መጽሐፈ መዝሙር 51
51
ይቅርታን ለመለመን የቀረበ ጸሎት
1አምላክ ሆይ! ስለ ዘለዓለማዊ ፍቅርህ ይቅር በለኝ፤
ስለ ታላቁ ምሕረትህም
ኃጢአቴን ደምስስልኝ። #2ሳሙ. 12፥1-15።
2በደሌን ሁሉ አጥበህ አስወግድልኝ፤
ከኃጢአቴም አንጻኝ።
3እኔ ስሕተቴን ዐውቃለሁ፤
የኃጢአቴንም ብዛት ዘወትር እገነዘባለሁ።
4እኔ ያመፅኩት በአንተ ላይ ነው፤
የበደልኩትም አንተን ብቻ ነው፤
አንተ የምትጠላውን ነገር አደረግሁ፤
ስለዚህ በእኔ ላይ መፍረድህና
እኔንም መቅጣትህ ትክክል ነው። #ሮም 3፥4።
5ከተፀነስኩበት ጊዜ ጀምሮ ኀጢአተኛ ነኝ፤
ከተወለድኩበትም ጊዜ ጀምሮ በደለኛ ነኝ።
6አንተ ቅንነትንና እውነትን ስለምትወድ
የጥበብህን ምሥጢር አስተምረኝ።
7በሂሶጵ ቅጠል ረጭተህ ኃጢአቴን አስወግድልኝ፤
እኔም እነጻለሁ።
እጠበኝ፤ እኔም ከበረዶ ይበልጥ ነጭ እሆናለሁ።
8የሰበርካቸውን አጥንቶቼን አድሰህ
የደስታንና የሐሤትን ድምፅ አሰማኝ፤
9ፊትህን ከኃጢአቴ መልስ፤
በደሌን ሁሉ ደምስስ።
10አምላክ ሆይ! ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፤
አዲስና የጸና መንፈስን ስጠኝ።
11ከፊትህ አታርቀኝ፤
ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ አትውሰድብኝ።
12በአዳንኸኝ ጊዜ እንደ ሰጠኸኝ ዐይነቱን ደስታ ስጠኝ፤
ታዛዥ እንድሆን አድርገኝ
13ከዚህ በኋላ ትእዛዝህን ለሕግ ተላላፊዎች አስተምራለሁ፤
ኃጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ።
14አቤቱ አዳኜ አምላኬ ሆይ!
ደም ከማፍሰስ አድነኝ፤
ስለ አዳኝነትህም የምስጋና መዝሙር እዘምራለሁ።
15እግዚአብሔር ሆይ! እንድናገር እርዳኝ፤
እኔም አመሰግንሃለሁ።
16መሥዋዕት አያስደስትህም እንጂ ባቀረብኩልህ ነበር፤
የሚቃጠል መሥዋዕትም አያስደስትህም።
17ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት የተሰበረ ልብ ነው፤
እግዚአብሔር ሆይ አንተ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም።
18አምላክ ሆይ!
ጽዮንን ለመርዳት፥ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች ለመገንባት
እባክህ ፈቃድህ ይሁን።
19በዚያን ጊዜ በትክክለኛ መሥዋዕትና በሚቃጠል መሥዋዕት ትደሰታለህ፤
እኛም በመሠዊያህ ላይ እንደገና ኰርማዎችን እናቀርባለን።
Currently Selected:
መጽሐፈ መዝሙር 51: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997