የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ራእይ 11:1-19

የዮሐንስ ራእይ 11:1-19 አማ05

ከዚህ በኋላ ለመለኪያ እንደሚያገለግል በትር ያለ አንድ ሸንበቆ ተሰጠኝ፤ እንዲህም ተባልኩ፦ “ተነሥ፤ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና መሠዊያውን ለካ፤ በዚያ የሚያመልኩትንም ቊጠር፤ ከቤተ መቅደሱ ውጪ ያለውን ክፍት ቦታ ግን ተወው፤ እርሱ ለአሕዛብ የተሰጠ ስለ ሆነ አትለካው፤ አሕዛብ ቅድስቲቱን ከተማ ለአርባ ሁለት ወር ይረግጡአታል፤ ሁለቱ ምስክሮቼ የሐዘን ልብስ ለብሰው አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሥልሳ ቀን ትንቢት እንዲናገሩ ኀይል እሰጣቸዋለሁ።” እነርሱ በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙ ሁለቱ የወይራ ዛፎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው፤ ማንም እነርሱን ሊጐዳ ቢፈልግ እሳት ከአፋቸው ወጥቶ ጠላቶቻቸውን ያቃጥላል፤ እነርሱን ሊጐዳ የሚፈልግ ሁሉ የሚሞተው በዚህ ዐይነት ነው። እነርሱ ትንቢት በሚናገሩባቸው በእነዚህ ቀኖች ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ለመዝጋት ሥልጣን አላቸው፤ እንዲሁም ውሃዎችን ወደ ደም ለመለወጥና በሚፈልጉትም ጊዜ ሁሉ በማንኛውም ዐይነት መቅሠፍት ምድርን ለመምታት ሥልጣን አላቸው። ምስክርነታቸውን ከጨረሱ በኋላ ከጥልቁ ጒድጓድ የሚወጣው አውሬ ከእነርሱ ጋር ተዋግቶ ያሸንፋቸዋል፤ ይገድላቸዋልም፤ ሬሳቸውም በምሳሌያዊ አጠራር ሰዶም ወይም ግብጽ በምትባል በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይጋደማል፤ ይህች ከተማ የእነርሱ ጌታ የተሰቀለባት ናት። ልዩ ልዩ ወገንና፥ ነገድ፥ ልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪዎችና ሕዝቦች ሦስት ቀን ተኩል ሬሳቸውን ይመለከታሉ፤ ሬሳቸው እንዳይቀበርም ይከለክላሉ። እነዚህ ሁለቱ ነቢያት የምድር ሰዎችን አስጨንቀው ስለ ነበረ በምድር የሚኖሩ ሰዎች በነቢያቱ ሞት ደስ ይላቸዋል፤ በደስታም በዓል ያደርጋሉ፤ ስጦታም ይለዋወጣሉ። ነገር ግን ሦስት ቀን ተኩል ካለፈ በኋላ ሕይወት የሚሰጥ እስትንፋስ ከእግዚአብሔር መጥቶ ወደ ሬሳዎቹ ገባ፤ በእግራቸውም ቆሙ፤ ያዩአቸውም ሰዎች እጅግ ፈሩ። ከዚህ በኋላ ሁለቱ ነቢያት “ወደዚህ ወደ ላይ ውጡ!” የሚል ታላቅ ድምፅ ከሰማይ ሰሙ፤ ጠላቶቻቸው እየተመለከቱአቸውም በደመና ወደ ሰማይ ወጡ። በዚያኑ ሰዓት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ የከተማይቱም አንድ ዐሥረኛ ፈራረሰ፤ በምድር መናወጥም ምክንያት ሰባት ሺህ ሰዎች ሞቱ፤ ከሞት የተረፉትም እጅግ ፈሩ፤ የሰማይንም አምላክ አከበሩ። ሁለተኛው ወዮ አለፈ፤ እነሆ፥ ሦስተኛው ወዮ ቶሎ ይመጣል። ሰባተኛውም መልአክ እምቢልታውን ነፋ፤ በሰማይም “የዓለም መንግሥት የጌታ የአምላካችንና የመሲሑ ሆናለች፤ እርሱ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይነግሣል፤” የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ተሰሙ። በእግዚአብሔር ፊት በዙፋኖቻቸው ላይ የተቀመጡት ኻያ አራቱ ሽማግሌዎችም በግንባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ እንዲህም አሉ፦ “ያለህና የነበርክ፤ ሁሉን የምትችል ጌታ አምላክ ሆይ! ትልቁን ሥልጣንህን በእጅህ ስላደረግህና ስለ ነገሥክ እናመሰግንሃለን። አሕዛብ ተቈጡ፤ የአንተም ቊጣ መጣ፤ ሙታን ፍርድ የሚያገኙበት ጊዜም ደረሰ፤ ለአገልጋዮችህ ለነቢያትና ለቅዱሳን ስምህንም ለሚያከብሩት፥ ለታናናሾችና ለታላላቆች፥ ዋጋቸውን የምትሰጥበት ጊዜ ደረሰ፤ ምድርን ያጠፉአትን የምታጠፋበት ጊዜም ደረሰ።” በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ተከፈተ፤ የእርሱም የኪዳን ታቦት በቤተ መቅደሱ ውስጥ ታየ። መብረቅ፥ ድምፅ፥ ነጐድጓድ፥ የምድር መናወጥና ታላቅም በረዶ ሆነ።