መዝሙር 77:10-20
መዝሙር 77:10-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የእግዚአብሔርን ኪዳን አልጠበቁምና፥ በሕጉም ለመሄድ እንቢ አሉ፤ ረድኤቱንና ያሳያቸውን ተአምራቱን ረሱ፥ በግብጽ ሀገርና በጣኔዎስ በረሃ በአባቶቻቸው ፊት የሠራውን ተአምራት። ባሕርን ከፍሎ አሳለፋቸው፤ ውኆችን እንደ ረዋት ውኃ አቆመ። ቀን በደመና መራቸው፥ ሌሊቱንም ሁሉ በእሳት ብርሃን። ዓለቱን በምድረ በዳ ሰነጠቀ፤ ከብዙ ጥልቅ እንደሚገኝ ያህል አጠጣቸው። ውኃንም እንደ ወንዞች አፈሰሰ። ውኃንም ከዓለት አፈለቀ፥ ነገር ግን እርሱን መበደልን እንደገና ደገሙ፥ ልዑልንም በምድረ በዳ አስመረሩት። ለነፍሳቸው መብልን ይፈልጉ ዘንድ፥ እግዚአብሔርን በልባቸው ፈተኑት። እግዚአብሔርን እንዲህ ብለው አሙት፦ “እግዚአብሔር በምድረ በዳ ማዕድን ያሰናዳ ዘንድ ዓለቱን ይመታ ዘንድ ውኃንም ያፈስ ዘንድ ይችላልን? እንጀራን መስጠትና ለሕዝቡስ ማዕድን መሥራት ይችላልን?”
መዝሙር 77:10-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እኔም፣ “የልዑል ቀኝ እጅ እንደ ተለወጠ ማሰቤ፣ ይህ ድካሜ ነው” አልሁ። የእግዚአብሔርን ሥራ አስታውሳለሁ፤ የጥንት ታምራትህን በርግጥ አስታውሳለሁ፤ ሥራህን ሁሉ አሰላስላለሁ፤ ድንቅ ሥራህን ሁሉ አውጠነጥናለሁ። አምላክ ሆይ፤ መንገድህ ቅዱስ ነው፤ እንደ አምላካችን ያለ ታላቅ አምላክ ማን ነው? ታምራትን የምታደርግ አምላክ አንተ ነህ፤ በሕዝቦችም መካከል ኀይልህን ትገልጣለህ። የያዕቆብንና የዮሴፍን ልጆች፣ ሕዝብህን በክንድህ ተቤዠሃቸው። ሴላ አምላክ ሆይ፤ ውሆች አዩህ፤ ውሆች አንተን አይተው ተሸማቀቁ፤ ጥልቆችም ተነዋወጡ። ደመናት ውሃን አንጠባጠቡ፤ ሰማያት አንጐደጐዱ፤ ፍላጾችህም ዙሪያውን አብለጨለጩ። የነጐድጓድህ ድምፅ በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ተሰማ፤ መብረቅህ ዓለምን አበራው፤ ምድርም ራደች፤ ተንቀጠቀጠች። መንገድህ በባሕር ውስጥ ነው፤ መሄጃህም በታላቅ ውሃ ውስጥ ነው፤ ዱካህ ግን አልታወቀም። በሙሴና በአሮን እጅ፣ ሕዝብህን እንደ በግ መንጋ መራኸው።
መዝሙር 77:10-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! እኔን ያስጨነቀኝ በታላቁ ኀይልህ እኛን ከመርዳት ማቆምህ ነው። እግዚአብሔር ሆይ! ያከናወንካቸውን ታላላቅ ሥራዎች አስታውሳለሁ፤ ባለፉት ዘመናት ያደረግኻቸው ተአምራት ትዝ ይሉኛል። ሥራዎችህን በጥሞና አሰላስላለሁ፤ ለድርጊቶችህም ከፍ ያለ ግምት እሰጣለሁ። አምላክ ሆይ፥ አንተ የምታደርገው ሁሉ ቅዱስ ነው፤ እንደ አንተ ያለ ታላቅ አምላክ ማነው? ተአምራትን የምታደርግ አምላክ አንተ ነህ፤ አንተ በሕዝቦች መካከል ኀይልህን አሳይተሃል። በኀይልህ የያዕቆብና የዮሴፍ ዘሮች የሆኑትን ሕዝብህን ተቤዥተሃል። አምላክ ሆይ! ውሃው አንተን ባየ ጊዜ ፈራ፤ ጥልቅ ባሕሮችም ተንቀጠቀጡ። ደመናዎች ዝናብን አዘነቡ፤ ነጐድጓድ በሰማይ አስገመገመ፤ የመብረቅ ፍላጻዎችህም ከላይ ከሰማይ አንጸባረቁ። የነጐድጓድህ ጩኸት በዐውሎ ነፋስ አስተጋባ፤ የመብረቅ ብልጭታ ዓለምን አበራ፤ ምድር ተናወጠች፥ ተንቀጠቀጠችም። መንገድህ በባሕር መካከል ነበር፤ ያለፍከውም በታላላቅ ወንዞች በኩል ነበር፤ ነገር ግን የእግርህ ዱካ አልተገኘም። እረኛ የበጎችን መንጋ እንደሚመራ፥ አንተም በሙሴና በአሮን አማካይነት ሕዝብህን መራህ።
መዝሙር 77:10-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እግዚአብሔርስ ማዘኑን ረሳን? በቁጣውስ ርኅራኄውን ዘጋውን? ይህ ድካሜ ነው አልሁ፥ የልዑል ቀኝ መለወጡ። የጌታን ሥራ አስታወስሁ፥ የቀደመውን ተኣምራትህን አስታወሳለሁና፥ በምግባርህም ሁሉ እናገራለሁ፥ ሥራህንም አሰላስላለሁ። አቤቱ፥ መንገድህ በመቅደስ ውስጥ ነው፥ እንደ እግዚአብሔር ያለ ታላቅ አምላክ ማን ነው? ተኣምራትን የምታደርግ አምላክ አንተ ነህ። ለሕዝብህ ኃይልህን አስታወቅሃቸው። የያዕቆብንና የዮሴፍን ልጆች፥ ሕዝብህን በክንድህ አዳንሃቸው። አቤቱ፥ ውኆች አዩህ፥ ውኆችም አይተውህ ፈሩ፥ ጥልቆችም ተነዋወጡ። ደመኖች ውሃን አዘነቡ፥ ደመኖች ድምፅን ሰጡ፥ ፍላጾችህም በየአቅጣጫው ወጡ። የነጐድጓድህ ድምፅ በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ነበረ፥ መብረቆች ለዓለም አበሩ፥ ምድር ተናወጠች ተንቀጠቀጠችም። መንገድህ በባሕር ውስጥ ነው፥ ያለፍከውም ኃይለኛ ውኆች በኩል ነው፤ ዱካህ ግን አልታወቀም።