መዝሙር 45:1-9
መዝሙር 45:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አምላካችን መጠጊያችንና ኀይላችን ነው፤ ባገኘን በታላቅ መከራም ጊዜ ረዳታችን ነው። ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፥ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢፈልሱ አንፈራም። ውኆቻቸው ጮኹ ደፈረሱም፥ ተራሮችም ከኀይሉ የተነሣ ተናወጡ። ፈሳሽ ወንዝ የእግዚአብሔርን ከተማ ደስ ያሰኛል፤ ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ። እንዳትታወክም እግዚአብሔር በመካከልዋ ነው፥ እግዚአብሔርም ፊት ለፊት ይረዳታል። አሕዛብ ደነገጡ ነገሥታትም ተመለሱ፤ ልዑል ቃሉን ሰጠ፥ ምድርም ተንቀጠቀጠች። የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ነው፤ የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው። የእግዚአብሔርን ሥራ፥ በምድር ያደረገውንም ተአምራት እንድታዩ ኑ። ከምድር ዳርቻ ጦርነትን ይሽራል፤ ቀስትን ይሰብራል፥ ጋሻንም ይቀጠቅጣል፥ በእሳትም የጦር መሣሪያን ያቃጥላል።
መዝሙር 45:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ልቤ መልካም ሐሳብ አፈለቀ፤ የተቀኘሁትን ቅኔ ለንጉሥ አሰማለሁ፤ አንደበቴም እንደ ባለሙያ ጸሓፊ ብርዕ ነው። አንተ ከሰዎች ሁሉ ይልቅ ውብ ነህ፤ ከንፈሮችህም የጸጋ ቃል ያፈልቃሉ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ለዘላለም ባርኮሃል። ኀያል ሆይ፤ ሰይፍህን በወገብህ ታጠቅ፤ ግርማ ሞገስንም ተላበስ። ስለ እውነት፣ ስለ ትሕትና፣ ስለ ጽድቅ ሞገስን ተጐናጽፈህ በድል አድራጊነት ገሥግሥ፤ ቀኝ እጅህም ድንቅ ተግባር ታሳይ። የሾሉ ፍላጻዎችህ በንጉሥ ጠላቶች ልብ ይሰካሉ፤ ሕዝቦችም ከእግርህ በታች ይወድቃሉ። አምላክ ሆይ፤ ዙፋንህ ከዘላለም እስከ ዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ይሆናል። ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፃን ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ፣ ከጓደኞችህ ይልቅ አንተን የደስታ ዘይት ቀባህ። ልብስህ ሁሉ በከርቤ፣ በአደስና በጥንጁት መዐዛ ያውዳል፤ በዝኆን ጥርስ ከተዋቡ ቤተ መንግሥቶችም፣ የበገናና የመሰንቆ ድምፅ ደስ ያሰኙሃል። ከተከበሩት ሴቶችህ መካከል የነገሥታት ሴቶች ልጆች ይገኛሉ፤ ንግሥቲቱም በኦፊር ወርቅ አጊጣ በቀኝህ ቆማለች።
መዝሙር 45:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ልቤ መልካም ርእስን ያፈልቃል፤ ጽሑፌም የሚያተኲረው በንጉሡ ላይ ነው፤ አንደበቴም እንደ መልካም ጸሐፊ ብዕር ነው። አንተ ከሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ የተዋብክ ነህ፤ ንግግርህም ሞገስ የሞላበት ነው፤ እግዚአብሔር ለዘለዓለም ባርኮሃል። በክብርና በግርማ የተሞላህ ኀያል ንጉሥ ሆይ፥ ሰይፍህን ታጠቅ። ስለ እውነትና ስለ ፍትሕ ግርማን ተጐናጽፈህ ድል ለማድረግ ገሥግሥ፤ ኀይልህም ታላላቅ ድሎችን ያስገኛል። ፍላጻዎችህ የተሳሉ ናቸው፤ የጠላቶችህንም ልብ ይወጋሉ፤ መንግሥታትም ተሸንፈው በእግርህ ሥር ይወድቃሉ። አምላክ ሆይ! ዙፋንህ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የጸና ነው። በትረ መንግሥትህም የፍትሕ በትረ መንግሥት ነው። አንተ መልካሙን ነገር ትወዳለህ፤ ክፉውን ነገር ትጠላለህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ መረጠህ፤ ከሌሎች ነገሥታትም ይበልጥ የደስታን ዘይት ቀባህ። ከከርቤ፥ ከእሬትና ከብርጒድ የተቀመመ ሽቶ በንጉሣዊ ልብስህ ላይ ተርከፍክፎአል፤ በዝሆን ጥርስ በተጌጠው ቤተ መንግሥትህም የበገና ሙዚቃ ቃና ያስደስትሃል። በቤተ መንግሥትህ ከሚገኙት ወይዛዝርት መካከል፥ የነገሥታት ሴቶች ልጆች ይገኛሉ፤ ንግሥቲቱም በንጹሕ ወርቅ ያሸበረቀ ጌጠኛ ልብስ ተጐናጽፋ ከዙፋንህ በስተቀኝ ቆማለች።
መዝሙር 45:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ልቤ መልካም ነገርን አፈለቀ፥ እኔ ሥራዬን ለንጉሥ እነግራለሁ፥ አንደበቴ እንደ ፈጣን ጸሓፊ ብርዕ ነው። ውበትህ ከሰው ልጆች ይልቅ ያምራል፥ ሞገስ በከንፈሮችህ ፈሰሰ፥ ስለዚህ እግዚአብሔር ለዘለዓለም ባረከህ። ኃያል ሆይ፥ በግርማህና በውበትህ ሰይፍህን በወገብህ ታጠቅ። ስለ ቅንነትና ስለ የዋህነት ስለ ጽድቅም አቅና ተከናወን ንገሥም፥ ቀኝህም በክብር ይመራሃል። ኃያል ሆይ፥ ፍላጻዎችህ የተሳሉ ናቸው፥ እነርሱም በንጉሥ ጠላቶች ልብ ውስጥ ይገባሉ፥ አሕዛብም በበታችህ ይወድቃሉ። አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ ለዘለዓለም ነው፥ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው። ጽድቅን ወደድህ ዓመፃንም ጠላህ፥ ስለዚህ ከባልንጀሮችህ ይልቅ እግዚአብሔር አምላክ የደስታ ዘይትን ቀባህ። በልብሶችህ ሁሉ ከርቤና ሽቱ ዝባድም አሉ፥ በዝሆን ጥርስ ከተዋቡ ቤተ መንግሥቶች ይልቅ የበገናና የመሰንቆ ድምጽ ደስ ያሰኙሃል።