መዝሙር 35:1-28
መዝሙር 35:1-28 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ የሚታገሉኝን ታገላቸው፤ የሚዋጉኝንም ተዋጋቸው። ትልቁንና ትንሹን ጋሻ ያዝ፤ እኔንም ለመርዳት ተነሥ። በሚያሳድዱኝ ላይ፣ ጦርና ጭሬ ምዘዝ፤ ነፍሴንም፣ “የማድንሽ እኔ ነኝ” በላት። ሕይወቴን የሚፈልጓት፣ ይቅለሉ፣ ይዋረዱ፤ እኔን ለማጥፋት የሚያሤሩ፣ ዐፍረው ወደ ኋላቸው ይመለሱ። በነፋስ ፊት እንዳለ እብቅ ይሁኑ፤ የእግዚአብሔር መልአክ ያሳድዳቸው። መንገዳቸው ጨለማና ድጥ ይሁን፤ የእግዚአብሔር መልአክ ያባርራቸው። ያለ ምክንያት ወጥመዳቸውን በስውር አስቀምጠውብኛልና፤ ያለ ምክንያት ለነፍሴ ጕድጓድ ቈፍረውላታል። ያልታሰበ ጥፋት ይምጣባቸው፤ የሰወሩት ወጥመድ ይያዛቸው፤ ይጠፉም ዘንድ ወደ ጕድጓዱ ይውደቁ። ነፍሴም በእግዚአብሔር ደስ ይላታል፤ በማዳኑም ሐሤት ታደርጋለች። የሠራ አካላቴ እንዲህ ይልሃል፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ አንተ ማን አለ? ችግረኛውን ከርሱ ከሚበረቱ፣ ችግረኛውንና ድኻውን ከቀማኞች ታድናለህ።” ጨካኝ ምስክሮች ተነሡ፤ ስለማላውቀውም ነገር ጠየቁኝ። በበጎ ፈንታ ክፉ መለሱልኝ፤ ነፍሴንም ብቸኛ አደረጓት። እኔ ግን እነርሱ በታመሙ ጊዜ ማቅ ለበስሁ፤ ነፍሴንም በጾም አደከምኋት፤ ጸሎቴም መልስ ዐጥቶ ወደ ጕያዬ ተመለሰ። ለወዳጄ ወይም ለወንድሜ እንደማደርግ፣ እየተንቈራጠጥሁ አለቀስሁ፤ ለእናቴም እንደማለቅስ፣ በሐዘን ዐንገቴን ደፋሁ። እነርሱ ግን እኔ ስሰናከል በእልልታ ተሰበሰቡ፤ ግፈኞች በድንገት ተሰበሰቡብኝ፤ ያለ ዕረፍትም ቦጫጨቁኝ። እንደ ምናምንቴዎች አፌዙብኝ፤ ጥርሳቸውንም አፋጩብኝ። ጌታ ሆይ፤ እስከ መቼ ዝም ብለህ ታያለህ? ነፍሴን ከክፉ ሥራቸው፣ ብርቅ ሕይወቴን ከአንበሶች ታደጋት። በታላቅ ጉባኤ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበትም አወድስሃለሁ። ከምድር ተነሥተው ጠላቶቼ የሆኑት፣ በላዬ ደስ አይበላቸው፤ እንዲያው የሚጠሉኝ፣ በዐይናቸው አይጣቀሱብኝ። የሰላም ንግግር ከአፋቸው አይወጣም፤ ዳሩ ግን በምድሪቱ በጸጥታ በሚኖሩት ላይ፣ ነገር ይሸርባሉ። አፋቸውን አስፍተው ከፈቱብኝ፤ “ዕሠይ! ዕሠይ! በዐይናችን አየነው” አሉ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህን አይተሃልና ዝም አትበል፤ ጌታ ሆይ፤ ከእኔ አትራቅ። አምላኬ፣ ጌታዬ፤ ለእኔ ለመሟገት ተነሥ! ልትከራከርልኝም ተንቀሳቀስ። እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ በጽድቅህ ፍረድልኝ፤ በእኔም ላይ ደስ አይበላቸው። በልባቸው፣ “ዕሠይ! ያሰብነው ተሳካ! ዋጥ አደረግነውም” አይበሉ። በጭንቀቴ ደስ የሚላቸው፣ ይፈሩ፤ ግራም ይጋቡ፤ በእኔ ላይ ራሳቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ፣ ዕፍረትንና ውርደትን ይከናነቡ። ፍትሕ ማግኘቴን የሚወድዱ፣ እልል ይበሉ፤ ሐሤትም ያድርጉ፤ ዘወትርም፣ “የባሪያው ሰላም ደስ የሚለው፣ እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ይበል!” ይበሉ። አንደበቴ ጽድቅህን፣ ምስጋናህንም ቀኑን ሙሉ ይናገራል።
መዝሙር 35:1-28 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሆይ! የሚቃወሙኝን ተቃወማቸው፤ የሚዋጉኝንም ተዋጋቸው። ጋሻና ጥሩር ያዝ፤ መጥተህም እርዳኝ። በሚያሳድዱኝ ላይ ጦርና ሰይፍህን ምዘዝና “እኔ አዳኝህ ነኝ” ብለህ አረጋግጥልኝ። እኔን ለመግደል የሚፈልጉ ሁሉ ኀፍረትና ውርደት ይድረስባቸው! በእኔ ላይ የሚያሤሩም ሁሉ ተዋርደው ወደ ኋላቸው ይመለሱ! የእግዚአብሔር መልአክ ሲያሳድዳቸው፤ በነፋስ እንደሚበተን ገለባ ይሁኑ! የእግዚአብሔር መልአክ ሲያሳድዳቸው መንገዳቸው ጨለማና ድጥ ይሁንባቸው! ያለ ምክንያት ወጥመድ በድብቅ ዘርግተውብኛል፤ እኔንም ለመያዝ ጒድጓድ ቆፍረዋል። ያላሰቡት ድንገተኛ ጥፋት ይድረስባቸው፤ የደበቁት ወጥመድ ይያዛቸው በቈፈሩትም ጒድጓድ ወድቀው ይጥፉ! ነፍሴ በእግዚአብሔር ደስ ይላታል፤ በማዳኑም ሐሴት ታደርጋለች። ጌታ ሆይ! ሁለመናዬ እንዲህ ብሎ ይናገራል፤ ተበዳዮችን ከበደለኛ የሚያድን፥ ድኾችንና ተጨቋኞችን ከነጣቂዎች የሚጠብቅ እንደ አንተ ያለ ማነው? ክፉ ሰዎች ባልሠራሁት ወንጀል ከሰሱኝ፤ በማላውቀውም ነገር በሐሰት መሰከሩብኝ። እኔን ብቸኛ አድርገው ደግን በክፉ መለሱልኝ። እኔ ግን እነርሱ በታመሙ ጊዜ ማቅ ለበስኩ፤ ሰውነቴንም በጾም አጐሳቈልኩ፤ ጸሎቴም መልስ ሳያገኝ ቀረ። ያዘንኩትም ለወዳጅ ወይም ለወንድም የሚታዘነውን ያኽል ነው፤ እናቱ የሞተችበት ሰው የሚያዝነውን ያኽል ራሴን ዝቅ አድርጌ አለቀስኩ። በተደናቀፍኩ ጊዜ ደስ ብሎአቸው ተሰባሰቡ፤ የማላውቃቸው ጋጠወጦች መጥተው ያለማቋረጥ አላገጡብኝ። ክፉዎች ሰዎች እንደሚያደርጉት እነርሱ በክፋት አፌዙብኝ፤ በእኔም ላይ ጥርሳቸውን አፋጩ። እግዚአብሔር ሆይ! እስከ መቼ ድረስ ዝም ብለህ ታየኛለህ? ከክፉ ሥራቸው አድነኝ፤ ከእነዚህ እንደ አንበሳ ጨካኝ ከሆኑ ሰዎች ታደገኝ! በዚያን ጊዜ በሕዝብ ጉባኤ መካከል ሆኜ አመሰግንሃለሁ፤ ብዙ ሕዝብም በተሰበሰበበት ቦታ አከብርሃለሁ። ያለ ምክንያት የሚጠሉኝ ጠላቶቼ በእኔ ምክንያት እንዲደሰቱ አታድርግ፤ በኋላዬ ሆነው እንዲጠቃቀሱብኝም አታድርግ። አነጋገራቸው የጠላት አነጋገር ነው፤ በሰላማዊ ሰው ላይ ተንኰልን ያቅዳሉ። “ይኸዋ! ይኸዋ! እኛ ራሳችን የሠራኸውን አየን!” እያሉ በመጮኽ ያሳጡኛል። እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ይህን ተመልክተሃል፤ ስለዚህ ጌታ ሆይ! ዝም አትበል! ከእኔም አትራቅ! ጌታዬና አምላኬ ሆይ! ተነሥተህ ተከላከልልኝ፤ ተነሥተህም ፍረድልኝ። እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! እንደ ጻድቅነትህ በእውነት ፍረድልኝ፤ ጠላቶቼም በእኔ ላይ ደስ እንዲላቸው አታድርግ። “ይኸዋ የልባችን ምኞት ደረሰ!” ብለው እንዲያስቡና ወይም “እኛ አሸነፍነው!” እንዲሉ አታድርግ። በእኔ መከራ ተደስተው ትኲር ብለው በንቀት የሚመለከቱኝ ሁሉ ይፈሩ፤ ግራም ይጋቡ፤ በእኔ ላይ ራሳቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ሁሉ ኀፍረትንና ውርደትን ይልበሱ። ድል ማድረጌ የሚያስደስታቸው ሁሉ ደስ ይበላቸው፤ “እግዚአብሔር ታላቅ ነው! ለአገልጋዩ ሁኔታዎች ሁሉ ሲሳኩለት እግዚአብሔር ደስ ይለዋል!” ይበሉ። አንደበቴ ቀኑን ሙሉ ስለ ጽድቅህና ስለ ምስጋናህ ይናገራል።
መዝሙር 35:1-28 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ የሚከሱኝን ክሰሳቸው፥ የሚዋጉኝንም ተዋጋቸው። ጥሩርና ጋሻ ያዝ፥ እኔንም ለመርዳት ተነሥ። ሰይፍንና ጦርን ምዘዝ፥ የሚያሳድዱኝን ለመቃወም፥ ነፍሴን፦ መድኃኒትሽ እኔ ነኝ በላት። ነፍሴን ሊያጠፉ የሚሹ ሁሉ ይፈሩ ይጐስቁሉም፥ ክፉትን በእኔ ላይ የሚያስቡ ይዋረዱ ወደ ኋላቸውም ይመለሱ። በነፋስ ፊት እንዳለ ትቢያ ይሁኑ፥ የጌታም መልአክ ያስጨንቃቸው። መንገዳቸው ዳጥና ጨለማ ይሁን፥ የጌታም መልአክ ያሳድዳቸው። በከንቱ ያጠፉኝ ዘንድ ወጥመዳቸውን ሸሽገውብኛልና፥ ነፍሴን በከንቱ አበሳጭተዋልና። ያላወቁት ወጥመድ ይምጣባቸው፥ የሸሸጉትም ወጥመድ ይያዛቸው፥ በዚህ ወጥመድ ውስጥ ይውደቁ። ነፍሴ ግን በጌታ ደስ ይላታል፥ በማዳኑም ሐሴት ታደርጋለች። አጥንቶቼ ሁሉ እንዲህ ይሉሃል፦ አቤቱ፥ እንደ አንተ ማን ነው? ችግረኛን ከሚቀማው እጅ፥ ችግረኛንና ድሀውንም ከሚነጥቀው እጅ ታድነዋለህ። የሐሰት ምስክሮች ተነሡብኝ፥ የማላውቀውንም በእኔ ላይ ተናገሩ። በበጎ ፈንታ ክፋትን መለሱልኝ፥ ለብቻዬም ቀረሁ። እኔስ እነርሱ በታመሙ ጊዜ ማቅ ለበስሁ፥ ነፍሴንም በጾም አደከምኋት፥ ጸሎቴም ወደ ብብቴ ተመለሰ። ለወዳጄና ለወንድሜ እንደማደርግ አደረግሁ፥ ለእናቱም እንደሚያለቅስ ራሴን ዝቅ ዝቅ አደረግሁ። በእኔ ላይ ተሰበሰቡ ደስም አላቸው፥ ግፈኞች በእኔ ላይ ተሰበሰቡ እኔም አላወቅሁም፥ መቦጫጨቃቸውን አላቆሙም። ፈተኑኝ በሣቅም ዘበቱብኝ፥ ጥርሳቸውንም በእኔ ላይ አንቀጫቀጩ። አቤቱ፥ እስከ መቼ ድረስ ዝም ብለህ ታየኛለህ? ነፍሴን ከክፉ ሥራቸው ብቸኛዪቱንም ከአንበሶች አድናት። አቤቱ፥ በታላቁ ጉባኤ ውስጥ እገዛልሃለሁ፥ በብዙ ሕዝብ መካከልም አመሰግንሃለሁ። ከሐዲ ጠላቶቼ በእኔ ደስ አይበላቸው፥ በከንቱ የሚጣሉኝም በዓይናቸው አይጠቃቀሱብኝ። በእርጋታ በምድሪቱ ለተቀመጡት ሰላምን አይናገሩምና፥ በቁጣም ሽንገላን ይመክራሉ። አፋቸውንም በእኔ ላይ አላቀቁ፥ እሰይ እሰይ፥ ዓይናችን አየው ይላሉ። አቤቱ፥ አንተ አየኸው፥ ዝም አትበል፥ አቤቱ፥ ከእኔ አትራቅ። አምላኬ ጌታዬም፥ ትፈርድልኝ ዘንድ ተነሥ፥ አቤቱ፥ ፍርዴን አድምጥ። አቤቱ አምላኬ፥ እንደ ጽድቅህ ፍረድልኝ፥ በእኔም ምክንያት ደስ አይበላቸው። በልባቸው፦ እሰይ እሰይ፥ ነፍሳችንን ደስ አላት አይበሉ፥ ደግሞም፦ ዋጥነው አይበሉ። በመከራዬ ደስ የሚላቸው ይፈሩ፥ በአንድነትም ይጐስቁሉ፥ በእኔ ላይ የሚታበዩ እፍረትንና ጉስቁልናን ይልበሱ። ጽድቄን የሚወድዱአት ደስ ይበላቸው ሐሴትንም ያድርጉ፥ የባርያውን ሰላም የሚወድድ ጌታ ታላቅ ይሁን ዘወትር ይበሉ። ምላሴ ጽድቅህን ሁልጊዜም ምስጋናህን ይናገራል።