መዝሙር 78:40-59
መዝሙር 78:40-59 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በምድረ በዳ ስንት ጊዜ ዐመፁበት! በበረሓስ ምን ያህል አሳዘኑት! ደግመው ደጋግመው እግዚአብሔርን ተፈታተኑት፤ የእስራኤልንም ቅዱስ አስቈጡት። እነርሱን በዚያ ቀን ከጠላት የታደገበትን፣ ያን ኀይሉን አላስታወሱም፤ በግብጽ ያደረገውን ታምራዊ ምልክት፣ በጣኔዎስም በረሓ ያሳየውን ድንቅ ሥራ አላሰቡም። ወንዞቻቸውን ወደ ደም ለወጠ፤ ከጅረቶቻቸውም መጠጣት አልቻሉም። የዝንብ ሰራዊት ሰደደባቸው፤ ነደፏቸውም፤ ጓጕንቸርም ላከባቸው፤ ሰዎችንም አጠፉ። አዝመራቸውን ለኵብኵባ፣ ሰብላቸውንም ለአንበጣ ሰጠባቸው። የወይን ተክላቸውን በበረዶ፣ የበለስ ዛፋቸውንም በውርጭ አጠፋ። ከብቶቻቸውን ለበረዶ፣ የከብት መንጋቸውን ለመብረቅ እሳት ዳረገ። ጽኑ ቍጣውን በላያቸው ሰደደ፤ መዓቱን፣ የቅናቱን ቍጣና መቅሠፍቱን ላከባቸው፤ አጥፊ የመላእክት ሰራዊትም ሰደደባቸው። ለቍጣው መንገድ አዘጋጀ፤ ነፍሳቸውንም ከሞት አላተረፈም፤ ነገር ግን ሕይወታቸውን ለመቅሠፍት አሳልፎ ሰጠ። የዐፍላ ጕልበታቸው መጀመሪያ የሆኑትን በካም ድንኳን፣ በኵሮቻቸውንም ሁሉ በግብጽ ምድር ፈጀ። ሕዝቡን ግን እንደ በግ አወጣቸው፤ በምድረ በዳም እንደ መንጋ መራቸው። ያለ ሥጋት መራቸው፤ እነርሱም አልፈሩም፤ ጠላቶቻቸውን ግን ባሕር ዋጣቸው። ቀኝ እጁም ወዳስገኘችው ወደዚህ ተራራ፣ ወደ ቅድስት ምድር አገባቸው። ሕዝቦችን ከፊታቸው አባረረ፤ ምድራቸውን ርስት አድርጎ በገመድ አከፋፈላቸው፤ የእስራኤልንም ነገዶች በጠላቶቻቸው ቤት አኖረ። እነርሱ ግን አምላክን ተፈታተኑት፤ በልዑልም ላይ ዐመፁ፤ ትእዛዙንም አልጠበቁም። ተመልሰው እንደ አባቶቻቸው ከዳተኛ ሆኑ፤ እንደማያስተማምን ጠማማ ቀስት ተወላገዱ። በኰረብታ ማምለኪያዎቻቸው አስቈጡት፤ ተቀርጸው በተሠሩ ጣዖቶቻቸው አስቀኑት። እግዚአብሔር ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፤ እስራኤልንም ፈጽሞ ተወ።
መዝሙር 78:40-59 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በበረሓ ሳሉ ብዙ ጊዜ በእርሱ ላይ ዐመፁ፤ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ አሳዘኑት። በመደጋገም እግዚአብሔርን ተፈታተኑት፤ የእስራኤልንም ቅዱስ አሳዘኑት። እነርሱን ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳነበትን ቀንና ታላቅ ኀይሉን አላስታወሱም። በግብጽ አገር በጾዓን ሜዳ ያደረጋቸውን ታላላቅ ሥራዎችና ተአምራቱን ዘነጉ። የወንዞቻቸውን ውሃ ወደ ደም ለወጠ፤ ስለዚህ ግብጻውያን ከወንዞቻቸው ውሃ መጠጣት አልቻሉም። እነርሱን የሚያሠቃዩ ዝንቦችንና ጥፋትን የሚያስከትሉ እንቊራሪቶችን ወደ እነርሱ ላከ። ሰብላቸውን ለኩብኩባ፥ ምርታቸውንም ለአንበጣ ሰጠ። የወይን ተክሎቻቸውን በበረዶ፥ የበለስ ዛፎቻቸውንም በውርጭ አጠፋ። ከብቶቻቸውን በበረዶ፥ በጎቻቸውንም በመብረቅ ገደለ። የጥፋት መልእክተኞች ቡድን የሆኑትን አስፈሪውንና ኀይለኛ ቊጣውን፥ ማዋረዱንና ማስጨነቁን ላከባቸው። ለቊጣው መንገድን አዘጋጀ፤ ከሞትም አላዳናቸውም፤ ነገር ግን ለመቅሠፍት አሳልፎ ሰጣቸው። የካምን ልጆች የመጀመሪያ የወንድነት ፍሬ፥ በግብጽ በኲሮችን ሁሉ ገደለ። ሕዝቡን አውጥቶ እንደ በጎች አሰማራቸው፤ በበረሓም እንደ በግ መንጋ መራቸው። በሰላም ስለ መራቸው አልፈሩም፤ ነገር ግን ባሕሩ ተጥለቅልቆ ጠላቶቻቸውን አሰጠማቸው። ወደ ተቀደሰችው ምድሩ፥ በኀይሉ ወደያዛት ወደ ተራራማዋ አገር አመጣቸው። ከእነርሱ በፊት አሕዛብን አባረረ፤ ምድራቸውንም ርስት አድርጎ ለእስራኤል ነገዶች አከፋፈለ፤ ቤቶቻቸውንም ለራሱ ሕዝብ ሰጠ። የእርሱ ሕዝቦች ግን በልዑል እግዚአብሔር ላይ ዐመፁ፤ ተፈታተኑትም፤ ትእዛዞቹንም አልፈጸሙም። ይልቁንም እንደ አባቶቻቸው ዐመፀኞችና ከዳተኞች ሆኑ፤ እንደ ተጣመመ ፍላጻ የማያስተማምኑ ሆኑ። የአሕዛብ አምልኮ በሚፈጽሙባቸው ስፍራዎቻቸው እግዚአብሔርን አስቈጡት፤ በጣዖቶቻቸውም አስቀኑት። እግዚአብሔርም በሰማ ጊዜ ተቈጣ፤ ሕዝቡንም ፈጽሞ ተዋቸው።
መዝሙር 78:40-59 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በምድረ በዳ ምን ያህል አስቈጡት፥ በበረሃም አሳዘኑት። መላልሰው፥ እግዚአብሔርንም ተፈታተኑት፥ የእስራኤልንም ቅዱስ አሳዘኑት። እነርሱም እጁን አላሰቡም፥ ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳነበትን ቀን፥ በግብጽ ያደረገውን ተኣምራቱን፥ በጾዓን አገር ያደረገውን ድንቁን። ወንዞቻቸውንም ወደ ደም ለወጠ፥ ምንጮቻቸውን እንዳይጠጡ። ዝንቦችንም በላያቸው ሰደደባቸው፥ በሉአቸውም፥ በጓጉንቸርም አጠፋቸው። ሰብላቸውን ለኩብኩባ፥ ምርታቸውንም ለአንበጣ ሰጠ። ወይናቸውን በበረዶ፥ በለሳቸውንም በአመዳይ አጠፋ። እንስሶቻቸውን ለበረዶ፥ ሀብታቸውንም ለመብረቅ ሰጠ። የቁጣውን ንዳድ በላያቸው ሰደደ፥ መቅሠፍትን መዓትንም መከራንም በክፉዎች መላእክት ሰደደ። ለቁጣው መንገድን ጠረገ፥ ነፍሳቸውንም ከሞት አላዳናትም፥ ሕይወታቸውንም ለመቅሰፍት አሳልፎ ሰጠ። በኩሮቻቸውን ሁሉ በግብጽ፥ የድካማቸውንም መጀመሪያ በካም ድንኳኖች መታ። ሕዝቡን ግን እንደ በጎች አሰማራቸው፥ እንደ መንጋም በምድረ በዳ መራቸው። በተስፋም መራቸው አልፈሩምም፥ ጠላቶቻቸውንም ባሕር ደፈናቸው። ወደ መቅደሱም ተራራ አገባቸው፥ ቀኙ ወደ ገዛችው ወደዚህች ተራራ፥ ከፊታቸውም አሕዛብን አባረረ፥ ርስቱንም በገመድ አካፈላቸው፥ የእስራኤልንም ወገኖች በድንኳናቸው አኖረ። ነገር ግን ልዑል እግዚአብሔርን ፈተኑት፥ ዐመፁበትም፥ ትእዛዙንም አልጠበቁም፥ ተመለሱም እንደ አባቶቻቸውም ከዱ፥ እንደ ጠማማ ቀስትም ተገለበጡ፥ በኰረብታ መስገጃዎቻቸውም አስቈጡት፥ በተቀረጹ ምስሎቻቸውም አስቀኑት። እግዚአብሔርም ይህን ሰምቶ ተቈጣ፥ እስራኤልንም ፈጽሞ ተወ፥