መዝሙር 31:9-24
መዝሙር 31:9-24 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ በመከራ ውስጥ ነኝና ማረኝ፤ ዐይኖቼ በሐዘን ደክመዋል፤ ነፍስና ሥጋዬም ዝለዋል። ሕይወቴ በመጨነቅ፣ ዕድሜዬም በመቃተት ዐለቀ፤ ከመከራዬ የተነሣ ጕልበት ከዳኝ፤ ዐጥንቴም በውስጤ ሟሟ። ከጠላቶቼ ሁሉ የተነሣ፣ ለጎረቤቶቼ መዘባበቻ፣ ለወዳጆቼ መሣለቂያ ሆኛለሁ፤ መንገድ ላይ የሚያገኙኝም ይሸሹኛል። እንደ ሞተ ሰው ተረሳሁ፤ እንደ ተሰበረ የሸክላ ዕቃም ተቈጠርሁ። የብዙ ሰዎችን ሹክሹክታ እሰማለሁና፤ ዙሪያው ሁሉ ሽብር አለ፤ በእኔ ላይ ባሤሩ ጊዜ፣ ሕይወቴን ለማጥፋት ዶለቱ። እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔ ግን በአንተ እታመናለሁ፤ “አንተ አምላኬ ነህ” እልሃለሁም። ዘመኔ ያለው በእጅህ ነው፤ ከጠላቶቼ እጅ ታደገኝ፤ ከሚያሳድዱኝም አድነኝ። ፊትህን በአገልጋይህ ላይ አብራ፤ በምሕረትህም አድነኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ እጮኻለሁና አልፈር፤ ክፉዎች ግን ይፈሩ፤ ሲኦል ገብተውም ጸጥ ይበሉ። በጻድቁ ላይ በእብሪት የሚናገሩ፣ ትዕቢትንና ንቀትን የተሞሉ፣ ዋሾ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ። በሰዎች ልጆች ፊት፣ ለሚፈሩህ ያስቀመጥሃት፣ መጠጊያ ላደረጉህም ያዘጋጀሃት፣ በጎነትህ ምንኛ በዛች! ከሰዎች ሤራ፣ በማደሪያህ ውስጥ ትሸሽጋቸዋለህ፤ ከአንደበት ጭቅጭቅም፣ በድንኳንህ ውስጥ ትከልላቸዋለህ። በተከበበች ከተማ ውስጥ፣ የሚያስደንቅ ምሕረቱን ያሳየኝ፣ እግዚአብሔር ይባረክ። እኔ በደነገጥሁ ጊዜ፣ “ከዐይንህ ፊት ተወግጃለሁ” አልሁ፤ አንተ ግን ወደ አንተ ስጮኽ፣ የልመናዬን ቃል ሰማህ። እናንተ ቅዱሳኑ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ውደዱት! እግዚአብሔር ታማኞችን ይጠብቃል፤ ትዕቢተኞችን ግን ፈጽሞ ይበቀላቸዋል። እግዚአብሔርን ተስፋ የምታደርጉ ሁሉ፤ በርቱ፤ ልባችሁም ይጽና።
መዝሙር 31:9-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሆይ! በችግር ላይ ስለ ሆንኩ ምሕረትን አድርግልኝ፤ ዐይኖቼ፥ ነፍሴና ሥጋዬ በሐዘን ደክመዋል። ሕይወቴ በሐዘን ዕድሜዬም በመቃተት አለቀ፤ በችግሬ ምክንያት ኀይል አጣሁ፤ አጥንቶቼም ደከሙ። እኔ የጠላቶቼ መሳለቂያ፥ ለጐረቤቶቼ አስደንጋጭ፥ ለሚያውቁኝም አስፈሪ ነኝ፤ በመንገድ ሲያዩኝም ከእኔ ይሸሻሉ። እንደ ሞተ ሰው ተረሳሁ፤ ተሰብሮ እንደ ተጣለ የሸክላ ዕቃ ሆንኩ። የብዙ ሰዎችን ሹክሹክታ እሰማለሁ፤ በሁሉም አቅጣጫ ፍርሀት አለ፤ በእኔ ላይ ያሤራሉ፤ ሊገድሉኝ በማቀድ ያድማሉ። እግዚአብሔር ሆይ! አንተ አምላኬ ነህ፤ እኔ በአንተ እታመናለሁ። እኔ ሁልጊዜ በአንተ እጅ ነኝ፤ ከጠላቶቼ እጅና ከሚያሳድዱኝ ሁሉ አድነኝ። ወደ አገልጋይህ በፈገግታ ተመልከት፤ በዘለዓለማዊ ፍቅርህም አድነኝ። እግዚአብሔር ሆይ! ወደ አንተ በምጣራበት ጊዜ አታሳፍረኝ፤ ክፉዎች ግን ይፈሩ፤ ጸጥ ብለውም ወደ ሲኦል ይውረዱ። በጻድቅ ላይ በትዕቢትና በንቀት በኩራትም ስለሚናገር የሐሰት አንደበታቸውን ጸጥ አሰኝ። በአንተ ለመከለል ወደ አንተ ለሚጠጉ በሰዎች ሁሉ ፊት የምትሰጠው ለሚፈሩህ ያዘጋጀኸው ደግነት ምንኛ ትልቅ ነው! ከሚያሤሩባቸው ሰዎች በመኖሪያህ ጥላ ሥር ትደብቃቸዋለህ፤ ከመርዘኛ አንደበትም በከለላህ ትጠብቃቸዋለህ። በተከበበች ከተማ ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ በሚያስደንቅ ሁኔታ ዘላቂ ፍቅሩን የገለጠልኝ እግዚአብሔር ይመስገን! ከድንጋጤዬ የተነሣ ከፊትህ ያራቅኸኝ መስሎኝ ነበር፤ ነገር ግን ርዳታህን ፈልጌ ለምሕረት ወደ አንተ ስጣራ ጩኸቴን ሰማህ። እናንተ ለእርሱ የተቀደሳችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን ውደዱት፤ እግዚአብሔር ታማኞችን ይጠብቃል፤ ለትዕቢተኞች ግን ተገቢ ቅጣታቸውን ይሰጣል። እናንተ በእግዚአብሔር ተስፋ የምታደርጉ ሁሉ ጠንክሩ፤ በርቱም።
መዝሙር 31:9-24 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በጠላቴ እጅ አልዘጋኸኝም፥ በሰፊም ስፍራ እግሮቼን አቆምህ። ተቸግሬአለሁና አቤቱ ምራኝ፥ ዓይኔም ከኀዘን የተነሣ ደከመ፥ ነፍሴም ሆዴም። ሕይወቴ በኅዘን አልቃለችና፥ ዓመታቴም በልቅሶ ጩኸት፥ ኃይሌ በችግር ደከመ፥ አጥንቶቼም ተነዋወጡ። በጠላቶቼ ዘንድ ተነወርኹ፥ ይልቁንም በጎረቤቶቼ ዘንድ፥ ለሚያውቁኝም ፍርሃት ሆንሁ፥ በሜዳ ያዩኝም ከእኔ ሸሹ። እንደ ሞተ ሰው ከልብ ተረሳሁ፥ እንደ ተበላሸ ዕቃም ሆንሁ። የብዙ ሰዎችን ስድብ ሰምቻለሁና፥ በዙሪያው ፍርሃት ነበረ፥ በላዬ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ ነፍሴን ለመንጠቅ ተማከሩ። አቤቱ፥ እኔ ግን በአንተ ታመንሁ፥ አንተ አምላኬ ነህ አልሁ። ርስቴ በእጅህ ነው፥ ከጠላቶቼ እጅና ከሚያሳድዱኝ አድነኝ። ፊትህን በባርያህ ላይ አብራ፥ ስለ ምሕረትህም አድነኝ። አቤቱ፥ አንተን ጠርቻለሁና አልፈር፥ ክፉዎች ይፈሩ በሲኦልም ዝም ይበሉ። በድፍረትና በትዕቢት በመናቅም በጻድቅ ላይ የሚናገሩ የሽንገላ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ። በአንተ ለሚያምኑ በሰው ልጆች ፊት ያዘጋጀሃት ለሚፈሩህም የሰወርሃት፥ ቸርነትህ እንደምን በዛች! በፊትህ መጋረጃ ከሰው ክርክር ትጋርዳቸዋለህ፥ በድንኳንህም ከአንደበት ክርክር ትሸፍናቸዋለህ። በተከበበ ከተማ የሚያስደንቅ ምሕረቱን በእኔ የገለጠ ጌታ ይመስገን። እኔስ ከዓይንህ ፊት ተጣልሁ፥ በድንጋጤ አልሁ፥ አንተ ግን ወደ አንተ በጮኽሁ ጊዜ የልመናዬን ቃል ሰማኸኝ። ሁላችሁ ቅዱሳኑ፥ ጌታን ውደዱት፥ ጌታ እውነተኞችን ይፈልጋል፥ ትዕቢተኞችንም ፈጽሞ ይበቀላቸዋል።