መዝሙር 42:5-11
መዝሙር 42:5-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ነፍሴ ሆይ፤ ለምን ትተክዢያለሽ? ለምንስ በውስጤ ትታወኪያለሽ? ተስፋሽን በአምላክ ላይ አድርጊ፤ አዳኜና አምላኬን፣ ገና አመሰግነዋለሁና። ነፍሴ በውስጤ ተክዛለች፤ ስለዚህ በዮርዳኖስ ምድር፣ በአርሞንኤም ከፍታ፣ በሚዛር ተራራ ዐስብሃለሁ። በፏፏቴህ ማስገምገም፣ አንዱ ጥልቅ ሌላውን ጥልቅ ይጣራል፤ ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ፣ ሙሉ በሙሉ አጥለቀለቀኝ። እግዚአብሔር ምሕረቱን በቀን ያዝዛል፤ ዝማሬውም በሌሊት በእኔ ዘንድ አለ፤ ይህም ለሕይወቴ አምላክ የማቀርበው ጸሎት ነው። እግዚአብሔር ዐለቴን፣ “ለምን ረሳኸኝ? ጠላትስ እያስጨነቀኝ፣ ለምን በሐዘን እመላለሳለሁ?” እለዋለሁ። ጠላቶቼ ቀኑን ሙሉ፣ “አምላክህ የት አለ?” እያሉ፣ በነገር ጠዘጠዙኝ፣ ዐጥንቴም ደቀቀ። ነፍሴ ሆይ፤ ለምን ትተክዢያለሽ? ለምንስ በውስጤ ትታወኪያለሽ? ተስፋሽን በአምላክ ላይ አድርጊ፣ አዳኜና አምላኬን ገና አመሰግነዋለሁና።
መዝሙር 42:5-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እኔ ለምን ተስፋ እቈርጣለሁ፤ ለምንስ እጨነቃለሁ። በእግዚአብሔር እተማመናለሁ። ስለሚረዳኝም እርሱን አመሰግናለሁ። አምላኬ ሆይ! ተስፋ ቈርጬአለሁ ስለዚህም ከዮርዳኖስና ከሔርሞን ምድር ከሚዛር ተራራ አስብሃለሁ። በፏፏቴህ ድምፅ ጥልቁ ጥልቁን ይጠራል፤ ማዕበልህና ሞገድህ በእኔ ላይ አለፈ። እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ፍቅሩን በቀን ይሰጣል፤ በሌሊትም የምስጋና መዝሙር አቀርብለታለሁ፤ ወደ ሕይወቴ አምላክ እጸልያለሁ። ለአምላኬ! ለአምባዬ! “ለምን ረሳኸኝ? በጠላት ስለተጨቈንኩ ለምን እያዘንኩ ልሂድ?” እለዋለሁ። ጠላቶቼ “ሁልጊዜ አምላክህ የት አለ?” ብለው በሚያላግጡብኝ ጊዜ አጥንቶቼ እንኳ ይታመማሉ። እኔ ለምን ተስፋ እቈርጣለሁ? ለምንስ እጨነቃለሁ። በእግዚአብሔር እተማመናለሁ ስለሚረዳኝም እርሱን አመሰግናለሁ።
መዝሙር 42:5-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ይህን ሳስብ ነፍሴ በእኔ ውስጥ ፈሰሰች፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ምስጋና መኖሪያ ስፍራ እገባለሁና፥ በዓል የሚያከብሩ ሰዎች የደስታና ምስጋና ቃል አሰሙ። ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ። አምላኬ ሆይ፥ ነፍሴ በእኔ ውስጥ ታወከች፥ ስለዚህ በዮርዳኖስ ምድር በአርሞንኤምም በታናሹ ተራራ አስታውስሃለሁ። በፏፏቴህ ድምፅ ቀላይ ቀላይን ትጠራታለች፥ ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ አለፈ። ጌታ በቀን ቸርነቱን ያዝዛል፥ በሌሊትም ዝማሬው በእኔ ዘንድ ይሆናል፥ የእኔ ስእለት ለሕይወቴ አምላክ ነው። እግዚአብሔርን፦ አንተ መጠጊያዬ ነህ፥ ለምን ረሳኸኝ? ጠላቶቼ ሲያስጨንቁኝ ለምን አዝኜ እመላለሳለሁ? እለዋለሁ። ጠላቶቼ ሁልጊዜ፦ አምላክህ ወዴት ነው? ባሉኝ ጊዜ አጥንቶቼን እየቀለጣጠሙ ሰደቡኝ።