መዝሙር 35:13-18
መዝሙር 35:13-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እኔ ግን እነርሱ በታመሙ ጊዜ ማቅ ለበስሁ፤ ነፍሴንም በጾም አደከምኋት፤ ጸሎቴም መልስ ዐጥቶ ወደ ጕያዬ ተመለሰ። ለወዳጄ ወይም ለወንድሜ እንደማደርግ፣ እየተንቈራጠጥሁ አለቀስሁ፤ ለእናቴም እንደማለቅስ፣ በሐዘን ዐንገቴን ደፋሁ። እነርሱ ግን እኔ ስሰናከል በእልልታ ተሰበሰቡ፤ ግፈኞች በድንገት ተሰበሰቡብኝ፤ ያለ ዕረፍትም ቦጫጨቁኝ። እንደ ምናምንቴዎች አፌዙብኝ፤ ጥርሳቸውንም አፋጩብኝ። ጌታ ሆይ፤ እስከ መቼ ዝም ብለህ ታያለህ? ነፍሴን ከክፉ ሥራቸው፣ ብርቅ ሕይወቴን ከአንበሶች ታደጋት። በታላቅ ጉባኤ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበትም አወድስሃለሁ።
መዝሙር 35:13-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እኔ ግን እነርሱ በታመሙ ጊዜ ማቅ ለበስኩ፤ ሰውነቴንም በጾም አጐሳቈልኩ፤ ጸሎቴም መልስ ሳያገኝ ቀረ። ያዘንኩትም ለወዳጅ ወይም ለወንድም የሚታዘነውን ያኽል ነው፤ እናቱ የሞተችበት ሰው የሚያዝነውን ያኽል ራሴን ዝቅ አድርጌ አለቀስኩ። በተደናቀፍኩ ጊዜ ደስ ብሎአቸው ተሰባሰቡ፤ የማላውቃቸው ጋጠወጦች መጥተው ያለማቋረጥ አላገጡብኝ። ክፉዎች ሰዎች እንደሚያደርጉት እነርሱ በክፋት አፌዙብኝ፤ በእኔም ላይ ጥርሳቸውን አፋጩ። እግዚአብሔር ሆይ! እስከ መቼ ድረስ ዝም ብለህ ታየኛለህ? ከክፉ ሥራቸው አድነኝ፤ ከእነዚህ እንደ አንበሳ ጨካኝ ከሆኑ ሰዎች ታደገኝ! በዚያን ጊዜ በሕዝብ ጉባኤ መካከል ሆኜ አመሰግንሃለሁ፤ ብዙ ሕዝብም በተሰበሰበበት ቦታ አከብርሃለሁ።
መዝሙር 35:13-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እኔስ እነርሱ በታመሙ ጊዜ ማቅ ለበስሁ፥ ነፍሴንም በጾም አደከምኋት፥ ጸሎቴም ወደ ብብቴ ተመለሰ። ለወዳጄና ለወንድሜ እንደማደርግ አደረግሁ፥ ለእናቱም እንደሚያለቅስ ራሴን ዝቅ ዝቅ አደረግሁ። በእኔ ላይ ተሰበሰቡ ደስም አላቸው፥ ግፈኞች በእኔ ላይ ተሰበሰቡ እኔም አላወቅሁም፥ መቦጫጨቃቸውን አላቆሙም። ፈተኑኝ በሣቅም ዘበቱብኝ፥ ጥርሳቸውንም በእኔ ላይ አንቀጫቀጩ። አቤቱ፥ እስከ መቼ ድረስ ዝም ብለህ ታየኛለህ? ነፍሴን ከክፉ ሥራቸው ብቸኛዪቱንም ከአንበሶች አድናት። አቤቱ፥ በታላቁ ጉባኤ ውስጥ እገዛልሃለሁ፥ በብዙ ሕዝብ መካከልም አመሰግንሃለሁ።