የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙር 35:1-14

መዝሙር 35:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እግዚአብሔር ሆይ፤ የሚታገሉኝን ታገላቸው፤ የሚዋጉኝንም ተዋጋቸው። ትልቁንና ትንሹን ጋሻ ያዝ፤ እኔንም ለመርዳት ተነሥ። በሚያሳድዱኝ ላይ፣ ጦርና ጭሬ ምዘዝ፤ ነፍሴንም፣ “የማድንሽ እኔ ነኝ” በላት። ሕይወቴን የሚፈልጓት፣ ይቅለሉ፣ ይዋረዱ፤ እኔን ለማጥፋት የሚያሤሩ፣ ዐፍረው ወደ ኋላቸው ይመለሱ። በነፋስ ፊት እንዳለ እብቅ ይሁኑ፤ የእግዚአብሔር መልአክ ያሳድዳቸው። መንገዳቸው ጨለማና ድጥ ይሁን፤ የእግዚአብሔር መልአክ ያባርራቸው። ያለ ምክንያት ወጥመዳቸውን በስውር አስቀምጠውብኛልና፤ ያለ ምክንያት ለነፍሴ ጕድጓድ ቈፍረውላታል። ያልታሰበ ጥፋት ይምጣባቸው፤ የሰወሩት ወጥመድ ይያዛቸው፤ ይጠፉም ዘንድ ወደ ጕድጓዱ ይውደቁ። ነፍሴም በእግዚአብሔር ደስ ይላታል፤ በማዳኑም ሐሤት ታደርጋለች። የሠራ አካላቴ እንዲህ ይልሃል፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ አንተ ማን አለ? ችግረኛውን ከርሱ ከሚበረቱ፣ ችግረኛውንና ድኻውን ከቀማኞች ታድናለህ።” ጨካኝ ምስክሮች ተነሡ፤ ስለማላውቀውም ነገር ጠየቁኝ። በበጎ ፈንታ ክፉ መለሱልኝ፤ ነፍሴንም ብቸኛ አደረጓት። እኔ ግን እነርሱ በታመሙ ጊዜ ማቅ ለበስሁ፤ ነፍሴንም በጾም አደከምኋት፤ ጸሎቴም መልስ ዐጥቶ ወደ ጕያዬ ተመለሰ። ለወዳጄ ወይም ለወንድሜ እንደማደርግ፣ እየተንቈራጠጥሁ አለቀስሁ፤ ለእናቴም እንደማለቅስ፣ በሐዘን ዐንገቴን ደፋሁ።

መዝሙር 35:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እግዚአብሔር ሆይ! የሚቃወሙኝን ተቃወማቸው፤ የሚዋጉኝንም ተዋጋቸው። ጋሻና ጥሩር ያዝ፤ መጥተህም እርዳኝ። በሚያሳድዱኝ ላይ ጦርና ሰይፍህን ምዘዝና “እኔ አዳኝህ ነኝ” ብለህ አረጋግጥልኝ። እኔን ለመግደል የሚፈልጉ ሁሉ ኀፍረትና ውርደት ይድረስባቸው! በእኔ ላይ የሚያሤሩም ሁሉ ተዋርደው ወደ ኋላቸው ይመለሱ! የእግዚአብሔር መልአክ ሲያሳድዳቸው፤ በነፋስ እንደሚበተን ገለባ ይሁኑ! የእግዚአብሔር መልአክ ሲያሳድዳቸው መንገዳቸው ጨለማና ድጥ ይሁንባቸው! ያለ ምክንያት ወጥመድ በድብቅ ዘርግተውብኛል፤ እኔንም ለመያዝ ጒድጓድ ቆፍረዋል። ያላሰቡት ድንገተኛ ጥፋት ይድረስባቸው፤ የደበቁት ወጥመድ ይያዛቸው በቈፈሩትም ጒድጓድ ወድቀው ይጥፉ! ነፍሴ በእግዚአብሔር ደስ ይላታል፤ በማዳኑም ሐሴት ታደርጋለች። ጌታ ሆይ! ሁለመናዬ እንዲህ ብሎ ይናገራል፤ ተበዳዮችን ከበደለኛ የሚያድን፥ ድኾችንና ተጨቋኞችን ከነጣቂዎች የሚጠብቅ እንደ አንተ ያለ ማነው? ክፉ ሰዎች ባልሠራሁት ወንጀል ከሰሱኝ፤ በማላውቀውም ነገር በሐሰት መሰከሩብኝ። እኔን ብቸኛ አድርገው ደግን በክፉ መለሱልኝ። እኔ ግን እነርሱ በታመሙ ጊዜ ማቅ ለበስኩ፤ ሰውነቴንም በጾም አጐሳቈልኩ፤ ጸሎቴም መልስ ሳያገኝ ቀረ። ያዘንኩትም ለወዳጅ ወይም ለወንድም የሚታዘነውን ያኽል ነው፤ እናቱ የሞተችበት ሰው የሚያዝነውን ያኽል ራሴን ዝቅ አድርጌ አለቀስኩ።

መዝሙር 35:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

አቤቱ፥ የሚከሱኝን ክሰሳቸው፥ የሚዋጉኝንም ተዋጋቸው። ጥሩርና ጋሻ ያዝ፥ እኔንም ለመርዳት ተነሥ። ሰይፍንና ጦርን ምዘዝ፥ የሚያሳድዱኝን ለመቃወም፥ ነፍሴን፦ መድኃኒትሽ እኔ ነኝ በላት። ነፍሴን ሊያጠፉ የሚሹ ሁሉ ይፈሩ ይጐስቁሉም፥ ክፉትን በእኔ ላይ የሚያስቡ ይዋረዱ ወደ ኋላቸውም ይመለሱ። በነፋስ ፊት እንዳለ ትቢያ ይሁኑ፥ የጌታም መልአክ ያስጨንቃቸው። መንገዳቸው ዳጥና ጨለማ ይሁን፥ የጌታም መልአክ ያሳድዳቸው። በከንቱ ያጠፉኝ ዘንድ ወጥመዳቸውን ሸሽገውብኛልና፥ ነፍሴን በከንቱ አበሳጭተዋልና። ያላወቁት ወጥመድ ይምጣባቸው፥ የሸሸጉትም ወጥመድ ይያዛቸው፥ በዚህ ወጥመድ ውስጥ ይውደቁ። ነፍሴ ግን በጌታ ደስ ይላታል፥ በማዳኑም ሐሴት ታደርጋለች። አጥንቶቼ ሁሉ እንዲህ ይሉሃል፦ አቤቱ፥ እንደ አንተ ማን ነው? ችግረኛን ከሚቀማው እጅ፥ ችግረኛንና ድሀውንም ከሚነጥቀው እጅ ታድነዋለህ። የሐሰት ምስክሮች ተነሡብኝ፥ የማላውቀውንም በእኔ ላይ ተናገሩ። በበጎ ፈንታ ክፋትን መለሱልኝ፥ ለብቻዬም ቀረሁ። እኔስ እነርሱ በታመሙ ጊዜ ማቅ ለበስሁ፥ ነፍሴንም በጾም አደከምኋት፥ ጸሎቴም ወደ ብብቴ ተመለሰ። ለወዳጄና ለወንድሜ እንደማደርግ አደረግሁ፥ ለእናቱም እንደሚያለቅስ ራሴን ዝቅ ዝቅ አደረግሁ።