የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙር 37:1-22

መዝሙር 37:1-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

አቤቱ፥ በመ​ዓ​ትህ አት​ቅ​ሠ​ፈኝ፥ በመ​ቅ​ሠ​ፍ​ት​ህም አት​ገ​ሥ​ጸኝ። ፍላ​ጾ​ችህ ወግ​ተ​ው​ኛ​ልና፥ እጅ​ህ​ንም በእኔ ላይ አክ​ብ​ደ​ህ​ብ​ኛ​ልና። ከቍ​ጣህ ፊት የተ​ነሣ ለሥ​ጋዬ ድኅ​ነት የለ​ውም፤ ከኀ​ጢ​አ​ቴም ፊት የተ​ነሣ ለአ​ጥ​ን​ቶቼ ሰላም የላ​ቸ​ውም። ኀጢ​አቴ ከራሴ ጠጕር በዝ​ቷ​ልና፥ እንደ ከባድ ሸክ​ምም በላዬ ከብ​ዶ​አ​ልና። ከስ​ን​ፍ​ና​ዬም ፊት የተ​ነሣ አጥ​ን​ቶቼ ሸተቱ፥ በሰ​በ​ሱም፤ እጅግ ጐሰ​ቈ​ልሁ፥ ጐበ​ጥ​ሁም፥ ሁል​ጊ​ዜም በት​ካዜ እመ​ላ​ለ​ሳ​ለሁ፤ ነፍሴ ስድ​ብን ጠግ​ባ​ለ​ችና፥ ለሥ​ጋ​ዬም ድኅ​ነ​ትን አጣሁ። ታመ​ምሁ እጅ​ግም ተሠ​ቃ​የሁ፥ ከል​ቤም ኀዘን የተ​ነሣ እጮ​ኻ​ለሁ። አቤቱ፥ ፈቃዴ ሁሉ በፊ​ትህ ነው፥ ጩኸ​ቴም ከአ​ንተ አይ​ሰ​ወ​ርም። ልቤ ደነ​ገ​ጠ​ብኝ፥ ኀይ​ሌም ተወኝ፥ የዐ​ይ​ኖ​ቼም ብር​ሃን ፈዘ​ዘ​ብኝ። ወዳ​ጆቼም ባል​ን​ጀ​ሮ​ቼም ባላ​ጋራ ሆኑኝ፥ ከበ​ውም ደበ​ደ​ቡኝ፥ ዘመ​ዶቼም ተስፋ ቈር​ጠው ተለ​ዩኝ። ነፍ​ሴ​ንም የሚ​ሹ​አት በረ​ቱ​ብኝ፥ መከ​ራ​ዬ​ንም የሚ​ፈ​ልጉ ከን​ቱን ተና​ገሩ፥ ሁል​ጊ​ዜም ያጠ​ፉኝ ዘንድ በሽ​ን​ገላ ይመ​ክ​ራሉ። እኔ ግን እን​ደ​ማ​ይ​ሰማ ደን​ቆሮ፥ አፉ​ንም እን​ደ​ማ​ይ​ከ​ፍት ዲዳ ሆንሁ። እን​ደ​ማ​ይ​ሰማ ሰው፥ በአ​ፉም መና​ገር እን​ደ​ማ​ይ​ችል ሰው ሆንሁ። አቤቱ፥ በአ​ንተ ታም​ኛ​ለ​ሁና፤ አቤቱ አም​ላኬ፥ አንተ ስማኝ። የጠ​ላ​ቶቼ መዘ​ባ​በቻ አታ​ድ​ር​ገኝ ብያ​ለ​ሁና፥ እግ​ሬም ቢሰ​ና​ከል በእኔ ላይ ብዙ ነገ​ርን ይና​ገ​ራሉ። እኔ​ንስ ይገ​ር​ፉኝ ዘንድ አቈ​ዩኝ፥ ቍስሌ ሁል​ጊዜ በፊቴ ነውና። በደ​ሌን እና​ገ​ራ​ለ​ሁና፥ ስለ ኀጢ​አ​ቴም እተ​ክ​ዛ​ለሁ። ጠላ​ቶቼ ሕያ​ዋን ናቸው፥ ይበ​ረ​ቱ​ብ​ኛ​ልም፥ በዐ​መ​ፃም የሚ​ጠ​ሉኝ በዙ። በበጎ ፋንታ ክፉን የሚ​መ​ል​ሱ​ልኝ ጽድ​ቅን ስለ ተከ​ተ​ልሁ ይከ​ስ​ሱ​ኛል። እንደ ርኩስ በድን ወን​ድ​ማ​ቸ​ውን ጣሉ፥ አቤቱ፥ አንተ አት​ጣ​ለኝ፤ አም​ላኬ፥ ከእኔ አት​ራቅ። አቤቱ፥ የመ​ድ​ኀ​ኒቴ አም​ላክ ሆይ፥ እኔን ለመ​ር​ዳት ፍጠን።

መዝሙር 37:1-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ዐመፀኞችን በማየት አትሸበር፤ በክፉ አድራጊዎችም አትቅና፤ እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፤ እንደ ለምለም ቅጠልም ይጠወልጋሉ። በእግዚአብሔር ታመን፤ መልካምንም አድርግ፤ በምድሪቱ ተቀመጥ፤ ዘና ብለህ ተሰማራ። በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፤ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል። መንገድህን ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ በርሱ ታመን፤ እርሱም ያከናውንልሃል፤ ጽድቅህን እንደ ብርሃን፣ ፍትሕህን እንደ ቀትር ፀሓይ ያበራዋል። በእግዚአብሔር ፊት ጸጥ በል፤ በትዕግሥትም ተጠባበቀው፤ መንገዱ በተቃናለት፣ ክፋትንም በሚሸርብ ሰው ልብህ አይሸበር። ከንዴት ተቈጠብ፤ ቍጣንም ተወው፤ ወደ እኵይ ተግባር እንዳይመራህ አትከፋ። ክፉ ሰዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን ምድርን ይወርሳሉ። ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ ስፍራውንም ብታሥሥ አታገኘውም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ። ክፉዎች በጻድቃን ላይ ያሤራሉ፤ ጥርሳቸውንም ያፋጩባቸዋል። እግዚአብሔር ግን ይሥቅባቸዋል፣ ቀናቸው እንደ ደረሰ ያውቃልና። ችግረኞችንና ድኾችን ለመጣል፣ አካሄዳቸው ቀና የሆነውንም ለመግደል፣ ክፉዎች ሰይፋቸውን መዘዙ፤ ቀስታቸውንም ገተሩ። ሰይፋቸው የገዛ ልባቸውን ይወጋል፤ ቀስታቸውም ይሰበራል። የጻድቅ ጥቂት ሀብት፣ ከክፉዎች ብዙ ጥሪት ይበልጣል። የክፉዎች ክንድ ይሰበራልና፣ ጻድቃንን ግን እግዚአብሔር ደግፎ ይይዛቸዋል። እግዚአብሔር የንጹሓንን የሕይወት ዘመን ያውቃል፤ ርስታቸውም ለዘላለም ይኖራል። በክፉ ጊዜ ዐንገት አይደፉም፤ በራብ ዘመንም ይጠግባሉ። ክፉዎች ግን ይጠፋሉ፤ የእግዚአብሔር ጠላቶች እንደ መስክ ውበት ይሆናሉ፤ ይጠፋሉ፤ እንደ ጢስም ተነው ይጠፋሉ። ኀጢአተኛ ይበደራል፤ መልሶም አይከፍልም፤ ጻድቅ ግን ይቸራል። እግዚአብሔር የባረካቸው ምድርን ይወርሳሉ፤ እርሱ የሚረግማቸው ግን ይጠፋሉ።

መዝሙር 37:1-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በክፉዎች ምክንያት አትበሳጭ፤ ኃጢአት በሚሠሩም አትቅና። እንደ ሣር ቶሎ ይደርቃሉ፤ እንደ ቅጠልም ጠውልገው ይረግፋሉ። በእግዚአብሔር ታምነህ መልካምን አድርግ፤ በምድሪቱም በሰላም ትኖራለህ። በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፤ እርሱም የልብህን ፍላጎት ሁሉ ይሰጥሃል። አካሄድህን ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ በእርሱ ታመን፤ እርሱም ይረዳሃል። ጽድቅህን እንደ ብርሃን የጉዳይህንም ትክክለኛነት እንደ ቀትር ፀሐይ ያበራዋል። በትዕግሥት ጸንተህ እግዚአብሔር የሚያደርገውን ለማየት ተጠባበቅ፤ ሌሎች ሰዎች ክፉ ሐሳባቸው ቢሳካላቸው አትበሳጭ። ቊጣ ወደ ክፉ ነገር ስለሚያመራ። ራስህን ከቊጣ መልስ፤ ከንዴትም ተጠበቅ፤ ክፉ አድራጊዎች ይገደላሉ፤ በእግዚአብሔር የሚታመኑ ግን ምድርን ይወርሳሉ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ክፉ አድራጊዎች ፈጥነው ይጠፋሉ፤ ብትፈልጋቸው እንኳ አታገኛቸውም። ትሑቶች ምድርን ይወርሳሉ፤ ብልጽግናንና ሰላምን በማግኘት ይደሰታሉ። ክፉ ሰው ደጉን ሰው ለማጥፋት ያሳድምበታል፤ በጥላቻም ጥርሱን ያፋጭበታል። ክፉዎች ሰዎች የሚጠፉበት ቀን እንደ ተቃረበ ስለሚያውቅ እግዚአብሔር በእነርሱ ይስቃል። ክፉዎች፥ ድኾችንና ምስኪኖችን ለመግደል፥ ደግ ሥራ የሚሠሩትንም ለማረድ፥ ሰይፋቸውን ይመዛሉ፤ ቀስታቸውን ያዘጋጃሉ። ነገር ግን ሰይፋቸው የራሳቸውን ልብ ይወጋል፤ ቀስታቸውም ይሰበራል። ከክፉ ሰው ብዙ ሀብት ይልቅ፥ የደግ ሰው ጥቂት ሀብት ይበልጣል። የክፉዎች ኀይል ይሰበራል ጻድቃንን ግን እግዚአብሔር ያበረታቸዋል። እግዚአብሔር ታዛዦቹን በየቀኑ ይጠብቃቸዋል፤ የሰጣቸውም ስጦታ ለዘለዓለም ከእነርሱ ጋር ይኖራል። ክፉ ቀን ሲመጣ ችግር አይደርስባቸውም፤ በራብ ዘመንም በቂ ምግብ በማግኘት ይጠግባሉ። ክፉዎች ግን ይጠፋሉ፤ የእግዚአብሔር ጠላቶች እንደ በረሓ አበባ ይረግፋሉ፤ እንደ ጢስም ከዓይን ይሰወራሉ። ክፉ ሰው የተበደረውን አይመልስም፤ ደግ ሰው ግን በልግሥና ይሰጣል። እግዚአብሔር የባረካቸው ምድርን ይወርሳሉ፤ እግዚአብሔር የረገማቸው ግን ይጠፋሉ።

መዝሙር 37:1-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በክፉዎች ላይ አትቅና፥ ዓመፃንም በሚያደርጉ ላይ አትቅና፥ እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፥ እንደ ለመለመ ቅጠልም ይረግፋሉና። በጌታ ታመን፥ መልካምንም አድርግ፥ በምድርም ተቀመጥ፥ ታምነህም ተሰማራ። በጌታ ደስ ይበልህ፥ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል። መንገድህን ለጌታ አደራ ስጥ፥ በእርሱም ታመን፥ እርሱም ያደርግልሃል። ጽድቅህን እንደ ብርሃን። ፍርድህንም እንደ ቀትር ያመጣዋል። በጌታ ጽና በተዕግሥትም ጠብቀው። መንገዱም በቀናችለትና በሚያደባ ሰው አትቅና። ከቁጣ ራቅ መዓትንም ተው፥ እንዳትበድል አትቅና። ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፥ በጌታ ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ። ጥቂት ጊዜ ቆይቶ፥ ክፉ አድራጊ አይኖርም፥ ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፥ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል። ክፉ በጻድቁ ላይ ያደባል፥ ጥርሱንም በእርሱ ላይ ያንገጫግጫል። ጌታ ግን ይሥቅበታል፥ ቀኑ እንደሚደርስ አይቶአልና። ክፉዎች ሰይፋቸውን መዘዙ፥ ቀስታቸውንም ገተሩ ድሀውንና ችግረኛውን ይጥሉ ዘንድ፥ ልበ ቅኖችንም ይወጉ ዘንድ፥ ሰይፋቸው ወደ ልባቸው ይግባ፥ ቀስታቸውም ይሰበር። በጻድቅ ዘንድ ያለው ጥቂት ነገር ከብዙ ክፉዎች ሀብት ይበልጣል። የክፉዎች ንድ ትሰበራለችና፥ ጌታ ግን ጻድቃንን ይደግፋቸዋል። የንጹሓንን ቀኖች ጌታ ያውቃል፥ ርስታቸውም ለዘለዓለም ትሆናለች፥ በክፉ ዘመንም አያፍሩም፥ በራብ ዘመንም ይጠግባሉ። ክፉዎቸ ግን ይጠፋሉ፥ የጌታ ጠላቶች እንደ መስክ ውበት፥ እንደ ጢስም ተንነው ይጠፋሉ። ክፉ ይበደራል አይከፍልምም፥ ጻድቅ ግን ይራራል ይሰጣልም። እርሱን የሚባርኩት ምድርን ይወርሳሉና፥ የሚረግሙት ግን ይጠፋሉ።