መዝሙር 44:1-8
መዝሙር 44:1-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ልቤ መልካም ነገርን ተናገረ፥ እኔም ሥራዬን ለንጉሥ እናገራለሁ፤ አንደበቴ እንደ ፈጣን ጸሓፊ ብርዕ ነው። ውበቱ ከሰው ልጆች ይልቅ ያምራል፤ ሞገስ ከከንፈሮችህ ፈሰሰ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ለዘለዓለም ባረከህ። ኀያል ሆይ፥ በደም ግባትህና በውበትህ፥ ሰይፍህን በወገብህ ታጠቅ። ስለ ቅንነትና ስለ የዋህነት ስለ ጽድቅም አቅና፥ ተከናወን፥ ንገሥም፤ ቀኝህም በክብር ይመራሃል። ኀያል ሆይ፥ ፍላጻዎችህ የተሳሉ ናቸው፥ አሕዛብ በበታችህ ይወድቃሉ። በንጉሥ ጠላቶች ልብ ውስጥ ይገባሉ፥ አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ ለዘለዓለም ነው፤ በትረ መንግሥትህ የጽድቅ በትር ነው። ጽድቅን ወደድህ፥ ዐመፃንም ጠላህ፤ ስለዚህ ከባልንጀሮችህ ይልቅ እግዚአብሔር አምላክህ የደስታ ዘይትን ቀባህ። ከርቤና ሽቱ ዝባድም በልብሶችህ ናቸው።
መዝሙር 44:1-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አምላክ ሆይ፤ በጆሯችን ሰምተናል፤ አባቶቻችን በቀድሞ ዘመን፣ እነርሱ በነበሩበት ዘመን፣ ያደረግኸውን ነግረውናል። ሕዝቦችን በእጅህ አሳድደህ አወጣሃቸው፤ አባቶቻችንን ግን ተከልሃቸው፤ ሕዝቦችን አደቀቅህ፤ አባቶቻችንን ግን ነጻ አወጣሃቸው። ምድሪቱን የወረሱት በሰይፋቸው አልነበረም፤ ድልንም የተጐናጸፉት በክንዳቸው አይደለም፤ አንተ ወድደሃቸዋልና ቀኝ እጅህ፣ ክንድህና የፊትህ ብርሃን ይህን አደረገ። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ንጉሤ ነህ፤ ያዕቆብም ድል እንዲያደርግ የወሰንህ አንተ ነህ። በአንተ ጠላቶቻችን በመጡበት እንዲመለሱ እናደርጋለን፤ በስምህም ባላጋራዎቻችንን ከእግራችን በታች እንረግጣለን። በቀስቴ አልተማመንም፤ ሰይፌም አያስጥለኝም። አንተ ግን በጠላቶቻችን ላይ ድልን ትሰጠናለህ፤ ባላንጣዎቻችንንም ታሳፍራለህ። ዘወትር በእግዚአብሔር እንመካለን፤ ስምህንም ለዘላለም እንወድሳለን። ሴላ
መዝሙር 44:1-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አምላክ ሆይ! በጥንት ዘመን ያደረግኸውን ሁሉ በጆሮአችን ሰማን፤ የቀድሞ አባቶቻችንም በዘመናቸው ስላደረግሃቸው ድንቅ ነገሮች ሁሉ ነግረውናል። በቀድሞ ዘመን እጆችህ ያደረጉትን ድርጊት ሁሉ አባቶቻችን ነግረውናል፤ ይኸውም፥ እነርሱን ለመትከል ሕዝቦችን አባረሃል፤ እነርሱን ለማደላደል ነዋሪዎቹን አጥፍተሃል። እነርሱ ምድርን የወረሱት በሰይፋቸው አይደለም፤ ድል አድርገው የወሰዱትም በራሳቸው ኀይል አይደለም፤ ይህን ሁሉ ያደረጉት አንተ ስለ ወደድካቸውና ከእነርሱም ጋር በመሆን በኀይልህና በብርታትህ ስለ ረዳሃቸው ነው። አንተ ንጉሤና አምላኬ ነህ፤ የያዕቆብ ዘር ለሆነው ሕዝብህ፥ ድልን የምታጐናጽፍ አንተ ነህ። በአንተ ርዳታ ጠላቶቻችንን ድል እንነሣለን፤ በስምህም ተቃዋሚዎቻችንን እንረግጣለን። በቀስቴ አልተማመንም፤ ሰይፌም አያድነኝም። ከጠላቶቻችን የምታድነን አንተ ነህ፤ የሚጠሉንንም የምታሳፍርልን አንተ ነህ። አምላክ ሆይ! ዘወትር በአንተ እንመካለን፤ ስምህንም ለዘለዓለም እናመሰግናለን።
መዝሙር 44:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ በጆሮአችን ሰማን፥ አባቶቻችንም በዘመናቸው በቀድሞ ዘመን የሠራኸውን ሥራ ነገሩን። እጅህ አሕዛብን አባረረች፥ እነርሱንም ተከልህ፥ አሕዛብን አስጨንቀህ እነሱን አለመለምክ። በሰይፋቸው ምድርን አልወረሱም ክንዳቸውም አላዳናቸው፥ ቀኝህና ክንድህ የፊትህም ብርሃን ነው እንጂ፥ ወድደሃቸዋልና። አምላኬና ንጉሤ አንተ ነህ፥ ለያዕቆብ መድኃኒትን እዘዝ። በአንተ ጠላቶቻችንን እንወጋቸዋለን፥ በስምህም የሚነሡብንን እንረግጣለን። በቀስቴ የምታመን አይደለሁምና፥ ሰይፌም አያድነኝምና፥ አንተ ግን ከጠላቶቻችን አዳንኸን፥ የሚጠሉንንም አሳፈርሃቸው።