በመቅሠፍት ሁሉ ምድርን ሊመቱ ሥልጣን አላቸው። ምስክራቸውን ከፈጸሙ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል፤ ያሸንፋቸውማል፤ ይገድላቸውማል። በድናቸውም በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይተኛል፤ እርስዋም በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብጽ የተባለች ደግሞ ጌታቸው የተሰቀለባት ናት። ከወገኖችና ከነገዶችም ከቋንቋዎችም ከአሕዛብም የሆኑ ሰዎች ሦስት ቀን ተኵል በድናቸውን ይመለከታሉ፤ በድናቸውም ወደ መቃብር ሊገባ አይፈቅዱም። እነዚህም ሁለት ነቢያት በምድር የሚኖሩትን ስላሠቃዩ በምድር የሚኖሩት በእነርሱ ላይ ደስ ይላቸዋል፤ በደስታም ይኖራሉ፤ እርስ በርሳቸውም ስጦታ ይሰጣጣሉ። ከሦስቱ ቀን ተኵልም በኋላ ከእግዚአብሔር የወጣ የሕይወት መንፈስ ገባባቸው፤ በእግሮቻቸውም ቆሙ፤ ታላቅም ፍርሃት በሚመለከቱት ላይ ወደቀባቸው። በሰማይም “ወደዚህ ውጡ” የሚላቸውን ታላቅ ድምፅ ሰሙ፤ ጠላቶቻቸውም እየተመለከቱአቸው ወደ ሰማይ በደመና ወጡ። በዚያም ሰዓት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ከከተማይቱም ዐሥረኛው እጅ ወደቀ፤ በመናወጥም ሰባት ሺህ ሰዎች ተገደሉ፤ የቀሩትንም ፍርሃት ያዛቸው፤ ለሰማዩም አምላክ ክብር ሰጡ። ሁለተኛው ወዮ አልፎአል፤ እነሆ ሦስተኛው ወዮ በቶሎ ይመጣል። ሰባተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በሰማይም “የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች፤ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣል፤” የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ሆኑ። በእግዚአብሔርም ፊት በዙፋኖቻቸው የተቀመጡ ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በግምባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር እየሰገዱ እንዲህ አሉ “ያለህና የነበርህ ሁሉን የምትገዛ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ትልቁን ኀይልህን ስለ ያዝህ ስለ ነገሥህም እናመሰግንሃለን፤ አሕዛብም ተቈጡ፤ ቍጣህም መጣ፤ በሙታንም ትፈርድ ዘንድ ዘመን መጣ፤ ለባሪያዎችህም ለነቢያትና ለቅዱሳን ስምህንም ለሚፈሩት ለታናናሾችና ለታላላቆችም ዋጋቸውን ትሰጥ ዘንድ፥ ምድርንም የሚያጠፉትን ታጠፋ ዘንድ ዘመን መጣ።” በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፤ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ፤ መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ ታላቅም በረዶ ሆነ።

ራእይ 11:1-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚያም ሸንበቆ የመሰለ መለኪያ በትር ተሰጠኝ፤ እንዲህም ተባልሁ፤ “ሄደህ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና መሠዊያውን ለካ፤ በዚያም የሚያመልኩትን ቍጠር። የውጭውን አደባባይ ግን ተወው አትለካው፣ ለአሕዛብ የተሰጠ ነውና። እነርሱ የተቀደሰችውን ከተማ አርባ ሁለት ወር ይረግጧታል። ለሁለቱ ምስክሮቼ ኀይል እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ማቅ ለብሰው አንድ ሺሕ ሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ይናገራሉ።” እነዚህም በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙት ሁለቱ የወይራ ዛፎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው። ማንም እነርሱን ሊጐዳ ቢፈልግ፣ እሳት ከአፋቸው ወጥቶ ጠላቶቻቸውን ያጠፋል፤ ሊጐዳቸው የሚፈልግ ሁሉ መሞት ያለበት በዚህ ዐይነት ነው። እነዚህ ሰዎች ትንቢት በሚናገሩባቸው ወራት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ለመዝጋት ሥልጣን አላቸው፤ ደግሞም ውሆችን ወደ ደም ለመለወጥ በሚፈልጉበት ጊዜ ሁሉ ምድርን በማንኛውም መቅሠፍት ለመምታት ሥልጣን አላቸው። ምስክርነታቸውን ከጨረሱ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል፤ ድል ይነሣቸዋል፤ ይገድላቸዋልም። ሬሳቸውም በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይጣላል፤ ይህች ከተማ ሰዶምና ግብፅ እየተባለች በምሳሌ የምትጠራውና የእነርሱም ጌታ የተሰቀለባት ናት። ከወገን፣ ከነገድ፣ ከቋንቋና ከሕዝብ የመጡ ሰዎች ሬሳቸውን ሦስት ቀን ተኩል ይመለከታሉ፤ ሬሳቸውም እንዳይቀበር ይከለክላሉ። እነዚህ ሁለት ነቢያት የምድር ነዋሪዎችን ያሠቃዩ ስለ ነበር፣ በምድር የሚኖሩ ሰዎች በእነርሱ ላይ በደረሰው ደስ ይላቸዋል፤ እርስ በርሳቸውም ስጦታ ይለዋወጣሉ። ከሦስቱ ቀን ተኩል በኋላ ግን፣ የሕይወት እስትንፋስ ከእግዚአብሔር ዘንድ መጥቶ ገባባቸው፤ እነርሱም ተነሥተው በእግሮቻቸው ቆሙ፤ ይመለከቷቸውም በነበሩት ላይ ታላቅ ድንጋጤ ወረደባቸው። ከዚያም፣ “ወደዚህ ውጡ” የሚላቸውን ታላቅ ድምፅ ከሰማይ ሰሙ፤ ጠላቶቻቸው እየተመለከቷቸው በደመና ወደ ሰማይ ወጡ። በዚያም ሰዓት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ የከተማዪቱም አንድ ዐሥረኛ ወደመ፤ በነውጡም ሰባት ሺሕ ሰዎች ሞቱ፤ የተረፉትንም ፍርሀት ያዛቸው፤ ለሰማይም አምላክ ክብር ሰጡ። ሁለተኛው ወዮ ዐልፏል፤ እነሆ፤ ሦስተኛው ወዮ ቶሎ ይመጣል። ሰባተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በሰማይም እንዲህ የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ተሰሙ፤ “የዓለም መንግሥት፣ የጌታችንና የእርሱ ክርስቶስ መንግሥት ሆነች፤ እርሱም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣል።” በእግዚአብሔር ፊት በዙፋኖቻቸው ላይ የተቀመጡት ሃያ አራቱ ሽማግሌዎችም በግንባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ እንዲህም አሉ፤ “ያለህና የነበርህ፣ ሁሉን ቻይ፣ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ እናመሰግንሃለን፤ ምክንያቱም አንተ ታላቁን ኀይልህን ይዘህ ነግሠሃል። አሕዛብ ተቈጥተው ነበር፤ የአንተም ቍጣ መጣች፤ በሙታን ላይ የምትፈርድበት፣ ለአገልጋዮችህ ለነቢያት፣ ለቅዱሳንና ስምህን ለሚፈሩት፣ ለታናናሾችና ለታላላቆች ዋጋቸውን የምትሰጥበት፣ ምድርንም ያጠፏትን የምታጠፋበት ዘመን መጣ።” ከዚያም በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተከፈተ፤ በመቅደሱም ውስጥ የኪዳኑ ታቦት ታየ፤ መብረቅ፣ ድምፅ፣ ነጐድጓድ፣ የምድር መናወጥና ታላቅም በረዶ ሆነ።

ራእይ 11:1-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በትር የሚመስል መለኪያ ለእኔ ተሰጠኝ፥ እንዲህም ተባለልኝ፦ ተነሥተህ የእግዚአብሔርን መቅደስና መሠዊያውን በዚያም የሚሰግዱትን ለካ። በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው አትለካውም፤ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል። ለሁለቱም ምስክሮቼ ማቅ ለብሰው ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ሊናገሩ እሰጣለሁ። እነዚህ በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙ ሁለቱ ወይራዎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው። ማንምም ሊጐዳቸው ቢወድ እሳት ከአፋቸው ይወጣል ጠላቶቻቸውንም ይበላል፤ ማንም ሊጐዳቸው ቢወድም እንዲሁ ሊገደል ይገባዋል። እነዚህ ትንቢት በሚናገሩበት ወራት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ሊዘጉ ሥልጣን አላቸው፥ ውኃዎችንም ወደ ደም ሊለውጡ በሚፈልጉበትም ጊዜ ሁሉ በመቅሠፍት ሁሉ ምድርን ሊመቱ ሥልጣን አላቸው። ምስክራቸውን ከፈጸሙ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል ያሸንፋቸውማል ይገድላቸውማል። በድናቸውም በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይተኛል እርስዋም በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብጽ የተባለች ደግሞ ጌታቸው የተሰቀለባት ናት። ከወገኖችና ከነገዶችም ከቋንቋዎችም ከአሕዛብም የሆኑ ሰዎች ሦስት ቀን ተኵል በድናቸውን ይመለከታሉ፥ በድናቸውም ወደ መቃብር ሊገባ አይፈቅዱም። እነዚህም ሁለት ነቢያት በምድር የሚኖሩትን ስለ ሣቀዩ በምድር የሚኖሩት በእነርሱ ላይ ደስ ይላቸዋል በደስታም ይኖራሉ እርስ በርሳቸውም ስጦታ ይሰጣጣሉ። ከሦስቱ ቀን ተኵልም በኋላ ከእግዚአብሔር የወጣ የሕይወት መንፈስ ገባባቸው በእግሮቻቸውም ቆሙ፥ ታላቅም ፍርሃት በሚመለከቱት ላይ ወደቀባቸው። በሰማይም፦ ወደዚህ ውጡ የሚላቸውን ታላቅ ድምፅ ሰሙ፤ ጠላቶቻቸውም እየተመለከቱአቸው ወደ ሰማይ በደመና ወጡ። በዚያም ሰዓት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፥ ከከተማይቱም አሥረኛው እጅ ወደቀ፥ በመናወጥም ሰባት ሺህ ሰዎች ተገደሉ፥ የቀሩትንም ፍርሃት ያዛቸው፥ ለሰማዩም አምላክ ክብር ሰጡ። ሁለተኛው ወዮ አልፎአል፤ እነሆ፥ ሦስተኛው ወዮ በቶሎ ይመጣል። ሰባተኛው መልአክ ነፋ፤ በሰማይም፦ የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣል የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ሆኑ። በእግዚአብሔርም ፊት በዙፋኖቻቸው የተቀመጡ ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በግምባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር እየሰገዱ እንዲህ አሉ፦ ያለህና የነበርህ ሁሉን የምትገዛ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ትልቁን ኃይልህን ስለ ያዝህ ስለ ነገሥህም እናመሰግንሃለን፤ አሕዛብም ተቈጡ፥ ቍጣህም መጣ፥ በሙታንም ትፈርድ ዘንድ ዘመን መጣ፥ ለባሪያዎችህም ለነቢያትና ለቅዱሳን ስምህንም ለሚፈሩት ለታናናሾችና ለታላላቆችም ዋጋቸውን ትሰጥ ዘንድ፥ ምድርንም የሚያጠፉትን ታጠፋ ዘንድ ዘመን መጣ። በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፥ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ፥ መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ ታላቅም በረዶ ሆነ።

ራእይ 11:1-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ ለመለኪያ እንደሚያገለግል በትር ያለ አንድ ሸንበቆ ተሰጠኝ፤ እንዲህም ተባልኩ፦ “ተነሥ፤ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና መሠዊያውን ለካ፤ በዚያ የሚያመልኩትንም ቊጠር፤ ከቤተ መቅደሱ ውጪ ያለውን ክፍት ቦታ ግን ተወው፤ እርሱ ለአሕዛብ የተሰጠ ስለ ሆነ አትለካው፤ አሕዛብ ቅድስቲቱን ከተማ ለአርባ ሁለት ወር ይረግጡአታል፤ ሁለቱ ምስክሮቼ የሐዘን ልብስ ለብሰው አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሥልሳ ቀን ትንቢት እንዲናገሩ ኀይል እሰጣቸዋለሁ።” እነርሱ በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙ ሁለቱ የወይራ ዛፎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው፤ ማንም እነርሱን ሊጐዳ ቢፈልግ እሳት ከአፋቸው ወጥቶ ጠላቶቻቸውን ያቃጥላል፤ እነርሱን ሊጐዳ የሚፈልግ ሁሉ የሚሞተው በዚህ ዐይነት ነው። እነርሱ ትንቢት በሚናገሩባቸው በእነዚህ ቀኖች ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ለመዝጋት ሥልጣን አላቸው፤ እንዲሁም ውሃዎችን ወደ ደም ለመለወጥና በሚፈልጉትም ጊዜ ሁሉ በማንኛውም ዐይነት መቅሠፍት ምድርን ለመምታት ሥልጣን አላቸው። ምስክርነታቸውን ከጨረሱ በኋላ ከጥልቁ ጒድጓድ የሚወጣው አውሬ ከእነርሱ ጋር ተዋግቶ ያሸንፋቸዋል፤ ይገድላቸዋልም፤ ሬሳቸውም በምሳሌያዊ አጠራር ሰዶም ወይም ግብጽ በምትባል በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይጋደማል፤ ይህች ከተማ የእነርሱ ጌታ የተሰቀለባት ናት። ልዩ ልዩ ወገንና፥ ነገድ፥ ልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪዎችና ሕዝቦች ሦስት ቀን ተኩል ሬሳቸውን ይመለከታሉ፤ ሬሳቸው እንዳይቀበርም ይከለክላሉ። እነዚህ ሁለቱ ነቢያት የምድር ሰዎችን አስጨንቀው ስለ ነበረ በምድር የሚኖሩ ሰዎች በነቢያቱ ሞት ደስ ይላቸዋል፤ በደስታም በዓል ያደርጋሉ፤ ስጦታም ይለዋወጣሉ። ነገር ግን ሦስት ቀን ተኩል ካለፈ በኋላ ሕይወት የሚሰጥ እስትንፋስ ከእግዚአብሔር መጥቶ ወደ ሬሳዎቹ ገባ፤ በእግራቸውም ቆሙ፤ ያዩአቸውም ሰዎች እጅግ ፈሩ። ከዚህ በኋላ ሁለቱ ነቢያት “ወደዚህ ወደ ላይ ውጡ!” የሚል ታላቅ ድምፅ ከሰማይ ሰሙ፤ ጠላቶቻቸው እየተመለከቱአቸውም በደመና ወደ ሰማይ ወጡ። በዚያኑ ሰዓት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ የከተማይቱም አንድ ዐሥረኛ ፈራረሰ፤ በምድር መናወጥም ምክንያት ሰባት ሺህ ሰዎች ሞቱ፤ ከሞት የተረፉትም እጅግ ፈሩ፤ የሰማይንም አምላክ አከበሩ። ሁለተኛው ወዮ አለፈ፤ እነሆ፥ ሦስተኛው ወዮ ቶሎ ይመጣል። ሰባተኛውም መልአክ እምቢልታውን ነፋ፤ በሰማይም “የዓለም መንግሥት የጌታ የአምላካችንና የመሲሑ ሆናለች፤ እርሱ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይነግሣል፤” የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ተሰሙ። በእግዚአብሔር ፊት በዙፋኖቻቸው ላይ የተቀመጡት ኻያ አራቱ ሽማግሌዎችም በግንባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ እንዲህም አሉ፦ “ያለህና የነበርክ፤ ሁሉን የምትችል ጌታ አምላክ ሆይ! ትልቁን ሥልጣንህን በእጅህ ስላደረግህና ስለ ነገሥክ እናመሰግንሃለን። አሕዛብ ተቈጡ፤ የአንተም ቊጣ መጣ፤ ሙታን ፍርድ የሚያገኙበት ጊዜም ደረሰ፤ ለአገልጋዮችህ ለነቢያትና ለቅዱሳን ስምህንም ለሚያከብሩት፥ ለታናናሾችና ለታላላቆች፥ ዋጋቸውን የምትሰጥበት ጊዜ ደረሰ፤ ምድርን ያጠፉአትን የምታጠፋበት ጊዜም ደረሰ።” በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ተከፈተ፤ የእርሱም የኪዳን ታቦት በቤተ መቅደሱ ውስጥ ታየ። መብረቅ፥ ድምፅ፥ ነጐድጓድ፥ የምድር መናወጥና ታላቅም በረዶ ሆነ።

ራእይ 11:1-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በትር የሚመስል የመለኪያ ሸንበቆ ተሰጠኝ፤ እንዲህም ተባልሁ “ተነሥተህ የእግዚአብሔርን መቅደስና መሠዊያውን በዚያም የሚሰግዱትን ለካ። ከመቅደሱ ውጭ ያለውን አደባባይ ግን ተወው፤ አትለካውም፥ ምክንያቱም ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና፤ እነርሱም ለአርባ ሁለት ወር ያህል የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል። ማቅ ለብሰው ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት እንዲናገሩ ለሁለቱም ምስክሮቼ ኃይል እሰጣለሁ።” እነዚህ በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙ ሁለቱ የወይራ ዛፎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው። ማንም ሊጐዳቸው ቢወድ እሳት ከአፋቸው ይወጣል፤ ጠላቶቻቸውንም ይበላል፤ ማንም ሊጐዳቸው ቢወድም እንዲሁ ሊገደል ይገባዋል። እነዚህ ትንቢት በሚናገሩበት ወራት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን የመዝጋት ሥልጣን አላቸው፤ ውሃዎችንም ወደ ደም ለመለወጥ በሚፈልጉበትም ጊዜ ሁሉ በመቅሠፍት ምድርን የመምታት ሥልጣን አላቸው። ምስክራነታቸውንም ከፈጸሙ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል፤ ያሸንፋቸውማል፤ ይገድላቸውማል። በድናቸውም በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይተኛል፤ እርሷም በምሳሌያዊ አነጋገር ሰዶምና ግብጽ የተባለችው፥ ጌታቸውም የተሰቀለባት ከተማ ናት። ከወገኖችና ከነገዶችም ከቋንቋዎችም ከአሕዛብም የሆኑ ሰዎች ሦስት ቀን ተኩል በድናቸውን ይመለከታሉ፤ በድናቸውም ወደ መቃብር እንዲገባ አይፈቅዱም። እነዚህም ሁለት ነቢያት በምድር የሚኖሩትን ስላሠቃዩ በምድር የሚኖሩት በእነርሱ ዕጣ ደስ ይላቸዋል፤ በደስታም ይኖራሉ፤ እርስ በርሳቸውም ስጦታ ይሰጣጣሉ። ከሦስቱ ቀን ተኩልም በኋላ ከእግዚአብሔር የወጣ የሕይወት መንፈስ ገባባቸው፤ በእግሮቻቸውም ቆሙ፤ ታላቅም ፍርሃት በሚመለከቱት ላይ ወደቀባቸው። በሰማይም “ወደዚህ ውጡ” የሚላቸውን ታላቅ ድምፅ ሰሙ፤ ጠላቶቻቸውም እየተመለከቱአቸው ወደ ሰማይ በደመና ወጡ። በዚያም ሰዓት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ከከተማይቱም ዐሥረኛው እጅ ወደቀ፤ በመናወጥም ሰባት ሺህ ሰዎች ተገደሉ፤ የቀሩትንም ፍርሃት ያዛቸው፤ ለሰማዩም አምላክ ክብር ሰጡ። ሁለተኛው ወዮ አልፎአል፤ እነሆ ሦስተኛው ወዮ በቶሎ ይመጣል። ሰባተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በሰማይም እንዲህ የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ተሰሙ፦ “የዓለም መንግሥት የጌታችንና የመሢሑ ሆነች፤ ለዘለዓለምም እስከ ዘለዓለም ይነግሣል፤” በእግዚአብሔርም ፊት በዙፋኖቻቸው የተቀመጡ ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በግምባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር እየሰገዱ እንዲህ አሉ፦ “ያለህና የነበርህ ሁሉን የምትገዛ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ትልቁን ኃይልህን ስለ ወሰድክና ስለ ነገሥህ እናመሰግንሃለን፤ አሕዛብም ተቈጡ፤ ቁጣህም መጣ፤ በሙታንም የምትፈርድበት ዘመን መጣ፤ ለባርያዎችህም ለነቢያትና ለቅዱሳን፥ ስምህንም ለሚፈሩት ለታናናሾችና ለታላላቆችም ዋጋቸውን የምትሰጥበት ምድርንም የሚያጠፉትን የምታጠፋበት ዘመን መጣ።” በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተከፈተ፤ የኪዳኑም ታቦት በቤተ በመቅደሱ ታየ፤ መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ ታላቅም በረዶ ሆነ።