መዝሙር 39:4-7
መዝሙር 39:4-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
መታመኛው የእግዚአብሔር ስም የሆነ፥ ወደ ከንቱ ነገር፥ ወደ ቍጣና ወደ ሐሰትም፥ ያልተመለከተ ሰው ብፁዕ ነው። አቤቱ አምላኬ፥ ብዙ ተአምራትህን አደረግህ፥ አሳብህንም ምንም የሚመስለው የለም፤ አወራሁ፥ ተናገርሁ፥ ከቍጥርም በዛ። መሥዋዕትንና ቍርባንን አልወደድሁም፤ ሥጋህን አንጻልኝ፤ የሚቃጠለውንና ስለ ኀጢአት የሚቀርበውን መሥዋዕት አልወደድሁም። በዚያን ጊዜ አልሁ፥ “እነሆ፥ መጣሁ፤ ስለ እኔ በመጽሐፍ ራስ ተጽፎአል፤
መዝሙር 39:4-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“እግዚአብሔር ሆይ፤ የሕይወቴን ፍጻሜ፣ የዘመኔንም ቍጥር አስታውቀኝ፤ ዐላፊ ጠፊ መሆኑንም ልረዳ። እነሆ፤ ዘመኔን በስንዝር ለክተህ አስቀመጥህ፤ ዕድሜዬም በፊትህ እንደ ኢምንት ነው፤ በርግጥ የሰው ሁሉ ሕይወት ተን ነው። ሴላ “ሰው የጥላ ውልብታ ነው፤ በከንቱም ይታወካል፤ ለማን እንደሚሆን ሳያውቅ ሀብት ንብረት ያከማቻል። “ጌታ ሆይ፤ አሁንስ ወደ ማን ልመልከት? ተስፋዬ በአንተ ላይ ነው።
መዝሙር 39:4-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ጌታ ሆይ! መጨረሻዬንና የቀኖቼን ብዛት እንዳውቅ አድርገኝ፤ ዕድሜዬም ምን ያኽል አጭር እንደ ሆነ ንገረኝ።” የዘመኔን መለኪያ ከእጅ መዳፍ እንዳይበልጥ አድርገህ አሳጠርከው፤ ዕድሜዬም በአንተ ፊት ከምንም አይቈጠርም፤ በእርግጥ የሰው ሕይወት እንደ ነፋስ ሽውታ ነው። ሰው ከጥላም የተሻለ አይደለም፤ በከንቱ ይደክማል፤ ሀብትን ያከማቻል፤ ነገር ግን ማን እንደሚጠቀምበት አያውቅም። እግዚአብሔር ሆይ! ታዲያ፥ እኔ ተስፋዬን በአንተ ላይ ከማድረግ በቀር ሌላ ምን እጠብቃለሁ?
መዝሙር 39:4-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ልቤም በውስጤ ሞቀብኝ፥ ከማሰቤም የተነሣ እሳት ነደደ፥ በአንደበቴም ተናገርሁ፦ አቤቱ፥ ፍጻሜዬን አስታውቀኝ፥ የዘመኔ ቁጥሮች ምን ያህል እንደ ሆኑ፥ እኔ ምን ያህል ረጋፊ እንደሆንኩ አውቅ ዘንድ። እነሆ፥ ዘመኖቼን ከእጅ መዳፍ አሳጠርካቸው፥ አካሌም በፊትህ እንደ ኢምንት ነው። ሰው ሁሉ በእውነት ከንቱ ነው። በእውነት ሰው እንደ ጥላ ይመላለሳል፥ በእውነት በከንቱ ይታወካል። ያከማቻል የሚሰበስብለትንም አያውቅም።