መዝሙር 51:5-19
መዝሙር 51:5-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስወለድ ጀምሮ በደለኛ፣ ገና እናቴም ስትፀንሰኝ ኀጢአተኛ ነኝ። እነሆ፤ እውነትን ከሰው ልብ ትሻለህ፤ ስለዚህ ጥልቅ ጥበብን በውስጤ አስተምረኝ። በሂሶጵ እርጨኝ፤ እኔም እነጻለሁ፤ ዕጠበኝ፤ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ። ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ፤ ያደቀቅሃቸው ዐጥንቶቼም ደስ ይበላቸው። ፊትህን ከኀጢአቴ መልስ፤ በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ። አምላኬ ሆይ፤ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ ቀና የሆነውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። ከፊትህ አትጣለኝ፤ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድ። የማዳንህን ደስታ መልስልኝ፤ በእሽታ መንፈስም ደግፈህ ያዘኝ። እኔም ለሕግ ተላላፊዎች መንገድህን አስተምራለሁ፤ ኀጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ። የድነቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ደም ከማፍሰስ አድነኝ፤ አንደበቴም ስለ ጽድቅህ በእልልታ ይዘምራል። ጌታ ሆይ ከንፈሮቼን ክፈት፤ አፌም ምስጋናህን ያውጃል። መሥዋዕትን ብትወድድ ኖሮ ባቀረብሁልህ ነበር፤ የሚቃጠል መሥዋዕትም ደስ አያሰኝህም። እግዚአብሔር የሚቀበለው መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም። በበጎ ፈቃድህ ጽዮንን አበልጽጋት፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥሮች ሥራ። የጽድቅ መሥዋዕት፣ የሚቃጠል መሥዋዕትና ሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕት ያን ጊዜ ደስ ያሰኙሃል፤ ኰርማዎች በመሠዊያህ ላይ የሚሠዉትም ያን ጊዜ ነው።
መዝሙር 51:5-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከተፀነስኩበት ጊዜ ጀምሮ ኀጢአተኛ ነኝ፤ ከተወለድኩበትም ጊዜ ጀምሮ በደለኛ ነኝ። አንተ ቅንነትንና እውነትን ስለምትወድ የጥበብህን ምሥጢር አስተምረኝ። በሂሶጵ ቅጠል ረጭተህ ኃጢአቴን አስወግድልኝ፤ እኔም እነጻለሁ። እጠበኝ፤ እኔም ከበረዶ ይበልጥ ነጭ እሆናለሁ። የሰበርካቸውን አጥንቶቼን አድሰህ የደስታንና የሐሤትን ድምፅ አሰማኝ፤ ፊትህን ከኃጢአቴ መልስ፤ በደሌን ሁሉ ደምስስ። አምላክ ሆይ! ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፤ አዲስና የጸና መንፈስን ስጠኝ። ከፊትህ አታርቀኝ፤ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ አትውሰድብኝ። በአዳንኸኝ ጊዜ እንደ ሰጠኸኝ ዐይነቱን ደስታ ስጠኝ፤ ታዛዥ እንድሆን አድርገኝ ከዚህ በኋላ ትእዛዝህን ለሕግ ተላላፊዎች አስተምራለሁ፤ ኃጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ። አቤቱ አዳኜ አምላኬ ሆይ! ደም ከማፍሰስ አድነኝ፤ ስለ አዳኝነትህም የምስጋና መዝሙር እዘምራለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! እንድናገር እርዳኝ፤ እኔም አመሰግንሃለሁ። መሥዋዕት አያስደስትህም እንጂ ባቀረብኩልህ ነበር፤ የሚቃጠል መሥዋዕትም አያስደስትህም። ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት የተሰበረ ልብ ነው፤ እግዚአብሔር ሆይ አንተ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም። አምላክ ሆይ! ጽዮንን ለመርዳት፥ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች ለመገንባት እባክህ ፈቃድህ ይሁን። በዚያን ጊዜ በትክክለኛ መሥዋዕትና በሚቃጠል መሥዋዕት ትደሰታለህ፤ እኛም በመሠዊያህ ላይ እንደገና ኰርማዎችን እናቀርባለን።
መዝሙር 51:5-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፥ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና። አንተን ብቻ በደልሁ፥ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፥ በነገርህ ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ። እነሆ፥ በዓመፃ ተወለድሁ፥ እናቴም በኃጢአት ፀነሰችኝ። እነሆ፥ እውነትን ወደድህ፥ የማይታይ ስውር ጥበብን አስታወቅኸኝ። በሂሶጵ እርጨኝ፥ እነጻማለሁ፥ እጠበኝ፥ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ። ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ፥ የሰበርሃቸውም አጥንቶቼ ደስ ይላቸዋል። ከኃጢአቴ ፊትህን መልስ፥ በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ። አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ። የማዳንህን ደስታ መልስልኝ፥ በእሽታ መንፈስም ደግፈኝ። ለሕግ ተላላፎች መንገድህን አስተምራለሁ፥ ኃጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ። የመድኃኒቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ከደም አድነኝ፥ አንደበቴም በአንተ ጽድቅ ትደሰታለች። አቤቱ፥ ከንፈሮቼን ክፈት፥ አፌም ምስጋናህን ይናገራል። መሥዋዕትን ብትወድድስ በሰጠሁህ ነበር፥ የሚቃጠለውም መሥዋዕት ደስ አያሰኝህም። የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበርውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።