የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙር 74:1-11

መዝሙር 74:1-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አምላክ ሆይ፤ ለዘላለም የጣልኸን ለምንድን ነው? በማሰማሪያህ ባሉ በጎችህስ ላይ ቍጣህ ለምን ነደደ? ጥንት ገንዘብህ ያደረግሃትን ጉባኤ፣ የዋጀሃትን የርስትህን ነገድ፣ መኖሪያህ ያደረግሃትን የጽዮን ተራራ ዐስብ። ርምጃህን ለዘላለሙ ባድማ ወደ ሆነው አቅና፤ ጠላት በመቅደስህ ውስጥ ያለውን ሁሉ አበላሽቷል። ጠላቶችህ በመገናኛ ስፍራህ መካከል ደነፉ፤ አርማቸውንም ምልክት አድርገው በዚያ አቆሙ። በጫካ መካከል ዛፎችን ለመቍረጥ፣ መጥረቢያ የሚያነሣ ሰው መሰሉ። ጥበበ እድ ያጌጠውን ሥራ ሁሉ፣ በመጥረቢያና በመዶሻ ሰባበሩት። መቅደስህን አቃጥለው አወደሙት፤ የስምህንም ማደሪያ አረከሱ። በልባቸውም፣ “ፈጽሞ እንጨቍናቸዋለን” አሉ፤ እግዚአብሔር በምድሪቱ ላይ የተመለከበትን ስፍራ ሁሉ አቃጠሉ። የምናየው ምልክት የለም፤ ከእንግዲህ የሚነሣ አንድም ነቢይ የለም፤ ይህ እስከ መቼ እንደሚቀጥል የሚያውቅ በእኛ ዘንድ የለም። አምላክ ሆይ፤ ጠላት የሚያሾፈው እስከ መቼ ነው? ባላንጣስ ለዘላለም በስምህ ያላግጣልን? እጅህን ለምን ትሰበስባለህ? ቀኝ እጅህን ለምን በብብትህ ሥር ታቈያለህ?

መዝሙር 74:1-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

አምላክ ሆይ! እንደዚህ ለምን ተውከን? ሕዝብህንስ የምትቈጣው ለዘለዓለም ነውን? ከጥንት ጀምሮ የመረጥከውን፥ የራስህ ወገን እንዲሆን ከባርነት የዋጀኸውን ሕዝብህን አስታውስ፤ ከዚህ በፊት መኖሪያህ ያደረግኸውን የጽዮንን ተራራ አስብ። በጠላቶቻችን ለዘለቄታ የፈራረሰውን ቤተ መቅደሱን ተዘዋውረህ ተመልከትልን። ጠላቶችህ “ድል አደረግን” ብለው በቤተ መቅደስህ ውስጥ ይደነፋሉ፤ በዚያም የድል ምልክት የሆነውን ዐርማቸውን ተክለዋል። እነርሱ እንጨቶችን በመጥረቢያ እንደሚቈርጡ የደን እንጨት ቈራጮችን ይመስላሉ። የግድግዳዎችዋን ጌጣ ጌጦች በመጥረቢያና በመዶሻ ሰባበሩ። መቅደስህን አፍርሰው በእሳት አቃጠሉት፤ ስምህ የሚጠራበትን ቦታ በመሬት ላይ ጥለው አረከሱት። እነርሱም “ኑ በሥልጣናችን ሥር እናድርጋቸው” አሉ። በሀገሪቱ ያሉትን የተቀደሱ ቦታዎችን ሁሉ አቃጠሉ። ከእንግዲህ ወዲህ ተአምራት አይኖሩም፤ ነቢያትም አይኖሩም፤ ይህ ሁኔታ እስከ መቼ እንደሚቈይ ከእኛ መካከል ማን ያውቃል? አምላክ ሆይ! ጠላቶች በአንተ ላይ የሚሳለቁት እስከ መቼ ነው? ስምህንስ የሚዳፈሩት ያለማቋረጥ ነውን? ለምን አትቀጣቸውም? ለምንስ ዝም ብለህ ትተዋቸዋለህ?

መዝሙር 74:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

አቤቱ፥ ስለምን ለሁልጊዜ ጣልኸኝ? በማሰማርያህ በጎች ላይስ ቁጣህ ስለምን ጨሰ? አስቀድመህ የፈጠርሃትን ማኅበርህን፥ የተቤዠሃትንም የርስትህን በትር፥ በእርሷ ያደርህባትን የጽዮንን ተራራ አስብ። መጠን ወደሌላቸው ፍርስራሶች እርምጃህን አቅና፥ ጠላት በመቅደስ ያለውን ሁሉ አጥፍቶአል። ጠላቶችህ በአደባባይህ ላይ አገሡ፥ ለድል ምልክት ዐላማቸውን አኖሩ። በላይኛው መግቢያ ውስጥ፥ በዱር፥ በመጥረቢያ እንጨቶችን የሚቆርጡ ሰዎችን ይመስላሉ። እንዲሁ በመጥረቢያና በመዶሻ ሰበሩአት። መቅደስህን በእሳት አቃጠሉ፥ የስምህንም ማደሪያ በምድር ውስጥ አረከሱ። አንድ ሆነው በልባቸው በየሕዝባቸው፦ ኑ፥ የእግዚአብሔርን የተቀድሱ ቦታዎችን አቃጠሉ። ምልክታችንን አናይም ከእንግዲህ ወዲህም ነቢይ አይኖርም፥ ይህም እስከ መቼ እንደሚቆይ የሚያውቅ በኛ ዘንድ የለም። አቤቱ፥ ጠላት እስከ መቼ ይሳደባል? ስምህን ጠላት ለሁልጊዜ ያቃልላልን? እጅህንም ለምን ትመልሳለህ? ቀኝ እጅህንም ለምን በብብትህ መካከል ታቆያለህ?