መዝሙር 39:2-6
መዝሙር 39:2-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከጥፋት ጕድጓድ ከረግረግ ጭቃም አወጣኝ፥ እግሮቼንም በዓለት ላይ አቆማቸው፥ አረማመዴንም አጸና። አዲስ ምስጋናን በአፌ ጨመረ፥ ይህም የአምላካችን ምስጋናው ነው፤ ብዙዎች አይተው ይፍሩ፥ በእግዚአብሔርም ይታመኑ። መታመኛው የእግዚአብሔር ስም የሆነ፥ ወደ ከንቱ ነገር፥ ወደ ቍጣና ወደ ሐሰትም፥ ያልተመለከተ ሰው ብፁዕ ነው። አቤቱ አምላኬ፥ ብዙ ተአምራትህን አደረግህ፥ አሳብህንም ምንም የሚመስለው የለም፤ አወራሁ፥ ተናገርሁ፥ ከቍጥርም በዛ። መሥዋዕትንና ቍርባንን አልወደድሁም፤ ሥጋህን አንጻልኝ፤ የሚቃጠለውንና ስለ ኀጢአት የሚቀርበውን መሥዋዕት አልወደድሁም።
መዝሙር 39:2-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንደ ዲዳ ዝም አልሁ፤ ለበጎ ነገር እንኳ አፌን ዘጋሁ፤ ሆኖም ጭንቀቴ ባሰ። ልቤ በውስጤ ጋለ፤ በማሰላስልበትም ጊዜ እሳቱ ነደደ፤ ከዚያም በአንደበቴ እንዲህ ተናገርሁ፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ የሕይወቴን ፍጻሜ፣ የዘመኔንም ቍጥር አስታውቀኝ፤ ዐላፊ ጠፊ መሆኑንም ልረዳ። እነሆ፤ ዘመኔን በስንዝር ለክተህ አስቀመጥህ፤ ዕድሜዬም በፊትህ እንደ ኢምንት ነው፤ በርግጥ የሰው ሁሉ ሕይወት ተን ነው። ሴላ “ሰው የጥላ ውልብታ ነው፤ በከንቱም ይታወካል፤ ለማን እንደሚሆን ሳያውቅ ሀብት ንብረት ያከማቻል።
መዝሙር 39:2-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አንድ ቃል እንኳ ሳልናገር ዝም አልኩ፤ መልካም ስለ ሆነ ነገር እንኳ አልተናገርኩም፤ ነገር ግን ሥቃዬ ከበፊት ይልቅ እየባሰ ሄደ። ልቤ በውስጤ ነደደ፤ በሐሳቤም እሳት ተያያዘ፤ ከዚያም መናገር ጀመርኩ። “ጌታ ሆይ! መጨረሻዬንና የቀኖቼን ብዛት እንዳውቅ አድርገኝ፤ ዕድሜዬም ምን ያኽል አጭር እንደ ሆነ ንገረኝ።” የዘመኔን መለኪያ ከእጅ መዳፍ እንዳይበልጥ አድርገህ አሳጠርከው፤ ዕድሜዬም በአንተ ፊት ከምንም አይቈጠርም፤ በእርግጥ የሰው ሕይወት እንደ ነፋስ ሽውታ ነው። ሰው ከጥላም የተሻለ አይደለም፤ በከንቱ ይደክማል፤ ሀብትን ያከማቻል፤ ነገር ግን ማን እንደሚጠቀምበት አያውቅም።
መዝሙር 39:2-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፥ ክፉ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ ሁሉ በአፌ ላይ ልጓም አኖራለሁ አልሁ። ከዝምታ የተነሣ እንደ ዲዳ ሆንሁ፥ ለበጎ እንኳ ዝም አልሁ፥ ሥቃዬም ተቀሰቀሰብኝ። ልቤም በውስጤ ሞቀብኝ፥ ከማሰቤም የተነሣ እሳት ነደደ፥ በአንደበቴም ተናገርሁ፦ አቤቱ፥ ፍጻሜዬን አስታውቀኝ፥ የዘመኔ ቁጥሮች ምን ያህል እንደ ሆኑ፥ እኔ ምን ያህል ረጋፊ እንደሆንኩ አውቅ ዘንድ። እነሆ፥ ዘመኖቼን ከእጅ መዳፍ አሳጠርካቸው፥ አካሌም በፊትህ እንደ ኢምንት ነው። ሰው ሁሉ በእውነት ከንቱ ነው።