መዝሙር 69:1-15
መዝሙር 69:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አምላክ ሆይ፤ አድነኝ፤ ውሃ እስከ ዐንገቴ ደርሶብኛልና። የእግር መቆሚያ በሌለው፣ በጥልቅ ረግረግ ውስጥ ሰጥሜአለሁ፤ ወደ ጥልቅ ውሃ ገባሁ፤ ሞገዱም አሰጠመኝ። በጩኸት ደከምሁ፤ ጕረሮዬም ደረቀ፤ አምላኬን በመጠባበቅ፣ ዐይኖቼ ፈዘዙ። ያለ ምክንያት የሚጠሉኝ፣ ከራሴ ጠጕር በዙ፤ ሕይወቴን ለማጥፋት የሚፈልጉ፣ በከንቱም የሚጠሉኝ ብዙዎች ሆኑ፤ ያልሰረቅሁትን ነገር፣ መልሰህ አምጣ ተባልሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ቂልነቴን ታውቃለህ፤ በደሌም ከአንተ የተሰወረ አይደለም። ጌታ እግዚአብሔር የሰራዊት ጌታ ሆይ፤ አንተን ተስፋ የሚያደርጉ፣ በእኔ ምክንያት አይፈሩ፤ የእስራኤል አምላክ ሆይ፤ አንተን አጥብቀው የሚሹ፣ ከእኔ የተነሣ አይዋረዱ። ስለ አንተ ስድብን ታግሻለሁና፤ ዕፍረትም ፊቴን ሸፍኗልና። ለወንድሞቼ እንደ ባዕድ፣ ለእናቴም ልጆች እንደ እንግዳ ሆንሁባቸው። የቤትህ ቅናት በላችኝ፤ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ዐርፏል። ነፍሴን በጾም ባስመረርሁ ጊዜ፣ እነርሱ ሰደቡኝ። ማቅ በለበስሁ ጊዜ፣ መተረቻ አደረጉኝ። በቅጥሩ ደጅ ለሚቀመጡት የመነጋገሪያ ርእስ፣ ለሰካራሞችም መዝፈኛ ሆንሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔ ግን በወደድኸው ሰዓት፣ ወደ አንተ እጸልያለሁ፤ አምላክ ሆይ፤ በታላቅ ምሕረትህ፣ በማዳንህም ርግጠኛነት መልስልኝ። ከረግረግ አውጣኝ፤ እሰጥም ዘንድ አትተወኝ፤ ከጥልቅ ውሃ፣ ከእነዚያ ከሚጠሉኝ ታደገኝ። ጐርፍ አያጥለቅልቀኝ፤ ጥልቅ ውሃም አይዋጠኝ፤ ጕድጓዱም ተደርምሶ አይዘጋብኝ።
መዝሙር 69:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የውሃ ሙላት እስከ አንገቴ ስለ ደረሰ፤ አምላክ ሆይ! አድነኝ! መቆሚያ ስፍራ ስለ አጣሁ በጥልቅ ረግረግ ውስጥ ለመስረግ ተቃርቤአለሁ፤ በጥልቅ ውሃ ውስጥ እገኛለሁ፤ ውሃ ሙላት ሊያሰጥመኝ ተቃርቦአል። ከመጮኼ ብዛት የተነሣ ደከምኩ፤ ጒሮሮዬም ቈሰለ፤ አምላኬን በመጠባበቅ ዐይኖቼ ፈዘዙ። ያለ ምክንያት የሚጠሉኝ ከራሴ ጠጒር ይልቅ በዝተዋል፤ ብዙዎች ጠላቶቼ ሊያጠፉኝ ይፈልጋሉ ያልሰረቅኹትን ነገር መመለስ አለብኝን? አምላክ ሆይ! ሞኝነቴን አንተ ታውቃለህ፤ ኃጢአቴ ከአንተ የተሰወረ አይደለም። የእስራኤል አምላክ ሆይ! አንተን ተስፋ የሚያደርጉ በእኔ ምክንያት አይፈሩ፤ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! አንተን የሚፈልጉ በእኔ ምክንያት አይዋረዱ። ስለ አንተ ስድብን ታግሼአለሁ፤ ኀፍረትም ፊቴን ሸፍኖታል። በወንድሞቼ መካከል እንግዳ፥ በእናቴም ልጆች መካከል ባይተዋር ሆንኩ። ለቤትህ ያለኝ ቅናት በውስጤ እንደ እሳት ይነዳል፤ በአንተ ላይ የተሰነዘረው ስድብ በእኔ ላይ ዐረፈ። በምጾምበት ጊዜ በጣም አለቀስኩ፤ በዚህም ተሰደብኩ። የሐዘን ልብስ ስለብስ እየተዘባበቱ ይስቁብኛል። በአደባባይ የሚቀመጡት ያሙኛል። ሰካራሞች በዘፈን ይሰድቡኛል። እግዚአብሔር ሆይ! እኔ ግን ወደ አንተ እጸልያለሁ፤ አንተ በመረጥከው ጊዜ ጸሎቴን መልሰህ፥ በዘለዓለማዊው ፍቅርህ ማዳንህን አረጋግጥልኝ። በረግረግ ውስጥ ከመስረግ አድነኝ፤ ከጠላቶቼም ጠብቀኝ፤ በጥልቅ ውሃም ከመስጠም አድነኝ። ጐርፍ እንዳይወስደኝ፥ ጥልቅ ባሕር እንዳያሰጥመኝ፥ መቃብር እንዳይውጠኝ ጠብቀኝ።
መዝሙር 69:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ ውኃ እስከ ነፍሴ ደርሶብኛልና አድነኝ። በጥልቅ ረግረግ ጠለቅሁ መቆሚያም የለኝም። ወደ ጥልቅ ባሕር ገባሁ ማዕበልም አሰጠመኝ። በጩኸት ደከምሁ ጉሮሮዬም ሰለለ፥ አምላኬን ስጠብቅ ዐይኖቼ ፈዘዙ። በከንቱ የሚጠሉኝ ከራሴ ጠጉር በዙ፥ በዓመፅ ያሚያሳድዱኝ ጠላቶቼ በረቱ፥ በዚያን ጊዜ ያልቀማሁትን መለስሁ። አቤቱ፥ አንተ ቅብጠቴን ታውቃለህ፥ ጥፋቴም ከአንተ አልተሰወረም። አቤቱ የሠራዊት አምላክ፥ ተስፋ የሚያደርጉህ በእኔ አይፈሩ፥ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ የሚሹህ በእኔ አይነወሩ። ስለ አንተ ስድብን ታግሻለሁና፥ እፍረትም ፊቴን ሸፍናለችና። ለወንድሞቼ እንደ ሌላ፥ ለእናቴ ልጆችም እንደ እንግዳ ሆንሁባቸው። የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና፥ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና። ነፍሴን በጾም አስመረርሁአት፥ ለስድብም ሆነብኝ። ማቅ ለበስሁ ምሳሌም ሆንሁላቸው። በደጅ የሚቀመጡ በእኔ ይጫወታሉ፥ ሰካራሞች በእኔ ላይ ይዘፍናሉ። አቤቱ፥ በመልካሙ ጊዜ ጸሎቴ ወደ አንተ ነው፥ አቤቱ፥ በቸርነትህ ብዛት በማዳንህም እውነት አድምጠኝ። እንዳይውጠኝ ከረግረግ አውጣኝ፥ ከሚጠሉኝና ከጥልቅ ውኃ አስጥለኝ።