አቤቱ፥ በመዓትህ አትቅሠፈኝ፥ በመቅሠፍትህም አትገሥጸኝ። ፍላጾችህ ወግተውኛልና፥ እጅህንም በእኔ ላይ አክብደህብኛልና። ከቍጣህ ፊት የተነሣ ለሥጋዬ ድኅነት የለውም፤ ከኀጢአቴም ፊት የተነሣ ለአጥንቶቼ ሰላም የላቸውም። ኀጢአቴ ከራሴ ጠጕር በዝቷልና፥ እንደ ከባድ ሸክምም በላዬ ከብዶአልና። ከስንፍናዬም ፊት የተነሣ አጥንቶቼ ሸተቱ፥ በሰበሱም፤ እጅግ ጐሰቈልሁ፥ ጐበጥሁም፥ ሁልጊዜም በትካዜ እመላለሳለሁ፤ ነፍሴ ስድብን ጠግባለችና፥ ለሥጋዬም ድኅነትን አጣሁ። ታመምሁ እጅግም ተሠቃየሁ፥ ከልቤም ኀዘን የተነሣ እጮኻለሁ። አቤቱ፥ ፈቃዴ ሁሉ በፊትህ ነው፥ ጩኸቴም ከአንተ አይሰወርም። ልቤ ደነገጠብኝ፥ ኀይሌም ተወኝ፥ የዐይኖቼም ብርሃን ፈዘዘብኝ። ወዳጆቼም ባልንጀሮቼም ባላጋራ ሆኑኝ፥ ከበውም ደበደቡኝ፥ ዘመዶቼም ተስፋ ቈርጠው ተለዩኝ። ነፍሴንም የሚሹአት በረቱብኝ፥ መከራዬንም የሚፈልጉ ከንቱን ተናገሩ፥ ሁልጊዜም ያጠፉኝ ዘንድ በሽንገላ ይመክራሉ። እኔ ግን እንደማይሰማ ደንቆሮ፥ አፉንም እንደማይከፍት ዲዳ ሆንሁ። እንደማይሰማ ሰው፥ በአፉም መናገር እንደማይችል ሰው ሆንሁ። አቤቱ፥ በአንተ ታምኛለሁና፤ አቤቱ አምላኬ፥ አንተ ስማኝ። የጠላቶቼ መዘባበቻ አታድርገኝ ብያለሁና፥ እግሬም ቢሰናከል በእኔ ላይ ብዙ ነገርን ይናገራሉ። እኔንስ ይገርፉኝ ዘንድ አቈዩኝ፥ ቍስሌ ሁልጊዜ በፊቴ ነውና። በደሌን እናገራለሁና፥ ስለ ኀጢአቴም እተክዛለሁ። ጠላቶቼ ሕያዋን ናቸው፥ ይበረቱብኛልም፥ በዐመፃም የሚጠሉኝ በዙ። በበጎ ፋንታ ክፉን የሚመልሱልኝ ጽድቅን ስለ ተከተልሁ ይከስሱኛል። እንደ ርኩስ በድን ወንድማቸውን ጣሉ፥ አቤቱ፥ አንተ አትጣለኝ፤ አምላኬ፥ ከእኔ አትራቅ። አቤቱ፥ የመድኀኒቴ አምላክ ሆይ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን።
መዝሙረ ዳዊት 37 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መዝሙረ ዳዊት 37:1-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos