የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙር 78:21-33

መዝሙር 78:21-33 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እግዚአብሔር ይህን ሲሰማ፣ እጅግ ተቈጣ፤ በያዕቆብም ላይ እሳት ነደደ፤ ቍጣውም በእስራኤል ላይ ተነሣ፤ በእግዚአብሔር አላመኑምና፤ በርሱም ማዳን አልታመኑም። እርሱ ግን ከላይ ደመናትን አዘዘ፤ የሰማይንም ደጆች ከፈተ፤ ይበሉም ዘንድ መና አዘነበላቸው፤ የሰማይንም መብል ሰጣቸው። ሰዎች የኀያላንን እንጀራ በሉ፤ ጠግበው እስከሚተርፍ ድረስ ምግብ ላከላቸው። የምሥራቁን ነፋስ ከሰማይ አስነሣ፤ የደቡብንም ነፋስ በኀይሉ አመጣ። ሥጋን እንደ ዐፈር፣ የሚበሩትን ወፎች እንደ ባሕር አሸዋ አዘነበላቸው፤ በሰፈራቸውም ውስጥ፣ በድንኳናቸው ዙሪያ አወረደ። እነርሱም እስኪጠግቡ ድረስ በሉ፤ እጅግ የጐመጁትን ሰጥቷቸዋልና። ነገር ግን ገና ምኞታቸውን ሳያረኩ፣ ምግቡ ገና በአፋቸው ውስጥ እያለ፣ የእግዚአብሔር ቍጣ በላያቸው ላይ መጣ፤ ከመካከላቸውም ብርቱ ነን ባዮችን ገደለ፤ የእስራኤልንም አበባ ወጣቶች ቀጠፈ። ይህም ሁሉ ሆኖ በበደላቸው ገፉበት፤ ድንቅ ሥራዎቹንም አላመኑም። ስለዚህ ዘመናቸውን በከንቱ፣ ዕድሜያቸውንም በድንጋጤ ጨረሰ።

መዝሙር 78:21-33 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እግዚአብሔር ይህን በሰማ ጊዜ በጣም ተቈጣ፤ በያዕቆብ ልጆች ላይ እሳቱ ነደደ፤ በእስራኤልም ላይ ቊጣው ተቀጣጠለ። ይህም የሆነው በእርሱ ስላላመኑና እንደሚያድናቸውም ስላልተማመኑበት ነው። ሆኖም ከላይ ያሉትን ሰማያትን አዘዘ፤ የሰማይንም በሮች ከፈተ። ይበሉት ዘንድ ለሕዝቡ መናን አዘነበላቸው፤ የሰማይንም ምግብ ሰጣቸው። በዚህ ዐይነት ሰዎች የመላእክትን እንጀራ በሉ፤ እግዚአብሔር የሚፈልጉትን ምግብ ሁሉ ሰጣቸው። የምሥራቅ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ፤ በኀይሉም የደቡብን ነፋስ አንቀሳቀሰ። ብዙ ሥጋ እንደ አፈር፥ ብዙ ድርጭቶችንም እንደ ባሕር አሸዋ ለሕዝቡ አዘነበላቸው። በሰፈራቸው መካከል በድንኳኖች ዙሪያ ድርጭቶችን አወረደላቸው። ስለዚህ ሕዝቡ በልተው ጠገቡ፤ እግዚአብሔር የተመኙትን ሁሉ ሰጣቸው። ይህም ሁሉ ሆኖ መጐምጀታቸው ሳይገታና ምግባቸውም ገና በአፋቸው ሳለ፥ የእግዚአብሔር ቊጣ በእነርሱ ላይ ተነሣ፤ የእስራኤልን ኀያላን ሰዎች ገደለ፤ ምርጥ ወጣቶችንም በአጭሩ ቀጨ። ይህም ሁሉ ሆኖ ሕዝቡ ኃጢአት ከመሥራት ገና አልተገታም፤ ብዙ ተአምራት ቢያሳያቸውም በእርሱ አላመኑም። ስለዚህ ዕድሜአቸውን እንደ እስትንፋስ አሳጠረ፤ ሕይወታቸውም በሽብር እንዲያልቅ አደረገ።