መዝሙር 34:11-19
መዝሙር 34:11-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የዐመፃ ምስክሮች ተነሡብኝ፥ የማላውቀንም በእኔ ላይ ተናገሩ። ስለ በጎ ፋንታ ክፉን መለሱልኝ፥ ሰውነቴንም ልጆችን አሳጡአት። እኔስ ባሠቃዩኝ ጊዜ ማቅ ለበስሁ፥ ነፍሴንም በጾም አደከምኋት፤ ጸሎቴም ወደ ብብቴ ተመለሰ። ለወዳጆቼና ለወንድሞቼ እንደማደርግ አደረግሁ፤ እንደሚያለቅስና እንደሚተክዝ ራሴን ዝቅ ዝቅ አደረግሁ። በእኔ ላይ ተሰበሰቡ፥ ደስም አላቸው፤ ይገርፉኝ ዘንድ ተማከሩ፥ እኔ ግን አላወቅሁም። ተሰበሩ፥ አልደነገጡምም። ፈተኑኝ፥ በእኔ ላይም ዘበቱብኝ፥ ሣቁብኝም፤ ጥርሳቸውንም በእኔ ላይ አንቀጫቀጩ። አቤቱ፥ እስከ መቼ ድረስ ትፈርድልኛለህ? ነፍሴን ከክፉ ሥራቸው፥ ብቸኝነቴንም ከአንበሶች አድናት፥ አቤቱ፥ በታላቁ ጉባኤ ውስጥ እገዛልሃለሁ፥ በብዙ ሕዝብ መካከልም አመሰግንሃለሁ። በግፍ የሚጠሉኝ በላዬ ደስ አይበላቸው፥ በከንቱ የሚጠሉኝና በዐይናቸው የሚጠቃቀሱብኝም።
መዝሙር 34:11-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ልጆቼ ሆይ፣ ኑ፤ ስሙኝ፤ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ። ሕይወትን የሚወድድ፣ በጎውንም ያይ ዘንድ ዕድሜን የሚመኝ ማን ነው? አንደበትህን ከክፉ ነገር ከልክል፤ ከንፈርህንም ከሽንገላ ጠብቅ። ከክፉ ሽሽ፤ መልካሙንም አድርግ፤ ሰላምን ፈልጋት፤ ተከተላትም። የእግዚአብሔር ዐይኖች ወደ ጻድቃን ናቸው፤ ጆሮዎቹም ለጩኸታቸው ክፍት ናቸው። የእግዚአብሔር ፊት ግን፣ መታሰቢያቸውን ከምድር ለማጥፋት በክፉ አድራጊዎች ላይ ነው። ጻድቃን ሲጮኹ፣ እግዚአብሔር ይሰማቸዋል፤ ከመከራቸውም ሁሉ ያድናቸዋል። እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል። የጻድቅ መከራው ብዙ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ከሁሉም ያድነዋል።
መዝሙር 34:11-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ልጆቼ ሆይ! ኑ አድምጡኝ፤ እኔም እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ። ከእናንተ መኖርንና ለብዙ ዘመንም መልካም ነገርን ለማየት የሚመኝ ማነው? እንግዲያውስ መጥፎ ነገር ከማውራትና ሐሰት ከመናገር ተቈጠቡ። ከክፉ ነገር ሽሹ፤ መልካም ነገርንም አድርጉ፤ ሰላምን ፈልጉአት፤ ተከተሉአትም። እግዚአብሔር ወደ ጻድቃን ይመለከታል፤ ጸሎታቸውንም ያደምጣል። ክፉ አድራጊዎችን ግን ይቃወማል፤ መታሰቢያቸውንም ከምድር ላይ ያጠፋል። ጻድቃን ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉ፤ እርሱም ይሰማቸዋል፤ ከችግራቸውም ሁሉ ያድናቸዋል። ልባቸው ለተሰበረ እግዚአብሔር ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የደቀቀውንም ያድናቸዋል። ጻድቅ ብዙ መከራ ይደርስበታል፤ እግዚአብሔር ግን ከዚህ ሁሉ ያድነዋል።
መዝሙር 34:11-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የአንበሳ ደቦሎች ተቸገሩ፥ ተራቡም፥ ጌታን የሚፈልጉት ግን መልካሙን ሁሉ አያጡም። ልጆቼ ኑ፥ ስሙኝ፥ ጌታን መፍራት አስተምራችኋለሁ። ሕይወትን የሚመኝ ሰው ማን ነው? በጎንም ዘመን ለማየት የሚወድድ? አንደበትህን ከክፉ ነገር፥ ከንፈሮችህም ሽንገላን ከመናገር ከልክል። ከክፉ ነገር ሽሽ መልካምንም አድርግ፥ ሰላምን እሻ ተከተላትም። የጌታ ዐይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮዎቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና። መታሰቢያቸውን ከምድር ያጠፋ ዘንድ የጌታ ፊት ክፉን በሚያደርጉ ላይ ተነሥቶአል። ጻድቃን ጮኹ፥ ጌታም ሰማቸው ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው። ጌታ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፥ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።