የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙር 38:11-22

መዝሙር 38:11-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከቍስሌ የተነሣ ወዳጆቼም ባልንጀሮቼም ሸሹኝ፤ ጎረቤቶቼም ርቀው ቆሙ። ሕይወቴን ለማጥፋት የሚሹ ወጥመድ ዘረጉብኝ፤ ሊጐዱኝ የሚፈልጉ ሊያጠፉኝ ዛቱ፤ ቀኑንም ሙሉ ተንኰል ይሸርባሉ። እኔ ግን እንደማይሰማ ደንቈሮ፣ አፉንም መክፈት እንደማይችል ዲዳ ሆንሁ። በርግጥም ጆሮው እንደማይሰማ፣ አንደበቱም መልስ መስጠት እንደማይችል ሰው ሆንሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ በተስፋ እጠብቅሃለሁ፤ ጌታ አምላኬ ሆይ፤ አንተ መልስ ትሰጠኛለህ። እኔ፣ “ጠላቶቼ በእኔ ላይ ደስ አይበላቸው፤ እግሬም ሲንሸራተት፣ በላዬ አይኵራሩብኝ” ብያለሁና። ልወድቅ ተቃርቤአለሁ፤ ከሥቃዬም ከቶ አልተላቀቅሁም። በደሌን እናዘዛለሁ፤ ኀጢአቴም አውካኛለች። ብርቱዎች ጠላቶቼ ብዙ ናቸው፤ ያለ ምክንያት የሚጠሉኝም ስፍር ቍጥር የላቸውም። መልካሙን ስለ ተከተልሁ፣ በበጎ ፈንታ ክፉ የሚመልሱልኝ ከሰሱኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ አትተወኝ፤ አምላኬ ሆይ፤ ከእኔ አትራቅ። ጌታዬ መድኅኔ ሆይ፤ እኔን ለመርዳት ፍጠን።

መዝሙር 38:11-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ወዳጆቼና ጓደኞቼ ሕመሜን ተጸየፉ፤ ዘመዶቼም ከእኔ ራቁ፤ ሊገድሉኝ የሚፈልጉ ወጥመድ ይዘረጉብኛል፤ ሊጐዱኝ የሚያቅዱ ሊያጠፉኝ ይዝታሉ፤ በእኔም ላይ ቀኑን ሙሉ ያሤራሉ። እኔ ግን ሊሰማ እንደማይችል ደንቆሮ፥ ለመናገር እንደማይችል ድዳ ሰው ነኝ። በእውነትም እንደማይሰማና መልስ ለመስጠት እንደማይችል ሰው ሆኜአለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! በአንተ እተማመናለሁ፤ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! አንተም መልስ ትሰጠኛለህ። “ጠላቶቼ እኔን በንቀት ዐይን እንዲመለከቱኝ ወይም እግሬን ሲያዳልጠው ራሳቸውን ከፍ እንዲያደርጉ አታድርግ!” ብዬ እለምናለሁ። ፋታ ከማይሰጠው ሕመሜ የተነሣ ተዝለፍልፌ ልወድቅ ተቃርቤአለሁ። በደሌን እናዘዛለሁ፤ ኃጢአቴም አስጨንቆኛል። ያለ ምክንያት ጠላት የሆኑብኝ ኀያላን ናቸው፤ በስሕተትም የሚጠሉኝ ብዙዎች ናቸው። እኔ ደግ ሥራ በመሥራቴ በመልካም ፈንታ ክፉ የሚመልሱልኝ፤ በእኔ ላይ በጠላትነት ተነሥተዋል። እግዚአብሔር ሆይ! አትተወኝ፤ አምላኬ ሆይ! ከእኔ አትራቅ። አዳኜ አምላኬ ሆይ! ፈጥነህ እርዳኝ።