መዝሙር 74:10-14
መዝሙር 74:10-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አምላክ ሆይ፤ ጠላት የሚያሾፈው እስከ መቼ ነው? ባላንጣስ ለዘላለም በስምህ ያላግጣልን? እጅህን ለምን ትሰበስባለህ? ቀኝ እጅህን ለምን በብብትህ ሥር ታቈያለህ? አምላክ ሆይ፤ አንተ ከጥንት ጀምሮ ንጉሤ ነህ፤ በምድር ላይ ማዳንን አደረግህ። ባሕርን በኀይልህ የከፈልህ አንተ ነህ፤ የባሕሩንም አውሬ ራሶች በውሃ ውስጥ ቀጠቀጥህ። የሌዋታንን ራሶች አደቀቅህ፤ ለምድረ በዳ ፍጥረታትም ምግብ አድርገህ የሰጠሃቸው፣
መዝሙር 74:10-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አምላክ ሆይ! ጠላቶች በአንተ ላይ የሚሳለቁት እስከ መቼ ነው? ስምህንስ የሚዳፈሩት ያለማቋረጥ ነውን? ለምን አትቀጣቸውም? ለምንስ ዝም ብለህ ትተዋቸዋለህ? አምላክ ሆይ! ከጥንት ጀምሮ ንጉሣችን አንተ ነህ፤ በምድርም ላይ ደኅንነትን አመጣህ፤ በታላቁ ኀይልህ ባሕሩን ከፈልክ፤ በባሕር የሚኖሩትን የታላላቅ አውሬዎች ራስ ቀጠቀጥክ፤ ሌዋታን የተባለውን የባሕር ዘንዶ ራስ ቀጠቀጥህ፤ ሥጋውንም በበረሓ ለሚኖሩ ፍጥረቶች ምግብ አድርገህ ሰጠሃቸው።
መዝሙር 74:10-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ ጠላት እስከ መቼ ይሳደባል? ስምህን ጠላት ለሁልጊዜ ያቃልላልን? እጅህንም ለምን ትመልሳለህ? ቀኝ እጅህንም ለምን በብብትህ መካከል ታቆያለህ? እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፥ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ። አንተ ባሕርን በኃይልህ ከፈልካት፥ የአውሬዎችን ራስ በውኃ ውስጥ ሰበርህ። አንተ የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ፥ ለኢትዮጵያ ሰዎችም እንደ ምግብ ሰጠሃቸው።