መዝሙር 89:19-52
መዝሙር 89:19-52 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚያን ጊዜ በራእይ ተናገርህ፤ ታማኝ ሕዝብህንም እንዲህ አልህ፤ “ኀያሉን ሰው ሥልጣን አጐናጸፍሁት፤ ከሕዝብ መካከል የተመረጠውንም ከፍ ከፍ አደረግሁት። ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት፤ በተቀደሰው ዘይቴም ቀባሁት። እጄ ይደግፈዋል፤ ክንዴም ያበረታዋል። በጠላት አይበለጥም፤ ክፉ ሰውም አይበግረውም። ባላንጣዎቹን በፊቱ አደቅቃቸዋለሁ፤ ጠላቶቹንም እቀጠቅጣለሁ። ታማኝነቴና ምሕረቴ ከእርሱ ጋር ይሆናል፤ በስሜም ቀንዱ ከፍ ከፍ ይላል። እጁን በባሕር ላይ፣ ቀኝ እጁንም በወንዞች ላይ አኖራለሁ። እርሱም፣ ‘አንተ አባቴ ነህ፤ አምላኬና መዳኛ ዐለቴም ነህ’ ብሎ ይጠራኛል። እኔም ደግሞ በኵሬ አደርገዋለሁ፤ ከምድር ነገሥታትም በላይ ከፍ ይላል። ምሕረቴንም ለዘላለም ለእርሱ እጠብቃለሁ፤ ከእርሱ ጋር የገባሁት ኪዳንም ጸንቶ ይኖራል። የዘር ሐረጉን ለዘላለም፣ ዙፋኑንም በሰማያት ዕድሜ ልክ አጸናለሁ። “ልጆቹ ሕጌን ቢተዉ፣ ደንቤን ባይጠብቁ፣ ሥርዐቴን ቢጥሱ፣ ትእዛዜንም ባያከብሩ፣ ኀጢአታቸውን በበትር፣ በደላቸውን በጅራፍ እቀጣለሁ። ምሕረቴን ግን ከእርሱ አላርቅም፤ ታማኝነቴንም አላጓድልበትም። ኪዳኔን አላፈርስም፤ ከአፌ የወጣውንም አላጥፍም። አንድ ጊዜ በቅድስናዬ ምያለሁና፣ ዳዊትን አልዋሸውም። የዘር ሐረጉ ለዘላለም፣ ዙፋኑም በፊቴ እንደ ፀሓይ ጸንቶ ይኖራል፤ በሰማይ ታማኝ ምስክር ሆና እንደምትኖረው፣ እንደ ጨረቃ እርሱ ለዘላለም ይመሠረታል።” ሴላ አሁን ግን ናቅኸው፤ ጣልኸውም፤ የቀባኸውንም እጅግ ተቈጣኸው። ከባሪያህ ጋር የገባኸውን ኪዳን አፈረስህ፤ የክብር ዘውዱን ትቢያ ላይ ጥለህ አቃለልኸው። ቅጥሩን ሁሉ አፈራረስህ፤ ምሽጉንም ደመሰስህ። ዐላፊ አግዳሚው ሁሉ ዘረፈው፤ ለጎረቤቶቹ መዘባበቻ ሆነ። የጠላቶቹን ቀኝ እጅ ከፍ ከፍ አደረግህ፤ ባላንጣዎቹም ሁሉ ደስ አላቸው። የሰይፉን ስለት አጠፍህ፤ በጦርነትም ጊዜ አልረዳኸውም። ግርማዊነቱን አጠፋህበት፤ ዙፋኑንም ከዐፈር ደባለቅኸው። የወጣትነት ዘመኑን አሳጠርኸው፤ ዕፍረትንም አከናነብኸው። ሴላ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህ እስከ መቼ ይሆናል? ራስህንስ ለዘላለም ትሰውራለህን? ቍጣህስ እንደ እሳት የሚነድደው እስከ መቼ ነው? ዘመኔ ምን ያህል ዐጭር እንደ ሆነች ዐስብ፤ የሰውን ልጆች እንዲያው ለከንቱ ፈጠርሃቸው! ሞትን ሳያይ ሕያው ሆኖ የሚቀር ሰው አለን? ራሱን ከሲኦል እጅ ማዳን የሚችል ማን ነው? ሴላ ጌታ ሆይ፤ ለዳዊት በታማኝነትህ የማልህለት፣ የቀድሞው ምሕረትህ የት አለ? ጌታ ሆይ፤ ባሪያህ እንዴት እንደ ተፌዘበት፣ የብዙ ሰዎችንም ነቀፋ እንደ ታቀፍሁ ዐስብ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ጠላቶችህ የተሣለቁበትን፣ የቀባኸውን ሰው ርምጃ የነቀፉበትን ሁኔታ ዐስብ። እግዚአብሔር ለዘላለም ይባረክ፤ አሜን፤ አሜን።
መዝሙር 89:19-52 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አንድ ጊዜ በራእይ ለታማኝ አገልጋይህ እንዲህ ብለህ ተናግረሃል፤ “አንዱን ታላቅ ጀግና ረድቼአለሁ፤ ከሕዝቤ መካከል መርጬ ዘውድን አቀዳጅቼዋለሁ። አገልጋዬን ዳዊትን አገኘሁት፤ የተቀደሰ ዘይት ቀብቼም አነገሥኩት። እርሱን ለመርዳትና ለማበርታት፥ እኔ ዘወትር ከእርሱ ጋር ነኝ። ጠላት አይረታውም፤ ክፉም ሰው አያዋርደውም። ጠላቶቹን አደቅለታለሁ፤ የሚጠሉትንም ሁሉ ከፊቱ አጠፋለታለሁ። ታማኝነቴና ዘለዓለማዊ ፍቅሬ ሁልጊዜ ከእርሱ ጋር ይሆናል። በሥልጣኔም ብርቱ አደርገዋለሁ። ግዛቱንም በባሕርና በወንዞች ማዶ በሚገኘው ምድር ላይ አደርግለታለሁ። እርሱም ‘አንተ አባቴና አምላኬ ነህ፤ አንተ አምባዬና አዳኜ ነህ’ ይለኛል። ከምድር ነገሥታትም ሁሉ በላይ እንዲሆን የብኲርናን ማዕርግ እሰጠዋለሁ። ለእርሱ ያለኝ ፍቅር ዘለዓለማዊ ነው፤ ከእርሱም ጋር የገባሁት ቃል ኪዳን ከቶ አይፈርስም። ዙፋኑ እንደ ሰማይ የጸና ይሆናል፤ ዘሩም ለዘለዓለም ይነግሣል። “ነገር ግን የእርሱ ዘሮች ሕጌን ቢጥሱ፥ በሥርዓቴም ባይኖሩ፤ ድንጋጌዎቼን ቢተላለፉና ትእዛዞቼን ባይጠብቁ፥ በኃጢአታቸው ምክንያት እቀጣቸዋለሁ፤ በበደላቸውም ምክንያት መከራ አመጣባቸዋለሁ። ነገር ግን ለዳዊት ያለኝ ፍቅር ከቶ አይገታም፤ ለእርሱ የሰጠሁትንም የተስፋ ቃል ከመፈጸም ወደ ኋላ አልልም። ከእርሱ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አላፈርስም፤ ለእርሱ ከሰጠሁትም የተስፋ ቃል አንዱን እንኳ አላስቀርም። “በማያዳግም ሁኔታ አንድ ጊዜ በቅዱስ ስሜ ስለ ማልኩ ለዳዊት ከቶ አልዋሽም። ትውልዱ አይቋረጥም፤ መንግሥቱንም ፀሐይ እስከምትኖርበት ዘመን እጠብቃለሁ። በሰማይ በእውነተኛነት እንደምትመሰክረው እንደ ጨረቃም የጸና ይሆናል።” አሁን ግን በመረጥከው ንጉሥ ላይ ተቈጥተሃል፤ ተለይተኸዋል፤ ጥለኸዋልም። ከአገልጋይህ ጋር የገባኸውን ቃል ኪዳን አፍርሰሃል፤ ዘውዱንም በዐፈር ላይ ጥለኸዋል። ቅጽሮቹን አፈራርሰሃል፤ ምሽጎቹንም ደምስሰሃል። የመንገድ ተላላፊዎች ሁሉ ንብረቱን ይዘርፋሉ፤ የጐረቤቶቹ መሳለቂያ ሆኖአል። ድልን ለጠላቶቹ ሰጥተህ፥ እንዲደሰቱ አደረግኻቸው። የመዘዘውን ሰይፍ እንዲመልስ አድርገኸዋል፤ በጦርነትም አልረዳኸውም። በትረ መንግሥቱን ነጠቅኸው፤ ዙፋኑንም በመሬት ላይ ጣልክበት። ያለ ዕድሜው አስረጀኸው፤ በኀፍረትም ሸፈንከው። እግዚአብሔር ሆይ! የምትሰወረው ለዘለዓለም ነውን? ቊጣህስ እንደ እሳት የሚነደው እስከ መቼ ነው? ዕድሜዬ ምን ያኽል አጭር እንደ ሆነ አስብ፤ ሰውን ሁሉ የፈጠርከው ለከንቱ ነውን? ሰው ሞት ሳይደርስበት እንዲሁ ለመኖር እንዴት ይችላል? ወደ መቃብር ሳይወርድ ሊቀርስ እንዴት ይችላል? ጌታ ሆይ! የቀድሞዎቹ የፍቅርህ ማረጋገጫዎች የት አሉ? ለዳዊት የሰጠኸውስ የተስፋ ቃል የት ነው? እኔ አገልጋይህ የቱን ያኽል እንደምሰደብ፥ የሕዝቦችን ሁሉ ስድብ ታግሼ እንደምኖር አስብ እግዚአብሔር ሆይ! ጠላቶችህ የመረጥከውን ንጉሥ ይሰድባሉ፤ በሄደበት ሁሉ ያፌዙበታል። እግዚአብሔር ለዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን!
መዝሙር 89:19-52 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጋሻችን ከጌታ ነው፥ ከንጉሣችንም ከእስራኤል ቅዱስ ነውና። በዚያ ጊዜ ለታማኞችህ በራእይ ተናገርህ፥ እንዲህም አልህ፦ ረድኤቴን በኃያል ላይ አኖርሁ፥ ከሕዝቤ የተመረጠውን ከፍ ከፍ አደረግሁ። አገልጋዬን ዳዊትን አገኘሁት፥ በቅዱስ ዘይቴም ቀባሁት። እጄም ትረዳዋለች፥ ክንዴም ታጸናዋለች። ጠላት በእርሱ ላይ አይጠቀምም፥ የዓመፃ ልጅም መከራ አይጨምርበትም። ጠላቶቹን ከፊቱ አጠፋለሁ፥ የሚጠሉትንም አዋርዳቸዋለሁ። እውነቴና ጽኑ ፍቅሬም ከእርሱ ጋር ነው፥ በስሜም ቀንዱ ከፍ ከፍ ይላል። እጁን በባሕር ላይ ቀኙንም በወንዞች ላይ አኖራለሁ። እርሱ፦ አባቴ አንተ ነህ፥ አምላኬ የመድኃኒቴም መጠጊያ ይላል። እኔም ደግሞ በኩሬ አደርገዋለሁ፥ ከምድር ነገሥታትም ከፍ ይላል። ለዘለዓለምም ጽኑ ፍቅሬን ለእርሱ እጠብቃለሁ፥ ኪዳኔም በእርሱ ዘንድ የታመነ ነው። ዘሩንም ለዓለምና ለዘለዓለም፥ ዙፋኑንም እንደ ሰማይ ዘመን አደርጋለሁ። ልጆቹ ግን ሕጌን ቢተዉ፥ በፍርዴም ባይሄዱ፥ ሥርዓቴንም ቢያረክሱ፥ ትእዛዜንም ባይጠብቁ፥ ኃጢአታቸውን በበትር፥ በደላቸውንም በመቅሠፍት እጐበኛታለሁ። ጽኑ ፍቅሩን ከእርሱ አላርቅም፥ በእውነቴም አልበድልም፥ ኪዳኔንም አላረክስም፥ ከከንፈሬም የወጣውን አልለውጥም። ዳዊትን በፍጹም እንዳልዋሸው አንድ ጊዜ በቅዱስነቴ ማልሁ። ዘሩ ለዘለዓለም፥ ዙፋኑም በፊቴ እንደ ፀሐይ ይኖራል። ለዘለዓለም እንደ ጨረቃ ይጸናል፥ ምስክርነቱ በደመና የታመነ ነው። አንተ ግን ናቅኸው ጣልኸውም፥ በቀባኸውም ላይ በቁጣ ተነሣህ። የአገልጋይህን ኪዳን አፈረስህ፥ ዘውዱንም በምድር አረከስህ። ቅጥሩን ሁሉ አፈራረስህ፥ አምባዎቹንም አጠፋህ። መንገድ አላፊም ሁሉ ዘረፈው፥ ለጎረቤቶቹም ስድብ ሆነ። የተቃዋሚዎቹን ቀኝ ከፍ ከፍ አደረግህ፥ ጠላቶቹንም ሁሉ ደስ አሰኘህ። የሰይፉንም ረድኤት መለስህ፥ በጦርነትም ውስጥ አልደገፍኸውም። በትረ መንግሥትን ሻርህ፥ ዙፋኑንም በምድር ላይ ጣልህ። ዕድሜውንም አሳጠርህ፥ በእፍረትም ሸፈንኸው። አቤቱ፥ እስከ መቼ ለዘለዓለም ፊትህን ትሰውራለህ? እስከ መቼስ ቁጣህ እንደ እሳት ይነድዳል? ጊዜዬ ምን ያህል ውስን መሆኑን አስታውስ፥ በውኑ የሰውን ልጅ ሁሉ ለከንቱ ፈጠርኸውን? ሕያው ሆኖ የሚኖር፥ ሞትንስ የማያይ ማን ነው? ነፍሱንስ ከሲኦል እጅ የሚያድን ማን ነው? ለዳዊት በእውነት የማልህ፥ አቤቱ፥ የቀድሞ ጽኑ ፍቅርህ ወዴት ነው? አቤቱ፥ የአገልጋዮችህን ስድብ፥ በእቅፌ ብዙ አሕዛብን የተቀበልሁትን፥ አቤቱ፥ ጠላቶችህን የሰደቡትን አንተ የቀባኸውን የሰደቡትን አስታውስ።