መዝሙር 38
38
መዝሙር 38
የጭንቅ ሰዓት ጸሎት
የዳዊት መዝሙር፤ ለመታሰቢያ።
1 እግዚአብሔር ሆይ፤ በቍጣህ አትገሥጸኝ፤
በመዓትህም አትቅጣኝ።
2ፍላጻዎችህ ወግተውኛልና፤
እጅህም ተጭናኛለች።
3ከቍጣህ የተነሣ ሰውነቴ ጤና አጥቷል፤
ከኀጢአቴም የተነሣ ዐጥንቶቼ ሰላም የላቸውም።
4በደሌ ውጦኛል፤
እንደ ከባድ ሸክምም ተጭኖኛል።
5ከንዝህላልነቴ የተነሣ፣
ቍስሌ ሸተተ፤ መገለም፤
6ዐንገቴን ደፋሁ፤ ጐበጥሁም፤
ቀኑንም ሙሉ በትካዜ ተመላለስሁ።
7ወገቤ እንደ እሳት ነድዷል፤
ሰውነቴም ጤና የለውም።
8እጅግ ዝያለሁ፤ ፈጽሞም ደቅቄአለሁ፤
ከልቤም መታወክ የተነሣ እጮኻለሁ።
9ጌታ ሆይ፤ ምኞቴ ሁሉ በፊትህ ግልጽ ነው፤
ጭንቀቴም ከአንተ የተሰወረ አይደለም።
10ልቤ በኀይል ይመታል፤ ጕልበት ከድቶኛል፤
የዐይኔም ብርሃን ጠፍቷል።
11ከቍስሌ የተነሣ ወዳጆቼም ባልንጀሮቼም ሸሹኝ፤
ጎረቤቶቼም ርቀው ቆሙ።
12ሕይወቴን ለማጥፋት የሚሹ ወጥመድ ዘረጉብኝ፤
ሊጐዱኝ የሚፈልጉ ሊያጠፉኝ ዛቱ፤
ቀኑንም ሙሉ ተንኰል ይሸርባሉ።
13እኔ ግን እንደማይሰማ ደንቈሮ፣
አፉንም መክፈት እንደማይችል ዲዳ ሆንሁ።
14በርግጥም ጆሮው እንደማይሰማ፣
አንደበቱም መልስ መስጠት እንደማይችል ሰው ሆንሁ።
15 እግዚአብሔር ሆይ፤ በተስፋ እጠብቅሃለሁ፤
ጌታ አምላኬ ሆይ፤ አንተ መልስ ትሰጠኛለህ።
16እኔ፣ “ጠላቶቼ በእኔ ላይ ደስ አይበላቸው፤
እግሬም ሲንሸራተት፣ በላዬ አይኵራሩብኝ” ብያለሁና።
17ልወድቅ ተቃርቤአለሁ፤
ከሥቃዬም ከቶ አልተላቀቅሁም።
18በደሌን እናዘዛለሁ፤
ኀጢአቴም አውካኛለች።
19ብርቱዎች ጠላቶቼ ብዙ ናቸው፤
ያለ ምክንያት የሚጠሉኝም ስፍር ቍጥር የላቸውም።
20መልካሙን ስለ ተከተልሁ፣
በበጎ ፈንታ ክፉ የሚመልሱልኝ ጠሉኝ።
21 እግዚአብሔር ሆይ፤ አትተወኝ፤
አምላኬ ሆይ፤ ከእኔ አትራቅ።
22ጌታዬ መድኅኔ ሆይ፤
እኔን ለመርዳት ፍጠን።
Currently Selected:
መዝሙር 38: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.