የውሃ ሙላት እስከ አንገቴ ስለ ደረሰ፤ አምላክ ሆይ! አድነኝ! መቆሚያ ስፍራ ስለ አጣሁ በጥልቅ ረግረግ ውስጥ ለመስረግ ተቃርቤአለሁ፤ በጥልቅ ውሃ ውስጥ እገኛለሁ፤ ውሃ ሙላት ሊያሰጥመኝ ተቃርቦአል። ከመጮኼ ብዛት የተነሣ ደከምኩ፤ ጒሮሮዬም ቈሰለ፤ አምላኬን በመጠባበቅ ዐይኖቼ ፈዘዙ። ያለ ምክንያት የሚጠሉኝ ከራሴ ጠጒር ይልቅ በዝተዋል፤ ብዙዎች ጠላቶቼ ሊያጠፉኝ ይፈልጋሉ ያልሰረቅኹትን ነገር መመለስ አለብኝን? አምላክ ሆይ! ሞኝነቴን አንተ ታውቃለህ፤ ኃጢአቴ ከአንተ የተሰወረ አይደለም። የእስራኤል አምላክ ሆይ! አንተን ተስፋ የሚያደርጉ በእኔ ምክንያት አይፈሩ፤ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! አንተን የሚፈልጉ በእኔ ምክንያት አይዋረዱ። ስለ አንተ ስድብን ታግሼአለሁ፤ ኀፍረትም ፊቴን ሸፍኖታል። በወንድሞቼ መካከል እንግዳ፥ በእናቴም ልጆች መካከል ባይተዋር ሆንኩ። ለቤትህ ያለኝ ቅናት በውስጤ እንደ እሳት ይነዳል፤ በአንተ ላይ የተሰነዘረው ስድብ በእኔ ላይ ዐረፈ። በምጾምበት ጊዜ በጣም አለቀስኩ፤ በዚህም ተሰደብኩ። የሐዘን ልብስ ስለብስ እየተዘባበቱ ይስቁብኛል። በአደባባይ የሚቀመጡት ያሙኛል። ሰካራሞች በዘፈን ይሰድቡኛል። እግዚአብሔር ሆይ! እኔ ግን ወደ አንተ እጸልያለሁ፤ አንተ በመረጥከው ጊዜ ጸሎቴን መልሰህ፥ በዘለዓለማዊው ፍቅርህ ማዳንህን አረጋግጥልኝ። በረግረግ ውስጥ ከመስረግ አድነኝ፤ ከጠላቶቼም ጠብቀኝ፤ በጥልቅ ውሃም ከመስጠም አድነኝ። ጐርፍ እንዳይወስደኝ፥ ጥልቅ ባሕር እንዳያሰጥመኝ፥ መቃብር እንዳይውጠኝ ጠብቀኝ።
መጽሐፈ መዝሙር 69 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መዝሙር 69:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos